1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተሳኩት ቃል-ኪዳኖች

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19 2009

የኢትዮጵያ መንግስትን በቅርብ የሚያውቁ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋብ ያለው ተቃውሞና የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እየገለጡ ነው። የዓለም አቀፉ የሰላም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሌክስ ደ ዋል ብዙ ስኬቶች ተጎናፅፏል የሚሉት ገዢው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በመመስረቱ ረገድ አልተሳካለትም ሲሉ ይወቅሳሉ።

https://p.dw.com/p/2Rt3K
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

ያልተሳኩት ቃል-ኪዳኖችና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

የምሥራቅ አፍሪቃን ፖለቲካ አብጠርጥረው ከፈተሹ ምሁራን መካከል ብሪታኒያዊው አሌክስ ደ ዋል አንዱ ናቸው። ፕሮፌሰሩ ከደፈጣ ውጊያ ጀምሮ የሚያውቋቸውን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር «ጓድ መለስ» ብለው የሚጠሩ የቅርብ ሰው ነበሩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በተሰማ ማግስት በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ባስነበቡት መጣጥፍ መለስ የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን በተቆጣጠሩባቸው ዓመታት «ምሁራዊ ብቃት መገለጫቸው» ነበር ሲሉ ፅፈዋል። በዚያው መጣጥፋቸው ላይ መለስ ሥልጣን ሲይዙ ከነበረችው የተሻለች ኢትዮጵያ ጥለው አልፈዋል ይበሉ እንጂ ስኬቶቻቸው ተሰባሪ መሆናቸውን አልሸሸጉም።

ኢሕዴግ ከ25 አመታት በፊት የአራት ኪሎውን መንበረ-ሥልጣን ሲቆጣጠር ሶስት አበይት አላማዎችን ለማሳካት ቃል-ገብቶ እንደነበር ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ያስታውሳሉ። ሶስቱ ዓላማዎች ድኅነትን ማጥፋትና አገሪቱን ማሳደግ፤ የማንነት ጥያቄን መመለስ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግስት መመስረት ነበሩ።በትረ-ሥልጣኑን ከሩብ ምዕተ-ዓመት በላይ የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ቃል ከገባቸው ሁለቱን ከእነ ውስንነታቸው አሳክቷል የሚሉት ደ ዋል ሶስተኛው ዛሬ አገሪቱ ለገባችበት አጣብቂኝ መነሾ እንደሆነ ይናገራሉ።

Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

«ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግስት ‘ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቃል ፤ በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ይከበራሉ’ ሲል ቃል ገብቶ ነበር። ይህ አልተከበረም። ልማታዊው መንግስት ዴሞክራሲን ለማዘግየት ሞክሯል። አገሪቱ የበለጠ እስክታድግ ኢትዮጵያውያን መ’ጠበቅ አለባቸው ሲል ነበር። እውነቱን ለመናገር አሁን መብቶቻችንን ተግባራዊ ማድረግ አለብን፤መጠበቅ የለብንም ካሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። መንግስት አሁን አንድ ቦታ የተከማቸ ስልጣን ባለቤትና ጨቋኝ እየሆነ የመጣ አምባገነናዊ  ሥርዓት ሆኗል። አሁን የገጠመው ትልቁ ፈተና ባለፉት አመታት የተገኙ ስኬቶችን መጠበቅ እና እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን ጉድለቶች ማከም ወደሚችል ወደ ተሻለ አካታች ሥርዓት የሚያደርገው ሽግግር ነው።»

ከሶስቱ ሌላ ያኔ ብዙም ያልተወራለት ነገር ግን ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል «ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ አሳክታዋለች» የሚሉት የተረጋጋ ውስጣዊ ሰላም አራተኛው ቃል-ኪዳን ነበር

«ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት በአስደናቂ ውስጣዊ ሰላም ቆይታለች። እነዚህ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የመጀመሪያው የውስጣዊ ሰላም ፈተናን ይወክላሉ።» የሚሉት ደ ዋል «እኔ እንደሚመስለኝ በተለይ ለመንግስት ዋንኛው ፈተና የተቃውሞውን መጠን መቆጣጠር እና ምላሹን ነፍጥ አልባ ማድረጉ ነው።» ሲሉ አክለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን ለወራት በዘለቀው ተቃውሞ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ግድያን ጨምሮ ኃይል የታከለበት ነው ሲሉ ይወነጅላሉ። ለሕዝባዊ መነሳሳት የሚሰጠው ምላሽ ገደብ ያለፈ ነው ሲሉም ይተቹታል። ተሟጋቾቹ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሱ አመፆች መሪ አልባ እና የሕዝብ ናቸው ሲሉ ይደመጣል። እንዲያ ሲባል ግን  በማሕበራዊ ድረ-ገፆች በተቃውሞው ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦች አልነበሩም ማለት አይደለም።

ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማሕበራዊ ድረ-ገጾች በኩል ድንበር የተሻገሩ ማስረጃዎች ይፋ በማድረጉም ረገድ በቡድን አሊያም በግላቸው የሚንቀሳቀሱ አራማጆች የጎላ ሚና ነበራቸው። እነዚህ ማስረጃዎች ግድያዎችን የሚያጋልጡ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለአደባባይ ያበቁ፤ የሟች እና ቁስለኛ ዜጎችን ማንነት በተደራጀ መልኩ የሰነዱ ናቸው።

በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አራማጆች እርስ በርስ የሚጣረሱ የመንግስት ዘገባዎችን፤የአፈፃጸም እንከኖች እና የፖሊሲ ግድፈቶች እየነቀሱ ሲያወጡም ታይተዋል። ባለፉት አመታት የተስተዋለው ሕዝባዊ ተቃውሞ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን አራማጆች ከፍ ያለ ሚና መጫወታቸውን የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ ያስረዳሉ።

Grioßbritanien London Äthiopier in England protestieren gegen Regierung
ምስል DW/H. Demisse

ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ቀስ በቀስ እየጋመ አስኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስ ያጓዘውን ተቃውሞ መቆጣጠርም ይሁን ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተስኖት ተስተውሏል። የጸጥታ ኃይሎች ለተቃውሞው በሰጡት ምላሽ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ500 መብለጡን መንግስት ራሱ አምኗል። እንደ ተቃዋሚዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከሆነ ግን ቁጥሩ ከዚያም ይልቃል። ከኦሮሚያ እስከ አማራ ክልል በሰፋው ተቃውሞ ኢትዮጵያውያን ነባር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ጎን ብለው ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል። መደበኛ ሥራቸውን አቋርጠው ከቤት ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ሰፊ ግዛት በሚሸፍኑት ሁለትክልሎች  ለተቀሰቀሱበት ተቃውሞዎች በውጭ አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤አራማጆች እና መገናኛ ብዙኃን ተጠያቂ ያደርጋል። አቶ ቻላቸው ታደሰ ግን የኢትዮጵያ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የተጠራቀመ ምሬት ገንፍሎ በመውጣቱ እንደሆነ ይሞግታሉ። በእሳቸው ትንታኔ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆን በወቅታዊው የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ያላቸው ሚና የተገደበ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ አገራት ከሚገኙ ፖለቲከኞች እና አራማጆች ባሻገር ጎረቤት ኤርትራ እና ግብፅ በወቅታዊው አለመረጋጋት ውስጥ እጃቸው አለበት ሲል ይከሳል። ደ ዋል መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ ፖለቲከኞች የተሳሳተ ፖለቲካዊ ሥሌት እያሰሉ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

«በአገር ውስጥ እየሆነ ያለው ከውጭው ጋር ምን እንደሚያገናኘው በግልፅ መናገር ይቸግረኛል። በእርግጥ እንደ ኤርትራ እና ግብፅ ያሉ የውጭ አገራት በመንግስቱ መፈራረስ ደስተኛ ይሆናሉ። በዲያስፖራው ዘንድ ለ25 ዓመታት ይህ ሥሌትና ይህ መንግስት አይሰራም፤ዘላቂ አይደሉም እያሉ ይተነብዩ ነበር። የእኛ ጊዜ ደርሷል ሲሉም ተደምጠዋል። በውጭ አገራት ለሚገኙትና ስለአገራቸው ለሚያስቡ ዜጎች ዋናው ጉዳይ ለአገሪቱ ስኬት እውቅና መስጠትና መለወጥ ያለበትን መለየት ይመስለኛል። የተመለከትንው ግን ሁሉንም የመተቸት አባዜ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚያሳዝነኝ ውድመት እና መከራና የሚረኩትን ስመለከት ነው። ለመንግስትም ይሁን በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ለመስራት ለሚሞክሩ ተቃዋሚዎች ተገቢውን ዋጋ አይሰጡም። በአንድ በኩል መንግስት ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሯል በሌላ ወገን ደግሞ መንግስቱን በኹከት እና አውዳሚ በሆነ መንገድ ለመጣል የሚሞክሩ አሉ።  ለመላው ኢትዮጵያውያንን ፈተናው ያንን አማካኝ ቦታ ማግኘቱ ይመስለኛል።»

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግም ይሁን የሚወስዳቸው እርምጃዎች ፖለቲካዊውን ቀውስ በዘላቂነት መፍታት አይችልም የሚል እምነት አላቸው። አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ካደረገች በኋላ ጋብ ያለው ተቃውሞ አንድ ቀን መቀስቀሱ እንደማይቀርም እምነታቸው ነው።

ፕሮፌሰር ደ ዋል እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግሥት ለመመሥረት ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።

«አንደኛው በዓረብ አብዮት እንደተመለከትንው ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሶ ሥርዓቱን መገርሰስ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህ ውጤቱ መልካም አይደለም። ሁለተኛው ገዢው ፓርቲ የመውጫ ቀዳዳውን መመልከት፤ የአገርን ሕዝባዊ ጥቅም ማስቀደም ነው።  የሥልጣን ቁጥጥራቸውን በማላላት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት-ግንባታው አካል መሆን አለባቸው። ይህ ለኢትዮጵያ የተሻለው አማራጭ ነው። ይህ ደግሞ ከኢሕአዴግ ብልሐት እና የአመራር ጥበብ፤ ከሕዝብ ደግሞ ኢሕአዴግ በርካታ ጠቃሚ ነገሮች ማሳካቱን እውቅና መስጠት ይጠይቃል። የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት ኢህአዴግ በርካታ ሥልጣን ለማካፈል ፈቃደኛ መሆን አለበት።»

አቶ ቻላቸው ታደሰ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዢውን መገዳደር ስለመቻላቸው ጥርጣሬ አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ