1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለስደተኞች እንክብካቤ በዱስልዶርፍ

ዓርብ፣ ነሐሴ 15 2007

ከቁመቱ ቀውለል ያለ ነው፤ በዝግታ ወደ ዳሱ አቀና። የሹራብ ኮፍያው ላይ ሌላ ኮፍያ ደርቧል። «ሪቻርድ ይባላል ከጋና ነው የመጣው» ሲል ዱስልዶርፍ ከተማ ውስጥ ለስደተኞች ድጋፍ የሚያደርገው ድርጅት ማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ ማይክል ሉቃስ አስተዋወቀን። ድርጅቱ በእንግሊዘኛ ስቴይ (stay)ይሰኛል።

https://p.dw.com/p/1GJeh
Flüchtlingsinitiative Stay in Düsseldorf
ምስል DW/N. Niebergall

[No title]

ሪቻርድ የቢራ መጠጫ ጠረጴዛ ላይ ደገፍ ብሎ በመቀመጥ ለማይክል አንድ ደብዳቤ ገፋ አደረገለት። ደብዳቤው ጋናዊው ስደተኛ በሚቀጥለው ሣምንት የኾነ ቦታ የሥራ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት ይገልጣል። ልምምዱ በትምኅርት ቤት ግዴታ ነው። ሪቻርድ የሥራ ልምምዱን ማድረግ ከጀመረ ገና አራት ቀናት ነው የተቆጠሩት፤ ኾኖም ሌላ ቦታ ሌላ ሥራ እንዲፈልግ የሚገልጥ ደብዳቤ ነው የደረሰው።ጀርመንኛ ይረዳል መልስ መስጠት ግን አይችልም። ማይክል ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶታል። ብቻ ነገ በማለዳው ደውሎ ለሪቻርድ አንዳች ነገር ለማድረግ እንደሚሞክር ቃል ገብቶለታል።

በየሳምንቱ ሐሙስ ማይክል እና የሥራ ባልደረቦቹ እንዲህ አይነት ርዳታ ለስደተኞች ይሰጣሉ። በርካታ ሰዎች ከቋሚ ሥራቸው ውጪ ዱስልዶርፍ ውስጥ በሚገኘው ማኅበር የነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ። ማኅበሩ የተቋቋመው በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 ዓም ነው። በማኅበሩ ሕፃናት እና ወጣቶች እንዲገናኙ ዕድል ከመፈጠሩም ባሻገር የቋንቋ ስልጠና ይሰጥበታል። እንደ ቴአትር ቡድን እና የእግር ኳስ የመሳሰሉ የትርፍ ጊዜ እንቅስቃሴዎችም እንዲደረጉበት ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።

የ18 ዓመቱ ጋናዊ ወጣት ስደተኛ ሪቻርድ
የ18 ዓመቱ ጋናዊ ወጣት ስደተኛ ሪቻርድምስል DW/N. Niebergall

የማኅበሩ ደምበኞች ተገን ጠያቂዎች፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የተሰጣቸው ስደተኞች፤ እንዲሁም እንደ ጋናዊው ሪቻርድ «ወረቀት አልባ» ስደተኞች ናቸው። ሚካኤል ሉቃስ

«ከደምበኞቻችን መካከል ከፊሉ ወረቀት የሌላቸው ናቸው። ቀደም ሲል የመኖሪያ ፈቃድ እዚህ ጀርመን ውስጥ ተሰጥቷቸው የነበሩ፤ በተገን ጠያቂነት ሒደት ውስጥ አልፈው የተከለከሉ ይገኙባቸዋል። ሰዎቹ አኹን ሀገራቸው ባለው ኹኔታ ተመልሰው በኋላ ላይ ድምፃቸውን አጥፍተው ወደ ጀርመን ዳግም ጉዞ በማድረግ ወረቀት አልባ ኑሮ መግፋት አይፈልጉም።»

ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ዱስልዶርፍ በሚገኘው ማኅበር ውስጥ የሚኖራቸውን የንግግር ሰአት በልዩ ኹናቴ ነው የሚመለከቱት። ለአብዛኞቹ መድሐኒቶችን ለማግኘት ይኽ አጋጣሚ ወሳኝ ነው። ከዚህ ውጪ መድሐኒት ለማግኘት አለያም ለመታከም አዳጋች እንደሚኾንባቸው ስቴይ (Stay)በተሰኘው ማኅበር ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት ሬጂና ሐየር ይናገራሉ። ሕጋዊ ሰነድ ስለሌላቸውም የጤና ዋስትና ሊኖራቸው አይችልም። ይህ መታወቂያ የሌለው ሰው ደግሞ ጀርመን ውስጥ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አይችልም።

የጤና ዋስትና ለማግኘት እንዲህ አይነት ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡበት ወረቀት ስለማይኖራቸው ሁኔታውን ያወሳስበዋል። እናም አብዛኛዎቹ ስቴይ ማኅበር እስኪመጡ ድረስ ኅመማቸውን ደብቀው አለያም ችለው ለመኖር ይገደዳሉ። አብዛኞቹ ርዳታ ፈላጊዎች ነፍሰ-ጡሮች፣ ከፍተኛ የጥርስ ኅመም የሚያሰቃያቸው ሰዎች ይገኑበታል። መሰል ኅመም እና ነፍሰጡሮች ጀርመን ውስጥ በየትኛውም ሐኪም ቤት አለያም ክሊኒክ ሊታከሙ ይችላሉ። እነዚህ ስደተኞች ግን ህጋ ሰነድ የላቸውም አብዛኞቹ ሐኪሞች የጤና ዋስትና መታወቂያ ለሌላቸው ኅሙማን የህክምና አገልግሎት አይሰጡም። ኅመምተኞቹን በመጡበት እግራቸው ነው የሚመልሷቸው።

ሬጂና ሔየር እና ማይክል ሉቃስ
ሬጂና ሔየር እና ማይክል ሉቃስምስል DW/N. Niebergall

ሪቻርድ እና ጓደኞቹ ተመሳሳይ ዕጣ መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። ሪቻርድ እንደሚለው ከኾነ እናቱን ፍለጋ ወደ ጀርመን ከመጣ አንድ ዓመት ግድም ሊኾነው ነው። እናቱ ከጋና የወጣችው እሱ ሕፃን ሳለ ነው። ሪቻርድ ጀርመን መጥቶ እናቱን ማግኘት ችሎ ነበር። ግን ከእናቱ ጋር መኖር የተፈቀደለት 18 ዓመት እስኪሆነው ነበር። ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ ግን ጀርመን መኖር የተፈቀደለት የሥራ ልምምድ ስለሚያደርግ ብቻ ነው። ወደ ጋና ደግሞ መመለስ አይፈልግም። አባቱ በሕይወት የሉም። ጋና ውስጥ ሌሎች የቤተሰብ አባላት የሉትም። በጀርመን የሕይወት ዕጣ ፈንታው የቀን ተቀን ራስ ምታቱ ነው። የሥራ ልምምድ የሚያደርግበት ቦታ ደግሞ ገና በአራት ቀኑ ሌላ ቦታ እንዲፈልግ ደብዳቤ ጽፎበታል። የስቴይ አባላት ሚካኤል እና ጓደኞቹ ፣ ነገር ዓለሙ ለተመሳቀለባቸው እንደ ሪቻርድ ላሉ ሰዎች የተቻላቸውን ለማድረግ ይጥራሉ።

ኒና ኒበርጋል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ