1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ፈተና መጀመር

ሰኞ፣ ሰኔ 3 2011

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታዩ ግጭቶች እና መፈናቀሎች ጋር ተያይዞ የመማር ማስተማሪ ሂደት ሲስተጓጎል መቆየቱ ቢነገርም፤ ዛሬ ለ10ኛ ክፍል የሚዘጋጀው ሀገር አቀፍ ፈተና መሠጠት ተጀምሯል።

https://p.dw.com/p/3K8no
Schulprüfung unter spezielle Militär Garde
ምስል DW/N. Desalegen

የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ተጀመረ

በተለያዩ ክልሎች የፈተናው አሰጣጥ ሂደት የተጀመረ ሲሆን በተለይ በትግራይ ክልል በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናው እየተካሄደ መሆኑን ከመቀሌ ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የላከል ዘገባ ያስረዳል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንደገለፀው ዘንድሮ  በትግራይ  ክልል  223  ሺህ ተማሪዎች  ሀገራዊ እና ክልላዊ ፈተና ይወስዳሉ።  ከነዚህ  መካከል 89 ሺህ ተማሪዎች የአስረኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳኘው አይጠገብ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከፌደራል ትምህርትና ምዘና ሴክተር መሥርያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎች ጋር ሲሰራ መቆየቱ ገልጸዋል።  

አብዛኛው አካባቢው በኮማድ ፖስት ሥር የሚገኘው ቤንሻንጉል ክልልም የዘንድሮው የሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው። በግጭቶች ምክንያት ከትምህርት ጊዜያቸው ዘግይተው የጀመሩ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝግጅቱ ተጠናቆ እየተፈተኑ እንደሆነ ከአሶሳ ዘጋቢያችን ነጋሳ ደሳለኝ በላከው ዘገባ ገልጿል። በተለይም በመንግሥት እና  በግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ዛሬ ፈተና መጀመራቸው ነው የተገለፀው።

Schulprüfung unter spezielle Militär Garde
ቤኒሻንጉል ተማሪዎች በፈተና ላይምስል DW/N. Desalegen

በአማራ ክልልም ፈተናው መሰጠት መጀመሩ ቢነገርም፤ ከ7ሺህ በላይ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ የሚሰጡትን የ10ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች እንደማይፈተኑ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። ወላጆች እና ተማሪዎች በምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ተማሪዎቹ ትምህርት ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ  በመላው የክልሉ አካባቢዎች ፈተናው በመልካም ሁኔታ እተካሄደ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ አንዳለ በቅርቡ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር  ካነጋገራቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰው መሆን አበረና የሺወርቅ አዘናው በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ ለፈተናም እንደማይቀመጡ ገልጸውለታል።

Ato Mulaw Abebe
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ምስል DW/A. Mekonne

የተማሪ ወላጆችም መንግሥት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ሚያደርገው ጥረት መልካም ቢሆንም የትምህርት ተቋማትን በማደረጀት ትምህርት እንዲቀጥሉ ማድረግ እንዳለበት በጭልጋ ወረዳ  የጉንትር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ስጦታው ክብረት ተናግረዋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ እንዳረጋገጡት በወቅቱ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸውና በመፈራረሳቸው ከ3ሺህ በላይ የሚቆተሩ የ10ኛና የ12ኛ ተማሪዎች አይፈተኑም።

በተመሳሳይ በቀጣይ ሳምንት ለሚካሄደው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናም በተመሳሳይ 3,400 ያህል ተማሪዎችም እንደማይፈተኑ ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት። በአማራ ክልል 804ሺህ ተማሪዎች የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኞች ናቸው። የ10ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ረቡዕ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ /ነጋሳ ደሳለኝ / ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ