1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሱዳን የሚፈለገዉ የልማት ገንዘብና የለጋሾች ህብረት

ዓርብ፣ ሰኔ 3 1997

በእርስ በርስ ግጭት የደቀቀዉን የሱዳንን ህዝብ ካለበት ማህበራዊ ችግር ለማዉጣት ለጋሽ አገራት ለልማት ድጋፍ የሚዉል ገንዘብ ለመስጠት ቃል በገቡት መሰረት ማሰባሰብ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/E0jw

ለሱዳን በታለመዉ የለጋሾች ጉባኤ ላይ ቃል ከተገባዉ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዉስጥም ባለፈዉ ሚያዝያ ወር በኦስሎ በተደረገዉ ስብሰባ ወቅት 500 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።አስተባባሪዎቹ ግን ገና ብዙ እንጠብቃለን እያሉ ነዉ።
ምንም እንኳን ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በርካታ ለጋሾች አይናቸዉን ወደሱዳን በማዞር ልገሳ ቢጀምሩም ቅንጅት የጎደለዉ በመሆኑ ለብክነት ተዳርጓል በሚል ነዉ አዲስ የለጋሾች ቡድን ለመሰባሰብ የበቃዉ።
በሱዳን የሚገኘዉን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ቀዉስ ለማስወገድ የዕርዳታ ማሰባሰቡን ጥረትና የማስተባበሩን ስራ እየሰራች የምትገኘዉ ኖርዌይ ናት።
ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ዉስጥ በዋና ከተማዋ ዖስሎ የተካሄደዉን የለጋሾች ጉባኤ ተከትሎ የኖርዌይ መንግስት ከአለም ባንክ ጋር የልማት እርዳታዉን በተመለከተ በቅርበት መስራት ጀምሯል።
በሱዳን በቅርቡ የተደረሰዉ የሰላም ስምምነትና በዳርፉር ያልበረደዉን የግጭት ሁኔታና በየመጠለያዉ የሚገኘዉን ህዝብ ህይወት ለማረጋጋት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያስፈልጋል።
ለጉዳዩ ሊዉል የሚገባዉን ገንዘብ ለማግኘትም በለጋሾች አካባቢ ሊፈጠር የሚችለዉን ዉጥንቅጥ ለማስወገድም የዓለም ባንክ የተቀናጀ የዕርዳታ ፈሰስ ለመፍጠር የሚጠቀመዉን መንገድ ቀይሷል።
እነዚህ ጥምር በጀቶችንም የፕሮጀክት መደራረብን በማስወገድ ስልታዊ በሆነ መልኩ የግንባታ አቅምን ተጠቅሞ ስራ ላይ የሚዉሉበትን መንገድ አመቻችቷል።
እነዚህ የተቀናጁ የልማት በጀት ፈሰሶች ባለፈዉ ግንቦት ወር የተቋቋሙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር በመሆን የፕሮጀክት ቀረፃ ተግባር ጀምረዋል።
ትኩረት ያደረጉባቸዉ ግንባር ቀደም የልማት ዘርፎችም የመንገድ ግንባታ፤እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የማህበራዊ ልማት ማለትም እንደ ትምህርት፤ ጤናና ዉሃ አገልግሎቶችን መገንባት ነዉ።
በርካታ ለጋሽ ወገኖች የተሰባሰቡበት የዚህ የበጀት ፈሰስ አሰባሳቢ የበላይ አካል እንደሚሉት ቡድናቸዉ ለሱዳን የማገገሚያና የልማት ጥያቄን ማንሳት የጀመረዉ ባለፈዉ አመት ነበር።
የደቡብ ሱዳን አማፅያንንና የካርቱምን መንግስት ከሸመገሉት ወገኖች አንዱ የሆኑት የኖርዌይ አለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ሂልዴ ፍራፍጆርድ ጆሃንሰን እንደሚሉት ወደሱዳን የሚሄደዉ የልማት እርዳታ ዉጤት እንዲኖረዉ በተቻለ መጠን ተቀናጅቶ መሆን ይኖርበታል።
እሳቸዉ እንደሚሉት ከሆነ ግጭቱ ከበረደ በኋላ የተዘበራረቀ የለጋሾች ትርኢት በስፍራዉ አጋጥሟቸዋል።
በርካታ ለጋሾች በጋራና በተናጠል ያላቸዉን ለመለገስ ሞክረዋል ሆኖም ቅንጅት የጎደለዉ ስለነበር ዉጤት አልታየም።
ስለዚህም ይላሉ ሚኒስትሩ ይህ አይነቱ ሁኔታ መጠነኛ አቅም ባላቸዉ መንግስታት እንቅስቃሴ ላይ ብክነትን አስከትሎ ችግር ፈጣሪ ከመሆን አይርቅም።
ለዚህም ነዉ ኖርዌይ ለሰላም ስምምነቱ የምትችለዉን ሁሉ አድርጋ ዛሬ ለጋሾችን በማስተባበር በርከት ያለ የድጋፍ ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት የምታደርገዉ።
የዓለም ባንክም በበኩሉ ከማዕከላዊዉ የካርቱም መንግስትና ከቀድሞዉ አማፂ ቡድን ማለትም የሱዳን ህዝቦች ነፃ አዉጪ ንቅናቄ የቀረበለትን የልማት ድጋፍ ጥያቄ ይመረምራል።
ከዚያም ባንኩ ራሱን ጨምሮ እንደ የተባበሩት መንግስታትና ከሌሎች ዋና ዋና ለጋሾች የሚገኘዉ የድጋፍ ገንዘብ እንዴት ባለ መልኩ ለልማት መዋል እንዳለበት ምክሩን ይለግሳል።
በተጨማሪም በየስድስት ወሩ ሁሉም ለጋሾች በተገኙበት የሱዳን መንግስት ባለስልጣናትና የሲቪሉን ህብረተሰብ ተወካች እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ባካተተ መልኩ የተደረሰበትን እድገት ለመገምገም ስብሰባ ያካሂዳሉ።
በሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር አይዛክ ዲዋን እንደሚሉት ድርጅታቸዉ ገንዘቡ በተገቢዉ መንገድ ለታሰበለት ጉዳይ በአግባቡ መዋሉን ማረጋገጥ ይፈልጋል።
ይህም ሲባል ይላሉ አይዛክ ሙስና አይታሰብም፤ የተሰራዉ ስራና የወጣዉ ወጪ መመጣጠን አለበት፤ በዚያም ላይ አግባብ ያለዉ የወጪና ገቢ ምዝገባ መካሄድ ይኖርበታል።
ለዚህም ቁጥጥር ሲባል የሲቪሉ ህብረተሰብ ተወካዮች በየደረጃዉ በሚደረጉት የልማት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል።
በዚህም መንግስታቸዉ በትክክለኛዉ የልማት ተግባር ላይ ገንዘቡን ማዋል አለማዋሉን የመከታተል ሃላፊነት ይኖራቸዋል።
ያም ማለት ምንም እንኳን በተግባራዊ እንቅስቃሴዉ በቀጥታ መሳተፍ ባይችሉም በሚደረገዉ የልማት ሂደት ሁሉ ድምፅ ይኖራቸዋል።
በሂደቱም ከዚህ በፊት ለግብረ ሰናይ ተግባር በስፍራዉ ይንቀሳቀሱ የነበሩት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ የሚያበረክቱት ድርሻ እንደሚኖር ተገልጿል።