1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአምቦ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 2010

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አምቦን ዛሬ ጎበኙ። በአምቦ ስቴድየም ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት “ተስፋ ሰጪ እና የአብረን እንስራ” መልዕክቶች ላይ ማተኮራቸውን በስፍራው የተገኙ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2vtEt
Äthiopien Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል Oromia Government Communication Affairs Bureau

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአምቦ ጉብኝት

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ የረፋድ ውሏቸውን በአምቦ ከተማ አድርገዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በስተ-ምዕራብ 126 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ለማድመጥ ማልደው ወደ አምቦ ዩኒቨርስቲ ስቴድየም ተምመዋል፡፡ በሀገር ባህል ልብሶች ያጌጡ እና የዶ/ር አብይ ምስሎች የታተሙባቸው ካኔቴራዎችን ለብሰው ወደ ዝግጅቱ ቦታ ሲሄዱ የታዩም ነበሩ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ለማድረግ በተሸሞነሞኑ ፈረሶቻቸው ሆነው ወደ አደባባይ የወጡ በርካታ ፈረሰኞች እንደነበሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ከፈረሰኞቹ ውስጥ በአምቦ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ጭምር የመጡ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ህዝቡ በብዛት የወጣው “ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተጨማሪ የቤት ስራ ለመስጠት ነው” ብለዋል፡፡ አምቦ እና አካባቢዋ ከሶስት አመታት በላይ ጠንካራ ተቃውሞ ከታዩባቸው የኦሮሚያ ከተሞች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከተሾሙ ገና ሁለተኛ ሳምንታቸውን እንኳ ያልደፈኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከቀዳሚ የስራ ጉብኝታቸው ስፍራዎች አምቦን ያካተቱት፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ሲጓዙ እንዳደረጉት ሁሉ በአምቦ ጉዟቸውም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን አካትተዋል፡፡ ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በዛሬው ስነ-ስርዓት ተገኝተዋል፡፡    

Äthiopien Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል Oromia Government Communication Affairs Bureau

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ሆኑ አቶ ለማ “ተስፋ ሰጪ እና የአብረን እንስራ” መልዕክቶች ላይ ማተኮራቸውን በስፍራው የተገኙ ተናግረዋል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ የታደሙት የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር ኩማ ዴቢሳ ንግግሮቹን በጥሞና ከተከታተሉት አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ለማ “ዛሬ የመጣነው እንደከዚህ ቀደሙ እሳት ለማጥፋት ሳይሆን ተስፋን ለመናገር ነው” ማለታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ 

የአቶ ደመቀ ንግግር ቀድሞ ሲያሰሙት ከነበረው የተለየ እንደነበር የሚናገሩት የዩኒቨርስቲው መምህር ከታዳሚው ጥሩ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በስተመጨረሻ ንግግር ለማድረግ መድረኩን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለታዳሚው ሰላምታ ሲያቀርቡ ህዝቡ በሆታ እና በፉጨት አጅቧቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሌሎቹ ተናጋሪዎች ሁሉ “ቄሮ” በሚል ስያሜ የሚጠሩትን የኦሮሞ ወጣቶችንም አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በንግግራቸው የክልሉን ፕሬዝዳንት እና የምክትላቸውን መልዕክት አስተጋብተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወጣቶች እና በመድረክ መሪዎች ቀደም ሲል ተደጋግሞ ሲሰማ የነበረውን “አምቦ ትንሽ ብትሆንም ለእኛ ኒውዮርካችን ነች” የሚለውን አባባል በንግግራቸው ማካተታቸውን አቶ ኩማ ይናገራሉ፡፡ “ከአምቦ ጀግንነት እና ትግልን እናማራለን” ሲሉ መደመጣቸውንም አክለዋል፡፡ “አምቦ ከዚህ በኋላ የቱሪዝም፣ የባህል እና የፖለቲካ ማዕከል ትሆናለች፡፡ ካሁን በኋላ እንደበፊቱ በሌላ ነገር አትጠራም” ማለታቸውንም አንስተዋል። የዩኒቨርሰቲው መምህር ንግግሩ በአጠቃላይ ያሰደረባቸውን ስሜትም ያጋራሉ፡፡ እስከ እኩለ ቀን የዘለቀው የዛሬው የአምቦ ስነ ስርዓት በጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ስር የተካሄደ ቢሆንም ምን ዓይነት ችግር ሳይፈጠር መጠናቀቁን እድምተኞቹ ተናግረዋል፡፡ 

Äthiopien Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል Oromia Government Communication Affairs Bureau

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ  

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ