1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሄለን ጆሴፍ

Thuso Khumalo
ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 2012

ሄለን ጆሴፍ የተወለዱት እጎአ ሚያዚያ 8 ቀን 1905 ዓ ም ዌስት ሱሴክስ እንግሊዝ ውስጥ ነው። አብዛኛውን የልጅነት እድሜያቸውን ያሳለፉት ለንደን ከተማ ነው። በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከተመረቁ በኋላ እና በ 1930 ዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከመሄዳቸው በፊት በሕንድ ሀገር በመምህርነት አገልግለዋል።

https://p.dw.com/p/3gRCX
African Roots | Helen Joseph

አንድ የጥርስ ሀኪምን አግብተው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ጥሩ ህይወት ይኖሩ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከወታደሮች ጋር የነበራቸው ቆይታ ዓይናቸውን ከፍቶላቸዋል። ነገር ግን እ.ጎ.አ. በ 1952 የአፓርታይድን ትግል እንዲሳተፉ የገፋፋቸው የማህበራዊ ስራቸው ነው - ልክ እንደ ሌሎች ዝነኛ ሠራተኞች  ዊኒ ማዲኪዜላ-ማንዴላ ። ዶይቸ ቬለ DW ከአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ እና የኔልሰን ማንዴላ የቀድሞ ቃል አቀባይ ካርል ኒሀውስ ጋር የሄለን ጆንሰንን ህይወት በሚመለከት ቃለ መጠይቅ አካሂዷል። 
DW : ከሄለን ጆሴፍ ጋር መቼ ተገናኙ?
ካርል ኒሀውስ: ሄለን ጆሴፍን በ 19 ዓመቴ ነው የተዋወኳቸው። እናም እሳቸው በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ  የፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል አንዷ ነበሩ። 
ሄለን ጆሴፍ ምን አይነት ሰው ነበሩ? 
እጅግ የላቀ መርህ የሚከተሉ ሰው ነበሩ። ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ እኩል ናቸው የሚለው ክርስቲያናዊ አመለካከት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። ስለሆነም ዘረኛው የአፓርታይድ መንግስትን መቃወም እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። ስለዚህ የ ANC ጥምረት የሆነው የዲሞክራቶች ኮንግረስ ውስጥ ተሳትፈዋል። 
የ ANC ጥምረት አፓርታይድ የከፋፈላቸው የሁሉም ወገኖች ድጋፍ ነበረው። እንዴት ሕብረቱ የመሪነት ዕድል ሊሰጣቸው ቻለ?
አመለካከታቸን በግልፅ የማስቀመጥ ችሎታቸው የዚያ ኅብረት ግንባር ቀደም መሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በ 1956 በኪሊፕታውን በተካሄደው ሕዝባዊ  ሰልፍ ላይ የሕዝባዊ ነጻነት ቻርተሩን አንድ ክፍል እንዲያቀርቡ እና በ 1956 ደግሞ የህብረቱ ህንፃዎች ፊት ለፊት የተደረጉ ሰልፎችን እንዲመሩ እድል ተሰጥቷቸዋል።

African Roots | Helen Joseph

እ.ጎ.አ. ነሐሴ 9 ቀን 1956 ፣ 20,000 ሴቶች በአፓርታይድ ፖሊሲዎች ላይ ቁጣቸውን ገልፀው ነበር። ከዚህ አንዱ የሴቶችን የመንቀሳቀስ ነፃነታቸውን የሚገድብ እና ቤተሰቦቻቸውን ሰርተው እንዲደግፉ የማያግዝ ነበር። ሄለን ጆሴፍ ከጥቁር ፣ ከ“ከለርድ” እና ከህንድ ሴቶች ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ጄ ጂ ስትሪጃምስ ቢሮ ጽሕፈት ቤት የተደረገውን ሰልፍ በመምራት ፊርማ አሰባስበዋል። ከ እሴቶቻቸው መካከል  የትኞቹ ይገኙበታል?
ሴቶች ለራሳቸው መቆም እና መታገል እንዳለባቸው ያምኑ ነበር።  የሴቶች ጥቃት ፈጻሚዎች ላይም ቅጣት ሊበየንባቸው ይገባል የሚል ዕምነት ነበራቸው። 
እኝህ ነጭ የእንግሊዝ ተወላጅ ሴት ከፀረ አፓርታይድ ትግል ጋር የተቀላቀሉት እንዴት ነበር?
ዘረኛ ላልሆነ ማህበረሰብ ይሰሩ ነበር። ለሁሉም ደቡብ አፍሪቃውያን ነፃነትም ይሹ ነበር። እንደሳቸው ፍፁም ዘረኝነት የሌለበት ሰው ገጥሞኝ አያውቋም። 
የአፓርታይድ ስርዓት በተጠናከረበት ጊዜ ሄለን ጆሴፍ የፀረ አፓርታይድ ታጋዮች የመጀመሪያ ትውልድ ነበሩ ። ስለ እሷቸው ምን ያስታውሳሉ? 
እኔ በ 70 ዎቹ መገባደጃ ላይ ሳሉ ነው ያገኘኋቸው። በዛም ወቅት ጠንካራና በፀረ አፓርታይድ ትግል ሙሉ በሙሉ ይሳተፉ ነበር። በዛም ወቅት ኖርዝክሊፍ ጆሃንስበርግ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ የቁም እስረኛ ነበሩ.
ሥርዓቱ ለነጭ ተቃዋሚዎቹም የማይበገር ነበር። ሄለን ጆሴፍን ያጋጠማቸውን የጭካኔ ርምጃ ለመታዘብ ችለው ነበር ይሆን? 
ያረጁ እና ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ዕድሜ ላይ ሆነው እንኳን በርካታ ጊዜ ነጭ የአፓርታይድ ደጋፊዎች እቤታቸው እየሄዱ ተኩስ ከፍተውባቸው ያውቃሉ። አስታውሳለሁ እንደዚህ አይነት ክስተቶች የተፈጠረበት አንድ ቀን ጠዋት ቤታቸው ስደርስ ጥይት የተተኮሰባቸው የመስኮት መስታዎት ስብርባሪዎችን ሲጠርጉ አገኘኋቸው ። አይናቸው ደም ለብሶ ነበር። በጣምም ተናደዋል። እና ደጋግመው ይሉ የነበሩት ነገር ፤ እኛን መግደል ይችላሉ። ነገር ግን የዚህች ሀገር የነፃነት ትግል ዓላማ በጭራሽ መግደል አይችሉም የሚል ነበር ።
አስታውሳለሁ እኔ የታሰርኩ ጊዜም ጠይቀውኝ ነበር። ፍርድ ቤት የቀረብኩ ጊዜ በተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ሆነው ፍርድ ቤት እፊት ለፊት ያለው ቦታ ላይ ነበር የተቀመጡት። 
እቤታቸው በጠረጴዛ ላይ ካስቀመጡት አንድ ከእንጨት የተሰራ መስቀል ፊት አብረን ተንበርክከን እንድንፀልይ ሁልጊዜ ይጠይቁኝ ነበር። ናዚዎችን እና ዘረኝነትን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር።

ሄለን ጆሴፍ

እርሳቸው ያደርጓቸው ከነበሩ ነገሮች ውስጥ የሚያስታውሷቸው የትኞቹ ናቸው?
በእስር ላይ የሚገኙ እና ቤተሰቦቻቸው ሁሌ እንዲታወሱ ያደርጉ ነበር። ሁል ጊዜ የገና ዕለት እቤታቸው ድግስ ያዘጋጁ ነበር እና እኩለ ቀን 6 ሰዓት ላይ ብርጭቆዋቸውን ያነሱና «ከጎናችን መገኘት ላልቻሉት ባልደረቦቻችን» ይላሉ።  
የሄለን ጆሴፍ የመጨረሻዎቹ ቀናት ምን ይመስሉ ነበር? 

እስከ መጨረሻ እስትንፋሻቸው ድረስ ታግለዋል። ህይወታቸው ስታልፍ አልጋቸው ጎን ነበርኩ። ልክ  የገና ቀን እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ነው የሞቱት። ጆሃንስበርግ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በስማቸው የሚጠራው የሄለን ጆሴፍ ሆስፒታል ውስጥ ነበር ያረፉት። 
ይህ የሆነው ደቡብ አፍሪቃ ለዲሞክራሲ መንገዱን እየጠረገች በነበረችበት ወቅት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር  ጄ ጂ ስትሪዶም ሆስፒታል በሄለን ጆሴፍ ስም 1997 ሊሰየም የቻለው በሴቶች ተቃውሞ ውጤት ነው። ይህ ደግሞ ከወይዘርዋ የረዥም ዘመን ባልደረቦች በርካታ ውጤቶች አንዱ ነው። ለመሆኑ ሄለን ጆሴፍ ሁልጊዜ በትግሉ አራማጆች ውሳኔ ይስማሙ ነበር?   
በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ከሄለን ጆሴፍ ጋር ስወያይ እንደነገሩኝ ከሆነ « ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ እና የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ከገዢዉ ፓርቲ ጋር) በሚደራደሩበት ወቅት ብዙ ጉዳዮችን አሳልፈዉ ለመስጠት መስማማት ጀምረዋል የሚል ስሜት ነበራቸው።ለፍትሕ የተከፈለዉ ዋጋ ችላ ተብሎ እርቅ ለመፍጠር የተቀረፀዉ ፕሮጀክት ከፍተኛ እዉቅና ተሰጥቶታል ብለዉም ያምናሉ።»  
ካርል ኒሀውስ የገዥው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) አርበኛ ሲሆኑ ላለፉት 42 ዓመታት የፓርቲ አባል ሆነው አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት የአንድ ወታደራዊ አርበኞች ማህበር ብሔራዊ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። 
ቃለ መጠይቅ፦ በ ቱሶ ኩማሎ

ሄለን ጆሴፍ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።