1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አፈና

ረቡዕ፣ የካቲት 16 2008

ለዩጋንዳ እንጂ ለሌሎች የአፍሪቃ ሐገራት ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ቀርቶ-የሥልክ መስመሮችን ጭምር መዝጋት አዲስ አይደለም።ዘንድሮ ምርጫ የሚያደርጉ እንደ ቻድ፤ ዛምቢያ፤ጋና እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባሉ ሐገራት ተመሳሳይ እርምጃ እና ዉዝግብ መሰማቱ አይቀርም።

https://p.dw.com/p/1I0WJ
ምስል Getty Images/AFP/D. Hayduk

[No title]

የዩጋንዳ ሕዝብ የወደፊት መሪዎቹን ለመምረጥ ባለፈዉ ሐሙስ ሲዘጋጅ የሐገሪቱ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት ተቋረጠ።ዋትስአፕ፤ ቲዊተር፤ ፌስ ቡክ እና የመሳሰሉት የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት በዚያ የምርጫ ዕለት መቋረጣቸዉ «አጋጣሚ» የሚባል እንዳልሆነ ለማወቅ አብዛኞቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ጊዜ አልወሰደባቸዉም።መንግሥት ነዉ የዘጋዉ።ተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ማሠር፤ ማወክና ማዋከብ ለዩጋንዳ አዲስ አይደለም።ሐሙስ የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት ታከለበት።ክርስቲነ ሐርየስ የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ጋዜጠኛ እና የዓምደ መረብ ፀሐፊቷ (ብሎገር) ሊንድሴይ ኩኩንዳ የኢንተርኔት መስመሯ መቋረጡን መስመሩን ላኮናተራት ኩባንያ ታሳዉቃለች።የቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣናት የሰጧትን መልስ «የማይታመን» ትለዋለች።
«መጀመሪያ ላይ ዩጋንዳ ይሕን ያክል ማበዷን ማመን አልቻልኩም ነበር።አይን ያወጣ ሕገ-ወጥ ምግባር -ይፈፅማሉ ብዬ አላመንኩም።»ሆነ።ጋዜጠኛዋ «እብደት» ያለችዉን እርምጃ የዩጋንዳ የሠላሳ ዓመት ገዢ (ከእንግዲሕም ገዢ ናቸዉ) ዩዌሩ ሙሴቬኒ የዚያኑ ዕለት ማምሻ አረጋገጡ።የማሕበራዊ መገናኛ ዜዴዎቹ የተዘጉት «ግጭትን ለመከላከል» እና አጠቃላይ የምርጫዉ ዉጤት ሳይገለጥ የሚለቀቁ ሕገ-ወጥ ዉጤቶችን ለማስቆም ነዉ ብለዉ።
Cartoon Karikatur Ugandas Präsident Yoweri Museveni 30 Jahre an der Macht
ምስል Said Michael
የኮንራድ አደናወር መታሠቢያ (KAS በጀርመንኛ ምሕፃሩ) የተሠኘዉ የጀርመን ጥናት ተቋም አጥኚ ማቲያስ ካምፕ እንደሚሉት የዩጋንዳ መንግስት የአምደ-መረብ አገልግሎትን የዘጋዉ በሁለት ምክንያት ነዉ።የመረጃ ፍሰትና ነፃነን ለመገደብም እና ሙሴቬኒ እንዳሉት።
«የሁለቱም ቅይጥ ነዉ።ባንድ ወገን በመንግሥት በኩል ደሕንነትና ፀጥታን ለማስከበር ያለመ ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል እኩል መታየት ያለበት ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት መንግሥትን የሚተቹ የሲቢል ማሕበረሰብና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች በነፃነት የሚያደርጉትን ግንኙነት ማፈን ነዉ።»
ሙሳቬኔ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ለማራዘም የቀየሱት አጠቃላይ ሥልት በርግጥ ተሳክቶላቸዋል።ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ማፈኑ ግን ብዙም አልሰራላቸዉም። የዩጋንዳ ቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት የኢንተርኔት መሥመሩን መዝጋቱ-እንደታወቀ የዚያኑ ሐሙስ 1.5 ሚሊዮን ዩጋንዳዉያን VPN የተባለዉን መስመር በመጠቀም መረጃዎችን በማሕበራዊ መገኛ ዘዴዎች ያንዥቀዥቁት ነበር።VPN የዉጪ ሐገርን የኢንተርኔት መስመር መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ የዩጋንዳ የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኒሻኖች እጃቸዉን አጣጥፈዉ ከመመልከት ባለፍ -የሚያደርጉት የለም።
እገዳዉ ሌላም ዉጤት አለዉ።ከእገዳዉ በፊት ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙም ደንታ የሌላቸዉ ዩጋንዳዉያን፤ ኩኩንዳ እንደምትለዉ፤ የገዳዉን ዜና ከሰሙ በኋላ ከነፌስቡክ ጋር እንዳዲስ «ፍቅረኛ ተጣብቀዋል።» የፖለቲካ ተንታኝ ማቲያስ ካምፕ እንደሚሉት ደግሞ ዩጋንዳ ዉስጥ የዴሞክራሲያዊ እና የዜጎች መብቶች በተለያዩ መስኮች ሲደፈለቁ፤ መደበኛ መገናኛ ዘዴዎች ሲታፈኑ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ማሐበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ማፈን ግን አዲስ ነዉ።
«ከመደበኛ መገናኛ ዘዴዎች ይልቅ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የማተኮር አዲስ ነገር ይታየኛል።ዩጋንዳ ዉስጥ ከብዙ የአፍሪቃ ሐገራት በተሻለ መልኩ በርካታ መደበኛ መገናኛ ዘዴዎች አሉ።ይሁንና ብዙዎቹ ብዙ እንዳይተቹ ሥለተደረጉ የሐገሪቱ መንግሥት ብዙም አይፈራቸዉም።ማንም ሰዉ፤ ማንም ሳያየዉ በፈለገበት ጊዜ የፈለገዉን መረጃ የሚለቅበት ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ግን መንግሥትን ብዙ የሚያሳስብ ነዉ።እንዲሕ አይነቱ እርምጃ መጠናከሩ አይቀርም።»
ለዩጋንዳ እንጂ ለሌሎች የአፍሪቃ ሐገራት ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ቀርቶ-የሥልክ መስመሮችን ጭምር መዝጋት አዲስ አይደለም።ዘንድሮ ምርጫ የሚያደርጉ እንደ ቻድ፤ ዛምቢያ፤ጋና እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባሉ ሐገራት ተመሳሳይ እርምጃ እና ዉዝግብ መሰማቱ አይቀርም።
Uganda Kampala mit Schnellfeuergewehr bewaffnete Polizisten Passant Wahlplakate
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis
የአረብን ሕዝባዊ አብዮት--ለበጎብም ይሁን ለመጥፎ---ያቀጣጠሉት እኒያ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ናቸዉ።ቡርኪናቤዎች የረጅም ጊዜ ገዢያቸዉን የብሌስ ኮምፓኦሬን ሥርዓት ለመገርሠስ በአደባባይ የተሠለፉት በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠራርተዉ ነበር።የዚያኑ ያሕል ከፕሬዝደት ሆስኒ ሙባረክ እስከ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ያሉ ገዢዎች የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመዝጋት የሕዝብን አመፅ ለማፈን መሞከራቸዉ አልቀረም።ይሁንና የእስካሁኑ ሙከራ-ብዙ ሥፍራዎች ከሽፏል። የከእንግዲሁስ?
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሠ