1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ጥያቄ የበረከተበት የኦሮሚያ 'የኤኮኖሚ አብዮት'

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2009

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ልተገብረው ነው ባለው የ'ኤኮኖሚ አብዮት' አምስት ኩባንያዎች ሊያቋቁም አቅዷል። የክልሉ መንግሥት በወጣቶች፤አርሶ አደሮች እና ባለሐብቶች የሚቋቋሙት ኩባንያዎች ሥራ አጥነትን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሔ ይሆኑኛል ይበል እንጂ በርካታ ጥያቄዎች ገጥመውታል።

https://p.dw.com/p/2ZFVO
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

ጥያቄ የበረከተበት የኦሮሚያ 'የኤኮኖሚ አብዮት'

በተከከታታይ የአደባባይ ተቃውሞዎች ሲናጡ የከረሙት የኦሮሚያ ከተሞች ለጊዜው ተረጋግተዋል። በመንግሥትም ይሁን በባለሐባቶች ተቋማት ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች ጋብ ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለወራት የዘለቀውን ፖለቲካዊ ተቃውሞ ለማብረድ ገቢራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገባደድ የቀሩት ቀናት ጥቂት ቢሆኑም መጪው ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅም። 
የከረረ ተቃውሞ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከመጠነ-ሰፊ ግምገማዎች በኋላ የኤኮኖሚ አብዮት ያቀጣጥሉልኛል ያላቸውን እቅዶች ይፋ አድርጓል። የአገር ውስጥ መዋዕለ-ንዋይን ያበረታታል የተባለለት ይህ እቅድ ወጣቶች እና ገበሬዎችን ለመጥቀም ማቀዱም ተነግሯል። ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት፤ ኬኛ የመጠጥ ማቀነባበሪያ፤አምቦ ፕመር ማምረቻ፤ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ እና የኦሮሚያ የግንባታ ኩባንያዎች እንደሚቋቋሙ የክልሉ መንግሥት ገልጧል።የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በግል የፌስ ቡክ ገፃቸው እንዳሰፈሩት ይቋቋማሉ ከተባሉት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኬኛ የመጠጥ ማቀነባበሪያ ከገብስ አምራች ገበሬዎች ጋር በጥምረት ይሰራል።  ከአልኮል ነፃ መጠጦች፤ የማዕድን ውሐ፤ ለስላሳ መጠጦች ጭማቂዎች እንዲያመርት የታሰበው ይኸው ኩባንያ «310 ሺህ የሚሆኑ የኦሮሞ ወጣቶች፣ 400ሺህ የሚሆኑ የኦሮሞ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች» ባለ ድርሻ ሆነው ሊመሰረት መታቀዱንም አቶ አዲሱ ገልጠዋል። ኩባንያው ለመመሥረት የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራውን ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል። አቶ ታከለ ኡማ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ናቸው። 
ወደ 400 ሺህ በሚጠጉ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች ባለድርሻዎች የሚቋቋመው ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በኤኮኖሚ አብዮቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከታቀዱት መካከል አንዱ ነው። 310 ሺህ ወጣቶች እና 400 ሺህ የኦሮሞ ገበሬዎች እና ባለሐብቶች የሚያቋቁሙት ኬኛ የመጠጥ ማቀነባበሪያ ምሥረታም መንገድ ላይ ነው ተብሏል።  
'የኤኮኖሚ አብዮቱ' በአጠቃላይ የሚፈጀው የገንዘብ መጠን፤የሚፈጥረው የሥራ እድል ብዛት እና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግበት ጊዜ አይታወቅም። 
 
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎችም ይሁኑ እቅዶቹ ትችት እና ሙገሳ አላጣውም። የክልሉ መንግሥት በግል ባለሐብቶች ይዞታ ሥር የነበሩ የማዕድን ቦታዎች ወደ ወጣቶች ለማስተላለፍ ወስኗል። የክልሉ የመንግስት ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ «በምስራቅ ሸዋ ዞን 1500 ሄክታር የማዕድን ማዉጫ ቦታዎችን ከባለሃብቶች በማስመለስ 6 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች» መከፋፈሉን ገልጠዋል። ደርባ ሜድሮክ እና ዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ለማምረቻዎቻቸው የሚፈልጓቸውን ግብዓቶች ከተረደራጁ ወጣቶች ለመግዛት ሥምምነት መፈረማቸውንም አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገፃቸው አስፍረዋል። እነዚህ እርምጃዎች በሥራ ፈላጊ ወጣቶች ዘንድ መልካም እርምጃ ተደርገው ተወስደዋል።
መቀመጫቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረጉ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ግን 'የኤኮኖሚ አብዮቱ' ማዘናጊያ ነው ሲሉ ይተቻሉ። ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ቃሉን ለመጠበቁ ጥርጣሬ ያላቸውም አልጠፉም። ከሁሉም በላይ ግን በአደባባይ ተቃውሞ የተነሱ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው ሲሉ የሚሞግቱ አሉ። 
የኦሮምያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ታከለ ኡማ ግን ከተቺዎቻቸው የተለየ አቋም አላቸው። የፖለቲካ ጥያቄዎች በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ተመልሰዋል የሚሉት አቶ ታከለ ትችቶቹም ይሁን የፖለቲካ ጥያቄዎቹ ሕገ-መንግስቱን ካለ መረዳት ይመነጫሉ የሚል እምነት አላቸው።

Äthiopien Proteste | Brennende Reifen in Sabata
ምስል DW/M. Yonas Bula
Äthiopien Oromo Tracht
ምስል Getty Images/AFP/A. Maasho


እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ