1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ደም ለገሱ

ሰኞ፣ ሰኔ 18 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ዛሬ ለብሔራዊ የደም ባንክ የደም ልገሳ አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደም ሲለግሱ የሚያሳውን  ፎቶአቸውን አስደግፈው የጽህፈት ቤታቸው ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/30GXx
Äthiopien | Blutspende in Addis Abeba
ምስል Yohannes G/Egziabhare

ዶክተር ዐብይ ደም የለገሱት «በመስቀል አደባባይ ለደረሰው የፈሪዎች ጥቃት ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ድጋፋቸውን ለማሳየት መሆኑን » አቶ ፍጹም አስታውቀዋል። ከአደጋው በኋላ በአዲስ አበባ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጀመሩት የደም ልገሳ ዛሬም ቀጥሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ ላይ የሚካሄደውን ምርመራ ለማገዝ ከውጭ የመጡ መርማሪዎች ሥራ መጀመራቸው ተነገረ። የውጭ መርማሪዎቹ ዛሬ በአደጋው ስፍራ ተገኝተው ሥራቸውን ሲያካሂዱ ታይተዋል። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር በፌደራል ፖሊስ የታጀቡ የውጭ መርማሪዎች በመስቀል አደባባይ ምርመራ በማካሄድ ላይ ሳሉ መመልከቱን ነግሮናል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤ ኤፍ ፒ ፎቶ ጋዜጠኛ ዛሬ አደጋው በደረሰበት ስፍራ አቅራቢያ ኢትዮጵያውያን የማይመስሉ 4 ሰዎች ማየቱን እና አጠገባቸውም የአሜሪካን ኤምባሲ መኪና ቆሞ እንደነበር መናገሩ ተጠቅሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ኮሚሽን ምክትል ኮሚነሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተዘግቧል። ተጠርጣሪዎቹ ዶክተር አብይ አሕመድን በመደገፍ ቅዳሜ ሰኔ 16 በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ከፈነዳው ቦምብ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸው ተገልጿል። ምክትል ኮሚሽነሩን ጨምሮ 9 የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮች እና አባላት በቁጥጥር ስር ይገኛሉ። በአደጋው ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 30 መድረሱ ትናንት ተዘግቧል። የኢትዮጵያ የፀጥታ ባለሥልጣናት እስካሁን በአደጋው ማን ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ሂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ