1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦዘው የፌዴሬሽኑ ውዝግብ በአውሮጳ

ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2009

ዓምና ሆላንድ ዴን ሀግ ከተማ ላይ ከተሰናዳው ዝግጅት አንስቶ ፌዴሬሽኑ በአባላቱ እሰጥ-አገባ ተወጥሮ ተይዟል። ፌዴሬሽኑ «የአሠራር መዝረክረክ ይታይበታል» ከሚሉ አስተያየቶች አንስቶ «በፖለቲካ ተጠልፏል» እስከሚሉ ቅሬታዎች ድረስ በተለያዩ መድረኮች ይደመጣሉ። ይኽን ቅሬታ ተከትሎም አንዳንድ ቡድኖች በዘንድሮው ውድድር እንደማይሳተፉ ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/2h4pH
Frankfurt ESCFE Festival Frankreich U14
ምስል DW/S. Mantegaftot Sileshi

ስፖርት፣ ሀምሌ 17፣ 2009 ዓም

15ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ከፊታችን ረቡዕ አንስቶ እስከ ቅዳሜ ድረስ ይከናወናል። ዘንድሮው ጣሊያን መዲና ሮም ከተማ ውስጥ በሚከናወነው ውድድር ከጀርመን የሚካፈሉት ሁለት ቡድኖች ብቻ ናቸው፤ የሽቱትጋርት እና የፍራንክፉርት ቡድኖች። ሌሎቹ የጀርመን ቡድኖች በውድድሩ የማይሳተፉት ለምንድን ነው? የፌዴሬሽኑን ሕዝብ ግንኑኘት እንዲሁም በውድድሩ ከማይሳተፉ በድኖች መካከል የኢትዮ ኮሎኝ የስፖርትና የባህል ማኅበር ሊቀመንበርን አነጋግረናል። 

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማሰባሰብ ላለፉት 14 ዓመታት ዘልቋል። ዘንድሮ በ15ኛ ዓመቱ ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በአባላቱ ዘንድ የተነሳው ቅራኔ ጡዘቱ ላይ ደርሷል።

ዓምና ሆላንድ ዴን ሀግ ከተማ ላይ ከተሰናዳው ዝግጅት አንስቶም ፌዴሬሽኑ በአባላቱ እሰጥ-አገባ ተወጥሮ ተይዟል። ፌዴሬሽኑ የአሠራር መዝረክረክ ይታይበታል ከሚሉ አስተያየቶች አንስቶ በፖለቲካ ተጠልፏል እስከሚሉ ቅሬታዎች ድረስ በተለያዩ መድረኮች ይደመጣሉ። ይኽን ቅሬታ ተከትሎም አንዳንድ ቡድኖች በዘንድሮው ውድድር እንደማይሳተፉ ገልጠዋል።

ዘንድሮ ሮም በሚከናወነው ዝግጅት የሚሳተፉ ቡድኖች እነማን ናቸው? በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል የሕዝብ ግንኙነት ለሆኑት ለአቶ ግርማ ሣኅሌ ያቀረብኩላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ ነበር። መልሳቸው እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፦ «የሚመጡት ብዬ ከምገልጽልህ የሚቀሩትን ብገልጽልህ ይቀላል» ለዚያ ደግሞ ምክንያታቸውን ያብራራሉ። «ምክንያቱም 31 ቡድኖች ይሳተፋሉ። ከማይሳተፉት ከጀርመን ሀገር ኑረንበርግ በርሊን እና ኮሎኝ ቡድኖች ናቸው።»

Italien Rom (Bildergalerie) UGC
ምስል Rahmat Orozgani

ከጀርመን ቡድኖች መካከል ሙኒክ ባለፈው ዓመት ተሳታፊ ያልነበረ እንደሆነ በመግለጥ «ሙኒክን ባትጨምረው ይሻለኛል» ብለዋል ሕዝብ ግንኙነቱ። ቡድኖቹ ለምን ወደ ጣሊያን ሄደው ላለመሳተፍ የወሰኑበትን ምክንያት በተመለከተም «ለእኛ ግልጽ አይደለም» ሲሉ አክለዋል። ከጀርመን ቡድኖች መካከል ሽቱትጋርትና ፍራንክፈርት ወደ ሮም ሲያቀኑ ኑረንበርግ፣ በርሊን፣ ሙኒክ እና ኮሎኝ አይሳተፉም።

ላለፉት 22 ዓመታት ነዋሪነታቸውን በኮሎኝ ከተማ ያደረጉትና ከአውሮጳው የስፖርትና የባሕል ፌስቲቫል መሥራቾች አንዱ እንደሆኑ የገለጡት የኢትዮ ኮሎኝ ስፖርትና ባሕል ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አበበ በዘንድሮው ውድድር የማይሳተፉበትን ምክንያት ሲያብራሩ፦ «በዚህ ዓመት የቀረንበት ትልቁ ምክንያት ፌዴሬሽናችን በአሠራሩ ኹኔታ ስላልተደሰትንም ሳይሆን ጽድት ብሎ ወይንም [ግልጽ ኹኖ ] ስላልታየን ነው» ብለዋል። 

«ተጠልፋችኋል ይባላል ለዚህ ምን ትላላችሁ?» አቶ ግርማ ሣኅሌን ጠየቅናቸው። «ሊጠለፍ ነው የሚለውን ቃል የሚያውቀው እኮ ጠለፋውን የሚያውቅ ሰው ነው። እና እንደዚህ አይነት ገርን አናውቀውም» አሉን። አክለውም፦«15 ዓመት ስናከብር የኢትዮጵያ [ሠንደቅ ዓላማ] አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ አድርገን ነው። እስኪ ይንገሩን ምንአልባት የተለየ ባንዲራ ካዩ?» ሲሉም አከሉ። ለጠቅ አድርገውም፦ «እስኪ ይንገሩን አንድ የኢሕአዴግ ባለስልጣን መጦ መድረክ ሰጠነው ሲናገር? በምን ተነስተው ነው ዛሬ ኢሕአዴግ አለባችሁ፣ ተጠልፋችኋል የሚሉን?» ሲሉም መልሳቸውን በጥያቄ ቋጭተዋል።

ፌዴሬሽኑ በሌላ አካል ተጠልፏል ሲሉ በኢሜል መልእክታቸውን የላኩልን ግለሰቦች ለቃለ-መጠይቁ ፈቃደኛ አልሆኑም። ለኢትዮ ኑረንበርግ ቡድን የሚመለከተው አካል ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪም ምላሽ አላገኘም። የኢትዮ ኮሎኝ ቡድን ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ «ግልፅ ያልሆነ ያሉትን» አሠራር ምንነት ሲያብራሩ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል የበላይ ኾኖ ዝግጅቱ የሚከናወነው በአስተናጋጅሀገር እንደነበር በማብራራት ነው። ካለፈው ውድድር አንስቶ ግን ፌዴሬሽኑ ዝግጅቱን ሙሉ በሙሉ በራሱ ማሰናዳት እንደጀመረም አብራርተዋል። «ፌዴሬሽኑ ልክ ማዘጋጀት ሲጀመር ብዙ ጊዜ ጭራሽ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን እናያለን» ያሉት አቶ ተስፋዬ ሆላንድ የነበረውን መሰናዶ አወድሰዋል። ኾኖም ግን «ኪሳራ መጣ ሲባል እንዴት ኪሳራ ሊመጣ ይችላል?» በማለት ከረቡዕ ጀምሮ የነበረው የመግቢያ ክፍያ እና የመጸዳጃ ቤት ክፍያ ጉዳይ አንስተዋል። የመጸዳጃ ቤቱ ክፍያ ያልተለመደ አዲስ ነገር እንደነበረም ተናግረዋል።  

Ethiopian sport and culture festival in Europe 2016
ምስል DW/M. S. Siyoum

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ሕዝብ ግንኙነት አቶ ግርማ ሣኅሌ የስታዲየም መግቢያ እና የመጸዳጃ ቤት ክፍያ ጉዳዮችን አንስተው መጸዳጃ ቤቱን ለማስተዳደር ይዞ ከነበረ ድርጅት ገዝተው በ2ዩሮ ከሀምሳ የነበረውን የመጸዳጃ ቤት ክፍያ «ይኬ ህዝብ መበዝበዝ የለበትም ብለን» ቀኑን ሙሉ በሚያገለግል የአንድ ዩሮ ክፍያ መቀየራቸውን «አንድ ዩሮ ከፍለህ ቀኑን ሙሉ ትጠቀማለህ» ሲሉ ተናግረዋል። ክፍያውም አንዳንድ ለተሰበሩ ዕቃዎች እንዲሁም ለጽዳት ለመሳሰሉት ወጪ እንደተደረገ አብራርተዋል። ኢትዮ ኮሎኝ ጨምሮ ግን ሌሎች ቡድኖች ቅሬታ የሚያሰሙት ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ወጪ ተደረገባቸው ያሉት ነገሮች በግልጽ ንግግር እንዳልተደረገባቸው እና ሰነዶችን እንዳልተመለከቱ ነው።

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ሕዝብ ግንኙነት አቶ ግርማ ሣኅሌም ሆኑ  የኢትዮ ኮሎኝ ስፖርትና ባሕል ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አበበ የፌዴሬሽኑ አባላት ወደፊት በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ለ15 ዓመታት የዘለቀው ይህ ፌዴሬሽን ከማናቸውም ፖለቲካና እምነት ነፃ ሆኖ ኢትዮጵያውያን የሚሰባሰቡበት መድረክ እንዲሆን የእኛም ምኞታችን ነው

አትሌቲክስ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ ባሰራጨው የኢሜል መግለጫው በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዙሪያ ላይ ነገ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጧል። ለንድን ከተማ ውስጥ የሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊዎች ማንነት ዛሬ በከፊል እንደሚገለጥ ቀደም ሲል ተነግሮ ነበር።

የተጨዋቾች ዝውውር

የሞናኮው ተከላካይ ቤንጃሚን ሜንዲ ለማንቸስተር ሲቲ በ52 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ክፍያ በመፈጸም የዓለማችን እጅግ ውድ ገንዘብ ተከፋይ ተከላካይ መሆን ችሏል።  የ23 ዓመቱ የፈረንሳይ የግራ መስመር ተከላካይ ቤንጃሚን ሜንዲ የዝውውር ክፍለ-ጊዜው ከመዘጋቱ በፊት ዘንድሮ ለማንቸስተር ሲቲ ከፈረሙ ተጨዋቾች መካከል አምስተኛው መኾን ችሏል።  ማንቸስተር ሲቲ አምስቱ ተጨዋቾችን ለማስፈረም በጥቅሉ 200 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል።

እስካሁን ከተደረጉ የቅርብ ጊዜ የተጨዋቾች ዝውውር መካከል ከፍተኛ ክፍያ የተፈጸመው ለሉካኩ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ሉካኩን ለማስመጣት 75 ሚሊዪዮን ፓውንድ መክፈሉ ተዘግቧል። ቸልሲን የተቀላቀለው ሞራታ ሞራታ በ60 ሚሊዮን ፓውንድ ሲከተል፤ የማንቸስተር ሲቲው አዲስ ተከላካይ ሜንዲ 52 ሚሊዮን ፓውንድ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ