1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖሊስ እና የናትናኤል ጉዳይ

ሐሙስ፣ መስከረም 26 2009

እነ ናትናኤል የተያዙት ከትናንት በስተያ አዲስ አበባ ስታድዮም አካባቢ በሚገኘው ላሊበላ ሬስቶራንት ውስጥ ባለፈው እሁድ ቢሾፍቱ ስለደረሰው የሰዎች ሞት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተወያይታችኋል በሚል መሆኑን አቶ አምሀ ከናትናኤልን እና ከጓደኞቹ እንደሰሙ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/2Qz1k
Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien
ምስል Solomon Mengist

Blogger Natnael & Police's appeal - MP3-Stereo

ዛሬ ያስቻለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ፣ ከትናንት በስተያ የተያዙት  የዞን ዘጠኝ ዓምደ መረብ ዘጋቢ ናትናኤል ፈለቀ እና ሁለት ጓደኞቹ በዋስ እንዲለቀቁ ዛሬ ጠዋት ወስኖ ነበር ። ሆኖም በውሳኔው ላይ ቅሬታ አለኝ ያለው ፖሊስ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተከሳሾቹ እንዳይለቀቁብኝ ሲል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል ። የናትናኤል ጠበቃ አቶ አመሀ መኮንን ዛሬ ማምሻውን እንደተናገሩት እነ ናትናኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት እርሳቸው በሌሉበት ነበር ። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ  በዋስ እንዲለቀቁ ቢወሰንም ፣ 3ቱም ዛሬም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን  የናትናኤል ጠበቃ ዛሬ ጠዋት ለዶቼቬለ ተናግረው ነበር  ። ዛሬ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው የዞን ዘጠኝ ዓምደ መረብ ዘጋቢ ናትናኤል ፈለቀ ፣ እንዲሁም ጓደኞቹ ፀደቀ ድጋፌ እና አዲስ ዓለም ሙሉጌታ ናቸው ። ውሳኔው ከተሰጠ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን ፓሊስ ቅሬታ አለኝ ብሎ ተከሳሾቹን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ ብሏል ። ዛሬ የሆነውን የናትናኤል ጠበቃ አቶ አምሀ መኮንን ለዶቼቬለ ገልጸዋል ።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቄራ ምድብ  የሦስቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ትናንት ነበር የቀረበለት ።ሆኖም ፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት ካሳደረው በኋላ ዛሬ ትዕዛዙን መስጠቱን አቶ አምሀ መኮንን ለዶቼቬለ አስረድተዋል ።አቶ አምሀ  ዛሬ ጠዋት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ይግባኝ ቢቀርብበትም ተፈጻሚ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው ።እነ ናትናኤል የተያዙት ከትናንት በስተያ አዲስ አበባ ስታድዮም አካባቢ በሚገኘው ላሊበላ ሬስቶራንት ውስጥ ባለፈው እሁድ ቢሾፍቱ  ስለደረሰው የሰዎች ሞት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተወያይታችኋል በሚል መሆኑን  አቶ አምሀ ከናትናኤልን እና ከጓደኞቹ እንደሰሙ ተናግረዋል ። «ይህ ወንጀል አይደለም » ሲሉም  የተከሳሾቹ ጉዳይ  ለታየበት ፍርድ ቤት ዛሬ ጠዋት በተገኙበት ፍርድ ቤት መከራከሪያ አቅርበዋል ። ሆኖም ዛሬ እነ ናትናኤል የተከሰሱበት ምክንያት ተብሎ የተነገራቸው ሌላ ነው ።ሆኖም ጠበቃ አምሀ ደንበኛቸው ናትናኤልም ሆነ ጓደኞቹ የተያዙበት ምክንያት በቂ ነው ብለው አያምኑም ።
ነገ በዋስ ይለቀቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ፖሊስ ይግባኝ ያቀረበባቸው የዞን ዘጠኝ የዐምደ መረብ ዘጋቢ ናትናኤል ፈለቀ ፣ እና ጓደኖቹ  ካዛንቺስ 6 ተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ጠበቃ አመሀ ተናግረዋል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ