1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሴቶች መብት የሚከራከረዉ አዲሱ ጥምረት

ዓርብ፣ መስከረም 28 2014

አዲስ አበባ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ በፖሊስ ክፉኛ ስትደበደብ የሚሳያወዉ ቪዲዮ የማኅበረሰቡን ልብ ሰብሮአል። ይህችን ሴትም ሆነ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡን የሚጠብቀዉ ፖሊስ ነዉ። ፖሊስ ኅብረተሰቡን ከነዚህ መሰል ጥቃቶች መጠበቅ ያለበት ትልቁ አካል ነዉ። መንግሥትም ዞር ብሎ፤ ተቋማቱን መፈተሽ ይኖርበታል።

https://p.dw.com/p/41OcA
Äthiopien Das äthiopische Netzwerk für Menschenrechtsverteidigerinnen
ምስል Privat

በጋራ ለሴቶች መብት እንቁም

«አዲስ አበባ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ በፖሊስ ክፉኛ ስትደበደብ የሚሳያወዉ ቪዲዮ የማኅበረሰቡን ልብ ሰብሮአል። ይህችን ሴትም ሆነ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡን የሚጠብቀዉ ፖሊስ ነዉ። ፖሊስ ኅብረተሰቡን ከነዚህ መሰል ጥቃቶች መጠበቅ ያለበት ትልቁ አካል ነዉ። ግን ይኸዉ አካል እራሱ አጥቂ ሆኖ ሲገኝ፤ መንግሥትም እራሱን ዞር ብሎ፤  ተቋማቱን መፈተሽ ይኖርበታል።»

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑ ብዙ አመላካች ነገሮች መኖራቸዉን የነገረች፤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር እና ባለፈዉ መስከረም 21 ቀን በ 45 ሴቶች በይፋ የተመሰረተዉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት አባል ማህሌት አብርሃም ናት። በርግጥ ጥምረቱ ትላለች ወጣት ማኅሌት አብርሃም፤ በርግጥ ጥምረቱ ከአንድ ዓመት በፊት ይመስረት እንጂ በኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ምክንያት ለአንድ ዓመት ሥራ አላከናወነም ነበር።  

Äthiopien Das äthiopische Netzwerk für Menschenrechtsverteidigerinnen
ምስል Privat

«የመሰረትነዉ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት ነዉ። ጥምረቱ  ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ነበር የተመሰረተዉ። ግን የዛሬ ዓመት የኮቪድ ማለትም የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት አደገኛ ሁኔታ ስለነበረ፤ በበይነ መረብ ማለትም « በኢንተርኔት» ነበር ዉይይት አካሂደን ጥምረቱን የመሰረትነዉ። አሁን እንዳደረግነዉ አማካሪ ኮሚቴዎች   አልነበረንም። በዚህም ጥምረቱ ምንም ስራ አልሰራም ነበር። መጀመርያም ይህ ጥምረት እንዲቋቋም መነሻ ሃሳቡን ያመጡት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ማዕከል፤ እንደዚሁም ደግሞ የሰብዓዊ መብት፤ ከፍተኛ ጽ/ቤት  አንድ ላይ በመሆን ነዉ። ከዚህ በኋላ ለሴቶች መበት የሚታገሉ ሴቶችም ወንዶችም ፤ ፍላጎታቸዉን እንዲያሳዩ እና እንዲልኩ አድርገን፤  ፈቃደኛ የሆኑ እና ፍላጎታቸዉን ያሳዩ የሰብዓዊ ተሟጋቾች ነበሩ፤ መጀመርያ ለጥምረቱ መመስረት ጉልህ ሚና የተጫወቱት።»  

የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት በንቁ ይከታተላል። ባለፈዉ ሰሞን አዲስ አበባ ጎዳ ላይ በሁለት ፖሊሶች ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን ስትደበደብ የነበረችዉ ሴት አይነት ጉዳይ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነዉ። ይሁንና ይህ ገጠመኝ ከእድለኞች አንዱ ነዉ ማለት ይቻላል። ምክንያቱም በቪዲዮ ተቀርፆ ማኅበረሰቡ ሊሰማዉ በቅቶአል።    

ኢትዮጵያዉያት ሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቁጥር ጥቂት ነዉ ባይባለም፤ በርግጥ መድረክ ላይ ወጥቶ ፤ ድምጽ ለሌላቸዉ ድምጽ የሚሆነዉ ሴት ተሟጋቾች ቁጥር እጅግ ጥቂት ነዉ።  

Äthiopien Das äthiopische Netzwerk für Menschenrechtsverteidigerinnen
ምስል Privat

በመጨረሻም፤ ወጣት ማኅሌት አብርሃም፤ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት በአሁኑ ወቅት 45 አባላት እንዳሉት ብሎም ጥምረቱ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ለሴቶች መብት የሚታገሉ ወንድ የሰብዓዊ መብት ተቆርቆርያዎችንም ጥምረቱ አባል ስለሚያደርግ ሴትም ሆነ ወንድ የሰብዓዊ መብት ያገባኛል የሚል ሁሉ  በአባልነት እንዲመዘገብ ጥሪ አቅርባለች።

« ጥምረታችን የተቋቋመዉ በቅርቡ ነዉ።  ጥምረቱ ገና 45 አባላት ብቻ ነዉ ያሉት። እንደተባለዉም ጥምረቱ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ለግፉሃ የሚጮሁ ወንዶችንም ያካተተ ነዉ። የፆታ እኩልነት ወንዶችም ከፍተኛ ሚና አላቸዉ። ለሴቶች መብት የሚከራከሩ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ተቋማችንን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀርባለሁ።»  

የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረትን ተቀላቅለን ለሴቶች መብት በጋራ ብንጮህ፤ በሃይማኖት በባህል፤ በአጉል ልማድ ምክንያት  በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን እንከላከል ያለችንን፤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት አባል ማህሌት አብርሃምን ለሰጠችን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን። ሙሉዉን ስርጭት ለመከታተል የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ