1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጽዱ የኃይል ምንጭ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16 2008

ጀርመን የዓለማችንን ከባቢ አየር በግምባር ቀደምትነት በመበከል ከሚጠቀሱት ሃገራት መካከል ባትሆንም በ2013ዓ,ም በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ወደከባቢ አየር ከተለቀቀዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን 2,40 በመቶዉን ድርሻ መያዟ ተመዝግቧል። ቀዳሚዋ ቻይና 29,10 በመቶ፤ ተከታይዋ ዩናትድ ስቴትስ ደግሞ 15,00 በመቶዉን ይይዛሉ።

https://p.dw.com/p/1Ithk
Windmühlen in Rapsfeld
ምስል DW/A. Bowen

ጽዱ የኃይል ምንጭ

ቮልስዋገን እያልን የምንጠራዉ፤ ሆኖም ፈጣሪዎቹ ጀርመኖች የሕዝብ መኪና ወይም ፎልክስቫገን የሚሉት፤ እንዲሁም ፖርሸ እና BMW መገኛ የሆነችዉ ጀርመን መጠነኛ ካርቦን ወደከባቢ አየር የሚለቁ ተሽከርካሪዎችን በብዛት በማምረትና በመጠቀም ቀዳሚ ሀገር ለመሆን ታጥቃ መነሳቷን እያመላከተች ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት የዶቼ ቬለ ራዲዮ ጣቢያ በሚገኝበት በእዚህ በቦን ከተማ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የዓለም ሃገራት መንግሥታት ባለፈዉ ኅዳር ወር ፓሪስ ላይ ተሰብስበዉ የተስማሙበት ዉል ወደተግባር የሚመነዘርበትን መንገድ ለመቀየስ የተሰባሰቡት የየሃገራቱ ተወካዮች በኤሌክትሪክ የሚሽከረከሩትን ዘመናዊ አዉቶሞቢሎች እንዲጠቀሙባቸዉ ቀርበዉላቸዉ ነበር።

ጀርመን ከነፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ሙከራዋን የጀመረችዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1976ዓ,ም እንደነበር ሰነዶቿ ያሳሉ። ያኔ የጀርመን የምርምር ሚኒስቴር 100 ሜትር ርዝመት ያለዉ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ማማ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተከለ። ሆኖም የመጀመሪያዉ ሙከራ የተተከለዉ ከነፋስ ኃይል ማመንጫዉ መዘዉር በመንኮታኮቱ ብዙም ሳይቆይ ሙከራዉ ከሸፈ። የወደቀዉ ግን ወድቆ አልቀረም ዳግም ከ11 ዓመታት በኋላ እዚያዉ ሰሜን ጀርመን በሽሌስቪግ ሆልሽታይን ግዛት ከነፋስ ኤሌክትሪክ የሚያመነጨዉ የተጠናከረ ሥራ እዉን ሆነ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ከሰሜን ባህር ላይ የሚነፍሰዉን ንፋስ ወደኤሌክትሪክ ኃይል የሚለዉጡ 32 የንፋስ መዘዉሮች ተተክለዉበት ሥራዉን ቀጠለ። ከዚህም ደረጃ በደረጃ በየዓመቱ ሕጎችና መመሪያዎች እየወጡለት ከነፋስ፤ እንዲሁም ከፀሐይ፤ ባጠቃላይ ከጽዱ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮች የኤክትሪክ ኃይል የማመንጨቱ ተግባር እና ምርምሩ ተስፋፍቶ ቀጠለ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም በጃፓን ፉኩሺማ ርዕደ መሬት ያስከትለዉ ሱናሚና መዘዙ ትምህርት የሆነዉ የፌደራል ጀርመን መንግሥት ከአቶም የሚገኝ ኃይል መጠቀምን ደረጃ በደረጃ እየቀነሰ መጥቶ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2022 ከዚህ የሚላቀቅበትን እቅድም ነደፈ። በዚህ አካሄዱም የኃይል ምንጮቹ ሁሉ በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ መዘዝ የማያስከትሉ እንዲሆኑ ነዉ ፍላጎቱ።

Tesla Modell 3
ምስል AP

ጀርመን የኃይል ምንጮችን በመጠቀም በኩል በምታካሂደዉ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ዘርፍ የምታመነጨዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የኤልክትሪክ ኃይል 28 በመቶዉን ይሸፍናል። በቀጣይ አራት ዓመታት እስከ 35 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይሉን እንዲሸፍን የታቀደዉ የታዳሽ የኃይል ምንጭ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2050ዓ,ም ሀገሪቱ የምትጠቀመዉን የኤሌክትሪክ ኃይል 80 በመቶ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች በተገኘ ኤሌክትሪክ ለመሸፈን አልማ እየሠራች መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። የታዳሽ የኃይል ምንጮች መስፋፋትም ከቅሪተ አጽም በሚገኘዉ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ጽዱ የኃይል ምንጭ እንዲጠቀሙ እንደሚረዳ ነዉ የሚገለጸዉ። ይህን መሠረት ያደረጉት የጀርመን የአዉቶሞቢል ፋብሪካዎች አሁን ፊታቸዉን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን በብዛት ለገበያዉ ወደማቅረቡ አዙረዋል። የጀርመን መንግሥት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገዉ ይህን ዘርፍ ለማበረታት ጠቀም ያለ ገንዘብ መድቧል። የጀርመን የመጓጓዣ ዘርፍ ሚኒስትር ኖርበርት ባርተል፣

«ልማትን ለማጠናከር አዎንታዊ አቀራረብ ያላቸዉን በተናጠል ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን እንደግፋለን። አብዛኛዉ በምርምር ደረጃ ላይ ነዉ የሚገኙት። ባለፈዉ ዓመት በ2015ም እንዲሁ ለምርምር እና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለማምረት ከ2,7 ቢሊየን በላይ ዩሮ መድበናል።»

Solarpark in China
ምስል picture-alliance/dpa

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም ቀደም ሲል BMW ያወጣዉ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አዉቶሞቢል አንድ ጊዜ በተሞላዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ከተማ ዉስጥ ከሆነ 175 ኪሎ ሜትር፤ ከከተማ ዉጭ ባለዉ የፍጥነት መጓዣ አዉራ ጎዳና ላይ ከሆነ ደግሞ 154 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ ይችላል። እስካሁን በሀገሪቱ በዓመት ለገበያ የሚቀርበዉ ከ2,000 ያልበለጡ በኤሌክትሪክ የሚነዱ መኪናዎች ነበሩ። እስከመጪዉ አራት ዓመታት ድረስ ይህን እስከ 1 ሚሊየን ለማድረስ የታሰበ ሲሆን እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2030ዓ,ም ድረስም 5 ሚሊየን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ አዉቶሞቢሎች የጀርመንን ጎዳናዎች ይሞላሉ ተብሎ ታስቧል። እንደዉም ይላሉ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ምርምር እንዲካሄድ ገንዘብ ከሚመድቡት አካላት አንዱ የሆነዉ የአዉሮጳ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ባልደረባ ክርስቲያን ፍሪስ ባህ፤ በቀጣይ አስርት ዓመታት ዉስጥ በመጓጓዣና ተሽከርካሪዎች ረገድ ከፍተኛ አብዮት ይታያል።

«በመጓጓዣ ዘርፋችን በቀጣይ አስርት ዓመታት ዉስጥ አንድ አብዮት ወይም ለዉጥ እናያለን። የመረጃ እና የመጓጓዣዉ ቴክኒዎሎጂ በጋራ ዛሬ ላይ ሆነን ልንገምተዉ የምንችለዉ በላይ አሁን ካለዉ የመጓጓዣ ሥልት ፍጹም የተለየ አገልግሎት ወደሚሰጡ ዘዴዎች ይሸጋገራሉ።»

Deutschland Autoindustrie IAA Volkswagen VW E-up Bildgalerie 2
ምስል picture alliance/ZUMA Press/Tesla Motors

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1990ዓ,ም ወዲህ እንኳን ጀርመን ወደከባቢ አየር የምትለቀዉን ሙቀት አማቂ በካይ ጋዝ በ21 በመቶ መቀነሷን ነዉ። ያም ሆኖ ተሽከርካሪዎች ወደከባቢ አየር የሚለቁት ሙቀት አማቂ ጋዝ ከጎርጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም አንስቶ በአንድ በመቶ ጨምሮ መገኘቱ ተመዝግቧል። እርጥ ነዉ ጀርመን በሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ የሚሽከረከሩ አዉቶሞቢሎች ወደከባቢ አየር የሚለቁትን የብክለት መጠን በተሽከርካሪዎች ዓመታዊ ቴክኒካዊ ምርመራ ወቅት በመፈተሽ የአረንዴ መለያ እያደረገች መፍቀድና ማገድ የጀመረችዉ ቀደም ብላ ነዉ። ጭስ እያንቧለቀ የሚሽከረከር፤ አለያም ዘይትና ግሪስ ያፈሰሰ የሚንኳኳ መኪና የመርማሪዎቹን ፍተሻ ሊያልፍ አይደለም፤ ባለቤቱ ራሱም ቢሆን ድምጽ ሳያሰሙ በሚፈሱት መኪኖች ተርታ ያን ይዞ የመጓዝ ድርፍረቱም አይኖረዉም። እንዲህ ባለዉ የተሽከርካሪዎች ፍተሻ ከጀርመን ጎዳናዎች የሚታገዱ አዉቶሞቢሎች ደግሞ ቀጣይ መድረሻቸዉ ሦስተኛዉ የሚባለዉ ዓለም ይሆናል። አፍሪቃ።

ጀርመኖች እንዲህ የደከመዉን ተሽከርካሪ ከጎዳናቸዉ ላይ በማባረር ብቻ አይደለም የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ የሚታገሉት፤ በሚሽከረከሩት መኪናዎች ብዛት ጎዳናዎችና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች እንዳይጣበቡም ብስክሌት የሚያዘወትሩትን «የአካባቢ ጥበቃ ጀግኖች» እያሉ በማበረታታት የተለየ የማቆሚያ ሥፍራ ይሰጧቸዋል። እንደሰዉ በይፋ ጀግና መባል የሚጠላ የለም እና ሴቷም ከነ አጭር ቀሚሷ ወንዱም ከነሙሉ ሱፍ ልብሱ ብስክሌት ማሽከርከር ስለአካባቢ ተፈጥሮ የተሻለ እዉቀት ያለዉ መለያም እየሆነ ነዉ። ይህም ለእያንዳንዱ ነገር የሌሎችን ጥረት ብቻ ከመመልከት የየግል አስተዋፅኦ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነ ማሳያ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ