1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋናዉ ፕሬዝደንት የጀርመን ቆይታ

ሐሙስ፣ የካቲት 22 2010

የጋና ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ ጀርመንን በመጎብኘት ላይ ናቸው። የጀርመን እና የጋና መሪዎች በዋናነት የኤኮኖሚ ትብብር ላይ ያተኮረ ዉይይት ቢያካሂዱም ሕገ ወጥ ስደትንም በመዋጋቱ ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

https://p.dw.com/p/2tXJK
Berlin, Ghanas Präsident Addo Dankwa bei Kanzlerin Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/B.von Jutrczenka

በኤኮኖሚ ትብብር እና ስደትን በመዋጋት ላይ መክረዋል

 አዉሮጳን ቀስፎ የያዘዉ በረዷማዉ የአየር ሁኔታ የጋናዉን ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶን የጀርመን ጉብኝት አላደናቀፈም። ሆኖም ሊደረግ የነበረዉን ወታደራዊ አቀባበል ግን በዚሁ ምክንያት ቀርቷል። በተቃራኒዉ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የቀዘቀዘበት ጊዜ የለም። ጋና በምዕራብ አፍሪቃ የአርአያነት ገፅታ የገነባች ሀገር መሆኗን የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ገልጸዋል። ሁለቱም ፖለቲከኞች በሀገራቱ መካከል የኤኮኖሚ ትብብሩን ማስፋት እንደሚፈልጉ አመልክተዋል። ምንም እንኳን ጋና 584 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ በሚደርስ የንግድ ልዉዉጥ በአፍሪቃ የጀርመን ተፈላጊ ተጓዳኝ ብትሆንም ከሌላዉ ዓለም ጋር ሲነፃፀር ግን አነስተኛ ነው። እናም የጋናዉ ፕሬዝደንት ከእርዳታ ይልቅ ከጀርመንም ሆነ ከሌሎች ሃገራት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በንግድ እና በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ቢሆን እንደሚመርጡ ነው ያመለከቱት።

«ከጀርመንም ሆነ ከሌሎች የበለፁ ሃገራት ጋር የሚኖረን ትስስር ከእርዳታ ይልቅ በንግድ እና በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ እንዲሆን እንፈልጋለን። እርዳታ የመቀበሉ ዘመን ለአገሮቻችን ልማት ጠቃሚ አልነበረም ብለን እናስባለን። ይህም ድጋፍ የመፈለግ አስተሳሰብን ፈጥሯል፤ ይህ ደግሞ እኛን አልጠቀመንም።»

ሁለቱም ሃገራት የዉጭ የግል ባለወረቶች ትኩረት ወደ አፍሪቃ ቢሳብ ይሻሉ።  ጀርመን የቡድን 20 ፕሬዝደንት በነበረችበት ወቅት የመሠረተችዉ «ኮምፓክት አፍሪቃ» የተባለዉ የትብብር መድረክ ይህንኑ እንዲያመቻች የተቀየሰ ነው። ከፕሬዝደንት አኩፎ አዶ ጋር ከተነጋገሩ በኋላም ሜርክል የጀርመን የግል ባለወረቶች ወደጋና እንዲሄዱ ለማድረግ እያበረታቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

«የጋና የፋይናስ ሚኒስትር ኮምፓክት ስኬታማ እንዲሆን አብሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፤ በተለይም ጋና ዉስጥ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ረገድ ማለት ነው። በእኛ በኩልም የጀርመን የግል ባለሃብቶች ወደጋና በመሄድ ፕሮጀክቶቻቸዉን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመገፋፋት ላይ ነን። እስካሁን ያለው በጣም ትንሽ ነው።»

ሜርክል አክለውም በመጪዉ የመፀው ወራትም የኮምፓክት አፍሪቃ አባል ሃገራት በዚሁ ጉዳይ ይመክሩ ዘንድ በርሊን ላይ ስብሰባ እንደሚጠሩም ከወዲሁ አስታዉቀዋል።

Staatsflaggen von Ghana und Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/T. Imo

እስካሁን ግን በዚህ ረገድ ስብስቡ ያከናወነው ተጨባጭ ነገር የለም። የጀርመን የአፍሪቃ ፖሊሲ በዚህ ስብስብ ላይ ነፍስ እንዲዘራበት በአፍሪቃ የጀርመን የንግድ ማኅበረሰብ ማኅበር ሊቀመንበር ሽቴፈን ሊቢንግ አሳስበዋል። የጀርመን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አፍሪቃ ዉስጥ ለሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ከመንግሥት የተሰጠ ተጨማሪ ዋስትና የለም ሲል ይወቅሳል። ፌደራል ጀርመን መንግሥት በዚህ ላይ ቃል ቢገባም ከምርጫ ጋር በተያያዘዉ ረዥም ጊዜ በወሰዱ የዉስጥ ፖለቲካዉ ምክንያት እንስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። በጋናም በኩል ቢሆን መንግሥት ሊሠራቸዉ የሚገባ በርካታ ነገሮች አሉ። ከምንም በላይ የኃይል መቆራረጥ፤ ሙስና እና የሠራተኞች ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የዉጭ ባለሃብቶች ላይ ፍርሃት ፈጥሯል።  

ከኤኮኖሚ ጉዳዮች በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች ስደትን ለመከላከል በጋራ ለመሥራትም ተስማምተዋል። የጋናዉ መሪ ወጣቶች በስደት እና ሜዲትራኒያን ባህርን በማቋረጥ አቅማቸዉን ከሚያባክኑ የበለፀገች ሀገር በመገንባቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። ጀርመን የጥገኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ የጋና ዜጎች ወደሀገራቸዉ የሚመለሱበትን ሁኔታ እያፋጠነች ነው። ሜርክል ይህን አስመልክተዉ ባለፈዉ ታኅሳe ወር እንዲህ ነበር ያሉት፤

«በግዳጅ ከመመለሱ አስቀድሞ በፈቃደኝነት የሚመለሱትን እናበረታታለች። በተቃራኒዉ ከጋና በርካታ ወጣቶች ለትምህርትም ሆነ ለሙያዊ ሥልጠና ወደ ጀርመን እንዲመጡ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እንፈልጋለን። ሕገወጥ ስደተኝነትን መዋጋት ይኖርብናል፤ ሆኖም በአንፃሩ ለወጣቶች ሕጋዊ ዕድሎች እንዲከፈቱ እንፈልጋለን።»

ጀርመን ዉስጥ በአሁን ወቅት ወደጋና ሊመለሱ ይችላሉ የተባሉ አራት ሺህ ገደማ ተሰዳጆች ይኖራሉ። የተመላሽ ስደተኞችን ሁኔታ ለማመቻቸትም አክራ ላይ በጀርመን ትብብር አንድ ማዕከል ተከፍቷል። እንዲያም ሆኖ የጋናዉ ፕሬዝደንት ወደጋና ይመለሳሉ የተባሉት ማንነት አስቀድሞ እንዲጣራ ጠይቀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ/ ዳንኤል ፔልስ

ነጋሽ መሐመድ