1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለማርስ ጉዞ፣ በምድር ላይ የ 105 ቀናት ዝግጅት፣

ረቡዕ፣ ሐምሌ 8 2001

«የስበት ኃይል አለመኖር ብቻ አይደለም በሥነ ልቡና ላይ ተጽእኖ የሚያሣርፈው። እንበል ወደ ማርስ የበረራ ጉዞ ተሳታፊ ብሆን፣ መሬት አድማስ ላይ አንዲት ነጥብ ሆና ነው የማያት። እናም ፣ በፍጹም ፣ በሩን ልክፈትና ወደቤቴ ልመለስ የማይባልበት ሁኔታ ነው። »

https://p.dw.com/p/IqI6
ለማርስ ጉዞ፣ በምድር ላይ የ 105 ቀናት ዝግጅት፣
ቀጣዩ የ 520 ቀናት ሙከራ ከመከናወኑ በፊት፤ ለማርስ የበረራ ጉዞ፣ በምድር ላይ በተካሄደው 105 ቀናት በወሰደው የመጀመሪያው ቅድመ-ዝግጅት፣ ሞስኮ ውስጥ ፣ዝግ በሆነ ልዩ ቤት ፣ ምርምራቸውን ያጠናቀቁ ሩሲያውያንና ምዕራብ አውሮፓውያን ጠፈርተኞች፣ምስል picture-alliance/ dpa

ለማርስ ጉዞ፣ በምድር ላይ የ 105 ቀናት ዝግጅት፣ከሳይንስ ጋር ግንኙነት ያለው ዜና በጥቂቱ--

አምስተርዳም፣

- የሰው ጽንስ ፣ በ 30ኛው ሳምንት ማለት ከ 4 ወር ገደማ አንስቶ የማስታወስም ሆነ የማስተዋል ችሎታ ያለው መሆኑን ኔደርላንዳውያን ሀኪሞች አስታወቁ። በ ማስትሪኽት ከተማ የህክምና ጣቢያ ፣ የማኅጸን ወይም የሴቶች ጉዳይ የህክምና ፕሮፌሰር Jan Nijhuis እንደገለጹት፣ በማህጸን ውስጥ የጽንስን እንቅሥቃሴ መከታተል በሚያስችል መሣሪያ ረዳትነት ጽንስ ለተወሰኑ ደቂቃዎችየሚያጋጥመውን ማስታወስ እንደሚችል ተደርሶበታል። 38 ሳምንት ዕድሜ ያለው ጽንስ ደግሞ ይበልጥ ያስታውሳል። ይህ ምርምር ፣ ገና ያልተወለዱ ህጻናትን አእምሮ ዕድገት ለመከታተል የሚበጅ መሆኑም ተመልክቷል።

ዌሊንግተን፣

- በሪኽተር መለኪያ 7.8 የደረሰ ኃይለኛ የምድር ነውጥ ፣ ዛሬ ፣ ደቡብ-ምዕራቡን የኒው ዚላንድ ጠረፍ የመታ ሲሆን፣ ብርቱ የውቅያኖስ ማዕበል (ሱናሚ)እንዳያጋጥም ማስጠንቀቂያ ቀርቧል። በደቡቡ የኒው ዚላንድ ደሴት፣ ኢንቨርካርጊል ከተሰኘችው ከተማ በስተምዕራብ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ራቅ ብሎ፣ 33 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ባለው የውቅያኖስ ወለል፣ የምድር ነውጥ መከሠቱን የመዘገበው የዩናይትድ ስቴትስ የሥነ-ምድር ጥናት ነክ መሥሪያ ቤት ነው።

ፍሎሪዳ፣

-መብረቅና ዶፍ ፣ እንዲሁም ሥነ-ቴክኒካዊ እክል፣ የ NASA ን፣ ከፍሎሪዳ Endeavour የተሰኘችውን መንኮራኩር የማምጠቅ መርኀ-ግብር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 5 ጊዜ ማስተጓጎሉ ተነገረ። ከትናንት በስቲያ ይሳካ ይሆናል ተብሎ የታሰበው መርኀ-ግብር አልሠመረም። እናም ቅድመ-ግዴታዎች ከተሣኩ፣ «ኤንደቨር» ፣

ዛሬ፣ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት ላይ፣ ወደ ዓለም አቀፉ የኅዋ ጣቢያ ትመጥቃለች። ይህችው መንኮራኩር በመጀመሪያ ባለፈው ሰኔ 6 ቀን 2001 ዓ ም ነበረ ትመጥቅቃለች ተብሎ ቀጥሮ ተይዞላት የነበረው። ሆኖም፤ ከውስጧ ፈሳሽ ሃይድሮጂን በመንጠባጠቡ የማምጠቁን እርምጃ መግታት ግድ ነው የሆነው። «ቻሌንጀር» የተባለችውን መንኮራኮር የተካችው «ኤንደቬር» 1,7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ማስወጣቷ ተመልክቷል። መንኮሯኩሯን የማምጠቋ አቅድ ዛሬ ወይም ነገ ካልተሣካ፣ ወደ ሐምሌ 19 ቀን 2001 ዓ ም ይገፋል። በኤንደቬር መንኮራኩር የሚጓዙት 6 አሜሪካውያንና አንድ ካናዳዊ ሲሆኑ፣ እነርሱም ከምድራችን 350 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓለም- አቀፍ የምርምር ጣቢያ፣ አንዳች የአየር ግፊት በሌለበት ጠፈርተኞች ምርምር የሚያካሂዱበትን መድረክ ይገጣጥማሉ።

ሙዚቃ-------

ቀደም ሲል መጨረሻ ላይ፣ የኅዋን ጉዞ የተመለከተ ዜና ነበረ ያዳመጥን። የቅርቡን ጉዞ የተመለከተ ማለት ነው!። ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ- ጊዜ፣ አልፎ -አልፎ እንዳወሳነው፣ በኅዋ ምርምር ሰፋ ያለ ምርምር ያደረጉት መንግሥታት ፣ የላቀ፣ ረጅም የኅዋ ጉዞ መርኀ-ግብር አላቸው። ለዚህም በየደረጃው ዝግጅታቸውን ማጠናከራቸው አልቀረም። ወደፊት ወደ ማርስ ደርሶ-መልስ ፣ በሚወስደው አንድ ዓመት ከ 155 ቀናት ጉዞ ፣ ጠፈርተኞች ዝግጁ ሆነው እንዲገኙ ለማለማመድ ይመስላል፣ሞስኮ አቅራቢያ በተዘጋጀ መንኮራኩር መሰል ፣ ልስን ክፍል ውስጥ ፣ የተዘጋጀውን የመጀመሪያውን የ 105 ቀናት ፈተና አልፈው በትናንቱ ዕለት ተገልለው ከቆዩበት ልዩ ቤት ወጥተው፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል። በዚያ የቆዩት 6 ሰዎች፣ 4 ሩሲያውያን፣ አንድ ጀርመናዊና አንድ ፈረንሳዊ ሲሆኑ፣ ሩሲያዊው ኮስሞኖትና ሳይንቲስት ሰርጌይ ራያዛንስኪ በሞስኮ የህክምናና የሥነ ህይወት ጉዳይ እንከኖች ተመራማሪ ተቋም ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቡድኑ የመግባባት ደረጃ ፍጹም አርኪ መሆኑን ነው ያስረዱት። 6 ቱ ጠፈርተኞች ፣ ከመጋቢት 22 ቀን 2001 ዓ ም አንስቶ ትናንት እስከተለቀቁበት ዕለት ድረስ ፣የፀሐይ ብርሃን ሳያዩ፣ በግልና በኅብረት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ማከናወናቸው ነው የተነገረላቸው። የሩሲያው «ሮስኮስሞስ» የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤትና የአውሮፓ የኅዋ ምርምር-ነክ መ/ቤት፣ ተገልለው የቆዩትን ጠፈርተኞች የሥነ ልቡና ይዞታ መርምረዋል። የጀርመን የአየርና የኅዋ ምርምር ማዕከል ኀላፊ ዮሐን ዲትሪኽ ቮኧርነር ፣ ይኸው ምርምር ለለሰው ልጅ፣ ትንሽ፣ ለማርስ ጉዞ ደግሞ ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።

« በመጀመሪያ ፣ መርኀ ግብሩ ከጅምሩ እስከፍጻሜው በመሳካቱ ተደስቼአለሁ። ተረት ሳይሆን በገሃድ ፣ ከዚያ በፊት የማይተዋወቁ ሰዎች 105 ቀናት ሙሉ እርስ በርሳቸው አንዳች ሳንክ ሳያጋጥማቸው መመለሳቸው አርኪ ነው። --»

ከ6ቱ ጠፈርተኞች መካከል፣ ጀርመናዊው የመከላከያ ሚንስቴት ኢንጅኔርና አስትሮኖት ኦሊቨር ክኒከል፣ ከውጭው ዓለም ጋር እንዳይገናኙ ጥትቅም ብሎ ተዘግቶ በነበረው ልዩ ቤት ውስጥ፣ የየትኛውም ሀገር ዜጋ መሆን አንዳች ያስከተለው ችግር እንዳልነበረና በዚያ ውስጥ ልምምድ ማድረጋቸውን ፣ ማጥናታቸውንና የራሳቸውን አትክልት በመትክል በመንከባከብ ላይ አትኩረው እንደነበረ አስረድቷል። መምሸት-መንጋቱ፣ የሆነው ሆኖ ለአነርሱ ተለይቶም አይታወቅም ነበረና አሰልቺ መምሰሉን ክኒከል አልደበቀም።

«የመጀመሪያዎቹ 50 ቀናት ሆኑ ወይም 105 ቀናት፣ ሆነም-ቀረ በተመሳሳይ ሁኔታ ነበረ ዕለቱ የሚያልፈው። አንድ ዓይነት፣ አሰልቺ -ዓይነት ነበረ፣ ማለት ይቻላል።»

በተጠቀሰው የፍተሻ ልዩ ቤት የቆዩት ጨፈርተኞች ሁሉም ክብደት መቀነሣቸውን ፣ በማየት ብቻም ማወቅ እንደተቻለ ተነግሮአል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚበሉት፣ ጨው ያለበት ምግብ ፣ የጨዉ መጠን እንዲቀነስ ተደርጎ በቀን 6 ግራም ጨው ብቻ ነበረ የተፈቀደላቸው። ይህ ፣ በደም ግፊት ረገድ ምን እንዳስከተለም መመርመሩ አልቀረም። አውጥና ጎመን መሰል አትክልቶችን ማልማቱ ፣ በሥነ-ልቡና በኩል የሚያረጋ ሁኔታን ፈጥሮላቸው እንደሁ፣ ሆን ተብሎም የስልክ ግንኙነት ለአጭር እንደተቋረጠባቸው፣ ምን ተሰምቷቸው እንደነበረ ለማወቅ ተመራማሪዎቹ ጥረት አድርገዋል። ሩሲያዊው ከፕቴን ሰርጌይ ራዛንስኪ በዚያ ወደ ማርስ እንደሚደረግ በረራ ይቆጠር ዘንድ በታሰበው የ 50 ሚሊዮን ኪሎሜትር ጉዞ፣ ባልደረቦቻቸው አንዳች የመሰላቸት ስሜት እንዳልተንጸባረቀባቸው ነበረ ያስረዱት።

«በአጽንዖት መናገር የምፈልገው እስካሁን አብሬአቸው ከሠራሁ ሰዎች መካከል፤ እንደዚህኛው ቡድን እጅግ ያረካኝ የለም። ምንጊዜም የማንረሣው ግሩምና ልዩ ተመክሮ ነው።»

በተጠቀሰው የማርስ ጉዞ ዝግጅት ፣ 105 ቀናት ዝግ በሆነ 180 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ይዩ ቤት ውስጥ የቆዩት ጠፈርተኞች ፣ ወደፊት ተጨማሪ ምግብ የሚሰጥ ከሆነ ፣ ለሌላ ተመሳሳይ ሙከራም መሰለፍ እንደሚችሉ ነው የተነገረው። በመጪው 2010 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፣ በዚያው በሞስኮ አቅራቢያ ለ 520 ቀናት ተመሳሳይ ፍተሻ ይካሄዳል። አሁንም፣ የጀርመን የአየርና የኅዋ ምርምር ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮሐን ዲትሪኽ ቮርነር --

«የስበት ኃይል አለመኖር ብቻ አይደለም በሥነ ልቡና ላይ ተጽእኖ የሚያሣርፈው። እንበል ወደ ማርስ የበረራ ጉዞ ተሳታፊ ብሆን፣ መሬት አድማስ ላይ አንዲት ነጥብ ሆና ነው የማያት። እናም ፣ በፍጹም ፣ በሩን ልክፈትና ወደቤቴ ልመለስ የማይባልበት ሁኔታ ነው። »

ወደ ማርስ የበረራ ጉዞ ለማድረግ ፣ በሥነ ቴክኒክ ረገድም ገና ብዙ የሚጣሩ ጉዳዮች አሉ። ትክክለኛ ገሐዳዊ የማርስ ጉዞ፣ በሚበጡት 30 ወይም 40 ዓመታት ነው ተግባርዊ ሊሆን የሚችለው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ