1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሲራል ራማፎዛ በቅርቡ ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሐሙስ፣ የካቲት 8 2010

የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳንት ጃክኦፍ ዙማ ከ 8 ዓመታት በኋላ ስልጣን ለቅቀዋል። የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረንስ ራሲል ራማፎዛ መንበረ ስልጣኑን እንዲረከቡ ሰይሟል። የደቡብ አፍሪካዉ መሪ ጄኮብ  ዙማ በዛሬዉ ዕለት ስልጣን የለቀቁት ሰሞኑን ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና እሳቸዉ በሊቀመንበርነት ከሚመሩት የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረንስ ፓርቲ በደረሰባቸዉ ግፊት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2slGB
Südafrika - neuer Präsident Cyril Ramaphosa – Vereidigung
ምስል Reuters/M. Hutchings

Jacob Zuma finally steps down - MP3-Stereo


ከጎርጎሮሳዊዉ ግንቦት 2009 ዓ/ም ጀምሮ ደቡብ አፍሪቃን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ጄኮብ ዙማ በሙስና እና ሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች በተደጋጋሚ ሲከሰሱ ቆይተዋል።ይህንን ተከትሎም ፓርቲያቸዉ ANC  ከስልጣን እንዲለቁ  ጥያቄ ቢቀርብላቸዉም የፈጸምኩት ወንጀል የለም በሚል እስካለፈዉ ማክሰኞ ድረስ ስልጣን ላለመልቀቅ ሲያንገራግሩ ነበር። በፓርቲያቸዉ በኩል የቀረበዉን ጥያቄም አግባብነት የሌለዉ ሲሉ  አጣጥለዉት ነበር።
ይሁን እንጅ ፓርቲያቸዉ ANC  በ48 ስዓት ዉስጥ ከአባልነት እንደሚያሰናብታቸዉ በገለፀዉ መሠረት ስልጣን መልቀቃቸዉ ታዉቋል። ዙማ ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡት በታኅሳስ 2009 ተቀናቃኛቸዉን ታቦ ኢምቤኪን በድምፅ ብልጫ አሸንፈዉ የፓርቲዉ ሊቀመንበር ሆነዉ በመመረጣቸዉ ነበር። ዙማ ከምርጫዉ አንድ ወር ቀደም ብሎም ቢሆን የሙስና ክስ ተመስርቶባቸዉ የነበረ ቢሆንም ከወራት በኋላ ግን በፖለቲካ ተጽዕኖ ክሳቸዉ መሰረዙ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ለማካካስ በሚመስል መልኩም  በግንቦት 2009 ፕሬዝዳንት ሆነዉ ሲሾሙ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጠዉ መነሳታቸዉን ተናግረው ነበር። ይባስ ብለዉም ከአንድ አመት የስልጣን  ቆይታ በኋላ ፕሬዚዳንቱ  ለጠፋዉ መልካም ስሜ 7 መቶ ሺህ ዶላር ካሳ ይገባኛል ሲሉ ጠይቀዋል። ይህ የዙማ ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ በፍትህ እንደመቀለድ ተቆጥሮ የነበረ ቢሆንም በፓርቲያቸዉ በኩል ግን የተባለ ነገር አልነበረም። በ2012  የዴሞክራሲ ጥምረት የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ በዙማ ላይ በድጋሚ የሙስና ክስ እንዲመሰርት የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መፍቀዱም ዙማን የፓርቲ ሊቀመንበር  ከመሆን አላገደም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተደጋጋሚ በሚቀርብባቸዉ ተደጋጋሚ ዉንጀላ ተቃዋሚዎቻቸዉ ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲያቸዉም ጭምር አመኔታ አጥቶባቸዉ መሰንበቱን ነዉ የፓርቲዉ አባል የሚገልጹት።
 «በየትኛዉም ሁኔታ ቢሆን የመተማመኛ ድምፅ  ተፈላጊነት የለዉም።   ለኛ እጅግ ጠቃሚዉና  አሳሳቢዉ ጉዳይ  ፣ደቡብ አፍሪቃ  የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳት የማዋረድ  ምኞት አላት ብለን አለማመናችን ነዉ። » 
የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ዙማ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲያሽቆለቁል አድርገዋል ሲሉ ይተቹዋቸዋል።እናም አዲስ ሞራፍ መጀመር አለበት ይላሉ።
«እንደማስበዉ ፤ደቡብ አፍሪቃ የዙማን የአመታት ምዕራፍ መዝጋት ያስፈልጋታል። በኢኮኖሚያችን ላይ በፖለቲካ አካላትና በምክር ቤቶቻችን ላይ ባለፉት 8 ዓመታት ያሰራዉን ሳናካትት ያለ ዙማ   አዲስ መጻኢ መጻፍ መጀመር አለብን።» 
በመጭዉ አመት የስልጣን ጊዜያቸዉን የሚያጠናቅቁት ዙማ ምክትላቸዉ ሲራል ራምፎዛ መንበረ ስልጣኑን እንዲረከቧቸዉ ያለመተማመኛ ድምፅ መመረጣቸዉ እየተነገረ ነዉ። በበሳል ፖለቲከኛነታቸዉ የሚወደሱት የANCዉ ራማፎዛ በፓርቲ አባልነት የሚቀጥሉትን ዙማን ጨምሮ የፓርቲዉን አባላት ከሙስና ማፅዳት ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሏል። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራና  የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እንዲጨምር ማድረግም እንዲሁ።
ደቡብ አፍሪቃ ከጎርጎሮሳዊዉ 1994 የአፓርታይድ ማብቃት በኋላ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ 4 ጥቁር ፕሬዝዳንቶችን አስተናግዳለች። አምስተኛዉ ፕሬዝዳንት ሲራል ራማፎዛ በቅርቡ ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Südafrika | Präsident Zuma tritt zurück ARCHIV
ምስል Reuters/M. Hutchings
Südafrika historische Bilder zu Jacob Zuma
ምስል picture-alliance/dpa/K. Ludbrook

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ