1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፓኖራማአፍሪቃ

ፊላ የደራሼ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ

ሐሙስ፣ ግንቦት 17 2015

በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የተለያዩ ብሄረሰቦች ካላቸው ባህላዊ አሴቶች መካከል ነባር የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ ከእነኝህም መካከል ፊላ በመባል የሚታወቀው የደራሼ ብሄር ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ አንዱ ነው ፡፡ ፊላ ከትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚመደብ ነው፡፡ አጨዋወቱም በጋራ ሲሆን የተለየ ህብረ ድምፃዊ ቃናን ይሰጣል፡፡

https://p.dw.com/p/4RmDl
Befekadu Habtemariam
ምስል SNNPR

«ፊላ»በአካባቢው አጠራር ቆቦ ተብሎ ከሚጠራ ዛፍ የሚሠራ ነዉ

በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የተለያዩ ብሄረሰቦች ካላቸው ባህላዊ አሴቶች መካከል ነባር የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ ከእነኝህም መካከል ፊላ በመባል የሚታወቀው የደራሼ ብሄር ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ አንዱ ነው ፡፡ ፊላ ከትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚመደብ ነው ፡፡ አጨዋወቱም አንደ አርሞኒካ ከግራ ወደ ቀኝ በከንፈር ላይ በማንቀሳቀስ ሲሆን በተለይ በቡድን ሲጫወቱት የተለየ ህብረ ድምፃዊ ቃናን ይሰጣል፡፡ ለመሆኑ የደራሼዎች የሙዚቃ መሣሪያ ፊላ ከምን ይሰራል ፡፡ በደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ጥናት ባለሙያና የደራሼ ብሄር ተወላጅ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ሀብተማሪያም እንደሚሉት ፊላ ቀደምሲል በአካባቢው አጠራር ቆቦ ተብሎ ከሚጠራ ዛፍ ይሠራ ነበር ፡፡ አሁን ላይ ግን የብሄሩ አባላት ፊላን ለመሥራት የቀርቀሃ ግንድን እንደሚጠቀሙ አቶ በፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

Befekadu Habtemariam
ፊላ የደራሼ ህዝብ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ ምስል SNNPR

የፊላ የሙዚቃ መሣሪያ የብሄሩ አባላት ለምን ተግባራት መጫወት እንደጀመሩ አባቶች በአፈ ታሪክ ሥለሚገልጹት ታሪካዊ ዳራም ጥናት መደረጉን የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ “ የደራሼ ብሄር ራቅ ባሉ ጊዜያት ፊላን ንጉሱ በጎዳና በሚጓዝበት ጊዜ ከኋላ እና ከፊት እየተጫወቱ ለማጀቢያነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ይህም ፊላውን የሚጫወቱት በቡድን በመሆንና ሥረዓት ባለው መሥመር በመደርደር ነው ፡፡ ያ ማለት አሁን ላይ ከምናየውና ማርቺንግ ባንድ ተብሎ ከሚጠራው ዘመናዊ የዝግጅቶች ማድመቂያ ሥረዓት ጋር የመመሳሰል ሁኔታ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ “ ብለዋል፡፡

የፊላ ሙዚቃ የንጉሱን ጎዞ ለማድመቅ ይጀመር እንጂ  አገልግሎቱ በጊዜ ሂደት በዚህ ብቻ ተገድቦ እንዳልቀረ የሚናገሩት የባህል ጥናት ባለሙያውና የደራሼ ብሄር ተወላጅ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ሀብተማሪያም “ አሁኑወቅት የብሄሩ አባላት ፊላን በተለያዩ ማህበራዊ ክንውኖቻቸው ላይ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ፡፡ በተለይም እንደ ሠርግ ለመሳሰሉ የደስታ ማድመቂያነትና በእርሻ ሥራ ወቅት ለድካም ማነቃቂያነት እየዋለ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የፊላ የሙዚቃ መሣሪያ ውበቱ ህብረ ድምጻዊነቱ  ብቻ አይደለም  ፡፡ ፊላ ከሙዚቃው ምት ጋር  አብሮ የሚሄድ አካላዊ እነቅስቃሴንም ያጣመረ ነው ፡፡ ይህ ደግሞ የራሱ ሥረዓት እንዳለው ነው አቶ በፍቃዱ የሚናገሩት ፡፡

Kulturorchester des Derashe-Stammes und verstorbener Ethnologe des Derasé-Volkes
ፊላ የደራሼ ህዝብ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ ምስል Privat

አቶ አብቶ አኒቶ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ናቸው ፡፡ ክልሉ አሉኝ ከሚላቸው ቁሳዊ የማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶች መካከል  የደራሼ ብሄር የሙዚቃ መሣሪያ ፊላ አንዱ መሆኑን  አቶ አብቶ ይናገራሉ ፡፡  አሁን ላይ የፊላ የሙዚቃ መሣሪያን ከአገር አቀፍ እስከ አለምአቀፍ ባሉ ሂደቶች የሚገባውን ዕውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መጀመሩንም አቶ አብቶ ገልጸዋል፡፡

ፊላ የሙዚቃ መሣሪያ አገራዊና አለም አቀፋዊ እውቅና ማግኘቱ ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ሠፊ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብቶ “ በተለይ የሙዚቃ መሣሪያው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ሀብቱን እንዳይጠፋ ያስችላል ፡፡ በተጨማሪም አገር አቀፍ እና አለምአቀፍ ዘፋኞች ፊላን ከዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር አዋህደው በመጠቀም ከአድማጮች ጋር እንዲተዋወቅ ዕድል ይፈጥርለታል  “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ