1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የስኳር ፋብሪካዎች የአክሲዮን ሽያጭ መጀመር

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2011

በመንግስት ስር የሚገኙ ሁለት የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎችን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር የአክሲዮን ሽያጭ ተጀመረ። የአክሲዮን ሽያጩን ዛሬ ይፋ ያደረገው የኢትዮ-ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ነው። 

https://p.dw.com/p/3IcCO
Wonju Zucker Fabrik
ምስል DW/G. Tedla HG

ሁለት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት የአክሲዮን ሽያጭ ተጀመረ

በመንግስት ስር ያሉትን የወንጂ ሸዋ እና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት የአክስዩን ሽያጭ መጀመሩን የኢትዮ-ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ። ማህበሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው የስኳር ፋብሪካዎቹን አክስዮን ከ40 ሺህ በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ለመሸጥ እቅድ አለው። የየአካባቢዎቹ ማህብረሰብ በአምስት ዓመት የሚከፈል ብድር ወስደው አክሲዮን እንዲገዙ ለማስቻል ማህበሩ ከአዋሽ እና ንብ ኢንተርናሽናል ባንኮች ጋር የ800 ሚሊዮን ብር የብድር ስምምነት መፈረሙንም ይፋ አድርጓል። 

የኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ፕሬዚደንት አቶ ለማ ጉርሙ ማህበሩ “በወንጂ እና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ያተኮረው መስራቾቹ ከዚያ የመጡ በመሆናቸው እና አካባቢውንም በደንብ የሚያውቁት በመሆኑ ነው” ብለዋል። ከዚም ባሻገር የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ታሪክ አካል በመሆኑ ትኩረት እንደተደረገበት ገልጸዋል። 

የእነርሱ አክሲዮን ማህበር ከዚህ ቀደም ከታዩት የሚለይበትን አካሄድ ሲያስረዱ ደግሞ “ውጭ ምንዛሬን በተመለከተ እናት ኩባንያው የሆነው፣ ሆላንድ ያለው፣ ከ140 ዓመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ልምድ ያለው ኤች ቢ ኤ ኢንተርናሽናል ሸሪካችን ነው” ብለዋል። የአክሲዮን ማህበሩ ለማህበረሰቡ ያመቻቸው ዕድልም የተለየ እንደሆነ ይገልጻሉ። “ከ40 ሺህ ሰው በላይ የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሆን በአምስት ዓመት የግል ብድር ወስደው ከደመወዛቸው እና ከሌላ ገቢያቸው እየከፈሉ አክሲዮን እንዲገዙ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ስምምነት ከትልልቆቹ ባንኮች አዋሽ እና ንብ ጋር መፈረማችን ሞዴሉንን ለየት ያደርገዋል” ሲሉ የቦርዱ ፕሬዝዳንት አብራርተዋል። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ