1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የጋምቢያ የምክር ቤት አባላት ምርጫ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2009

ምርጫዉ ለአዲሱ ፕሬዝደንት ለአዳማ ባሮዉ ሥልጣናቸዉን ለማደላደል እንደ የሕዝብ ድጋፍ መለኪያ የሚታይ ነዉ።ፕሬዝደንቱም የድጋፋቸዉን መጠን ለማጠናከር በየአካባቢዉ እየዞሩ የፓርቲያቸዉ እጭዎች እንደሚረጡ ሲቀሰቅሱ ነዉ የሰነበቱት። የሐገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ፤ የምርጫ ዘመቻዉም ሆነ የዛሬዉ ድምፅ አሰጣጥ የገጠመዉ እንከን የለም

https://p.dw.com/p/2aoVc
Gambia Wahl | Wahlwerbung für Ex-Präsident Yahya Jammeh
ምስል DW/V. Haiges

የጋምቢያ ሕዝብ የምክር ቤት አባላቱን ዛሬ ሲመርጥ ነዉ የዋለዉ። ጋምቢያ ከ22 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በሕዋላ «ነፃ» የምክር ቤት ምርጫ ሲደረግባት ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ። በምርጫዉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ 239  ፖለቲከኞች ይወዳደራሉ። ከተወዳዳሪዎቹ መካከል 40 ያሕሉ በግል የቀረቡ ናቸዉ። አብዛኞቹ ዕጩዎች ግን የሐገሪቱን ሦስት ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወከሉ ናቸዉ። የምርጫ ዘመቻዉና ድምፅ አሰጣጡ በሠላም እየተካሔደ መሆኑን የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን አስታዉቋል። ዳንኤል ፔልስ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።
ዝርዝር
የትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር ትልቅ ከተማ ሴሬኩንዳ ግርግር-ወከባ፤ ቱማታ-ከበርቻቻ ተለይቷት አያዉቅም።ሰርገኛዉ ይጨፍርባታል።ቱጃሩ፤ ሹመኛ፤ ዝነኛዉ ያስጨፍር፤ያዘምር፤ያስፎክርባታል።የስፖርት ድል፤ የታዋቂ ሰዎች ልደት፤ የፖለቲከኞች ዲስኩር፤ መንፈሳዊ በዓላት---- ለከበርቻቸዉ ሰበቡ ብዙ ነዉ።
ሰሞኑን  ግን የእስከሰሞኑን ወከባ፤ ጫጫታ፤ ልፈፋ የዋጠ ግርግር፤ የድምፅ ማጉያ ስግምግምታ  ደምቆባታል።ምክንያት፤-
 

«በጣም ደስ ብሎኛል።አዲሶቹን የምክር ቤት እንደራሴዎቻችንን እንመርጣለን።ፕሬዝደንት ጃማሔ አምባገነን ነበሩ።አባርረናቸዋል።መጥፎ ሕጋችንን ለመለወጥ እንድንችል አዲስ የምክር ቤት አባላት መምረጥ አለብን።ሕገ-መንግሥታችንን መለወጥ አለብን።»ይላል ፓል ኬይቲ።እዚያዊ ሴሬኩንዳ ዉስጥ ትንሽ የመኪና መለዋወጫ ሱቅ አለቸዉ።በርግጥም  የጋምቢያ የፖለቲካ ድባብ ተለዉጧል።ሐገሪቱን ለ22 ዓመታት በብረት-ጡንቻ የገዙት ፕሬዝደንት ያሕያሕ ጃሜሕ ባለፈዉ ታሕሳስ በተደረገዉ ምርጫ ተሸንፈዋል።ጃሜሕ ስልጣናቸዉን ላሸናፊዉ ለአዳማ ባሮዉ አላስረክብም ብለዉ ሲያንገራግሩ ነበር።የአካባቢዉ ሐገራት ፖለቲካዊ ጫናና እና ወታደራዊ ዛቻ ጃሜሕ የሚወዷትን ሥልጣን ከቆዩባት በላይ እንዳይጠለጠሉበት በጠሱባቸዉ።ጥር። 
በዛሬዉ ምርጫ 53 መቀመጫዎች ላሉት ምክር ቤት 239 ዕጩዎች እየተፎካከሩ ነዉ።አብዛኞቹን ዕጩዎች ያቀረቡት የሐገሪቱ ሰዎስት ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸዉ።ከሰወስቱ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ፓርቲ (UDP) የተሰኘዉ ከፕሬዝደንት አዳማ ባሮዉ ጋር የሚተባበረዉ ፓርቲ ከፍተኛ ድጋፍ አለዉ ተብሎ ይታመናል። ያንኩባሕ ኪንቲም ይሕንኑ ነዉ የሚሉት።
                                    
«ድምፄን የምሰጠዉ ለUDP ነዉ።ምክንያቱም ጃሜሕን ለማስወገድ በፅናት የቆሙና የታገሉ ናቸዉ።በአደባባይ ወጥተዉ የጃሜሕን አገዛዝ «በቃ» ያሉ ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት መመረጥ የሚገባዉ ፓርቲ ነዉ።»

Gambia Wahl | Wahlbeobachter der EU
ምስል DW/V. Haiges

ይሁንና የጋምቢያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (GDC) እና APRC በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ አንጋፋዉ ፓርቲም ያላቸዉ ተቀባይነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
APRC የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የያሕያሕ ጃሜሕ ፓርቲ ነዉ። የጃሜሕ የትዉልድ ግዛት በሆነዉ በሐገሪቱ ደቡባዊ ግዛት ፎኒ የሚኖረዉ ሕዝብ አረንጓዴ ቲ ሸርት፤ ባርኔጣ፤ ሴቶቹ ሻሽም ጨምረዉበት አረንጌዳ-ባረንጓዴ ለብሶ ነዉ የሰነበተዉ። የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች፤ አዉራ ጎዳኖች፤ መኪኖች ሳይቀሩ ባረንጓዴ ምልክቶች፤ ቅስቶች እና መፈክሮች አሸብርቀዋል።አረንጓዴ የጃሜሕ ፓርቲ የAPRC አርማ ነዉ።
ጃሜሕ አምባገነን ናቸዉ።ከሥልጣን ተወግደዋል።ተሰደዋልም።አሁንም ግን በርካታ ደጋፊ አላቸዉ።ምርጫዉ ለአዲሱ ፕሬዝደንት ለአዳማ ባሮዉ ሥልጣናቸዉን ለማደላደል እንደ የሕዝብ ድጋፍ መለኪያ የሚታይ ነዉ።ፕሬዝደንቱም የድጋፋቸዉን መጠን ለማጠናከር በየአካባቢዉ እየዞሩ የፓርቲያቸዉ እጭዎች እንደሚረጡ ሲቀሰቅሱ ነዉ የሰነበቱት።ጋምቢያ ከአምበገነናዊ አገዛዝ ገና መላቀቅዋ ቢሆንም የሐገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ፤ የምርጫ ዘመቻዉም ሆነ የዛሬዉ ድምፅ አሰጣጥ የገጠመዉ እንከን የለም።የአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን ምክትል መሪ ቶማስ ቦሴረፕም ይሕንኑ አረጋግጠዋል።
                                  
«የምርጫ ዘመቻዉ እስካሁን ድረስ ሰላማዊ ነዉ።ሥርዓት የተከተለ ነዉ። የምርጫ ዘመቻዉን ዝርዝር ሒደት  የግምገማ ዉጤት የምናሳዉቀዉ ግን ከምርጫዉ በኋላ ነዉ።ለዚያ ትንሽ ጊዜ ይቀረናል።እስካሁን ግን ጥሩ ነዉ።»
ነጋሽ መሃመድ
አዜብ ታደሰ

Gambia Wahl | Wahlkampf in Serekunda
ምስል DW/V. Haiges