1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20 2008

«ዴሞክራሲያዊ ሐገራት ከሌሎቹ ይበልጥ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት አለባቸዉ። ይሕ ማለት ኢትዮጵያ ወይም አንጎላን ከመሳሰሉ አምገነናዊ ሥርዓቶች ጋር ከሚደረግ ግንኙነት ይልቅ ከደቡብ አፍሪቃ፤ኬንያ እና ጋና ጋር ይበልጥ አብሮ መስራት ያስፈልጋል።»

https://p.dw.com/p/1Iesk
ምስል Reuters/M.Kappeler

[No title]

የጀርመን ባለሥልጣናት ሐገራቸዉ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ።መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በቅርቡ የኬንያዉን ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታንና የሞዛምቢኩን ፕሬዝደንት ፊሊፕ ንዩስን ወደ በርሊን ጋብዘዉ ጀርመን ከአፍሪቃዉያኑ መንግሥታት ጋር ሥላለት ግንኙነት ተነጋግረዋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ-ቫልተር ሽታይን ማየር በበኩላቸዉ በመጪዉ ሳምንት ኒዠርንና ማሊን ይጎበኛሉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ከዚሕ ቀደም በርካታ የአፍሪቃ ሐገራትን ጎብኝተዉም ነበር።ግንኙነቱን የማጠናከሩ እርምጃ ሁነኛ ሥልት አለዉ ይሆን? ቴሬሳ ክሪኒገር የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናክሮታል

ለ እና ከ-አፍሪቃዉያን ጋር የሚደረገዉ ግብዣ-ጉብኝት፤ ዉይይት-የጦር ዘመቻ፤ ርዳታ- የትብብር-ዉል፤ ከወትሮዉ ጠንከር፤ ጠለቅ-ሠፋ፤ ደገምገም እያለ ነዉ።ምክንያቱ፤ የጀርመን የልማት መርሕ ጥናት ተቋም ባልደረባ ክርሲትነ ሐኬነሽ እንደሚሉት ብዙ ነዉ።የአፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ዕድገት እና የስደተኞች መብዛት ከብዙዎቹ ምክንያቶቹ ሁለቱ መሆናቸዉ ግን ርግጥ ነዉ።

«ባለፉት ዓመታት አፍሪቃ ዉስጥ ከፍተኛ የምጣኔ ሐብት ዕድገት መታየቱ አንዱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።የዚያኑ ያክል አሐገሪቱ ባሁኑ የስደተኞች ቀዉስም ተጠቃሽ ናት።»

ወትሮ እንደሚታወቀዉ የዉጪ ጉዳይ እና የልማት ተራድኦ ሚንስትሮች ብቻ ሳይሆኑ የትምሕርትና ሥልጠና ሚንስቴርም ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር ተባብሮ የሚሠራባቸዉን መስኮች የሚያመለክቱ ሰነዶችን ይፋ አድርጓል።ሚንስቴሩ በተለይ ከግብፅና ከደቡብ አፍሪቃ የትምሕርት ተቋማት ጋር የእርሻ ልማትን ለማሻሻል የሚረዱ ምርምርና ጥናቶችን ያደርጋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ የሚንስቴር መስሪያ ቤቶቹን ሥራና አሠራር «የሚያቀናጅ» ያለዉን መመሪያ አዉጥቷል።

መመሪያዉ ግን ወይዘሮ ሐኬንሽ እንደሚሉት «ግልፅም፤ ጥልቅም» አይደለም።ሮበርት ካፔልስም በዚሕ ይስማማሉ።GIGA የተሰኘዉ ጥናት ተቋም ሐላፊ የነበሩት ካፔልስ እንደሚሉት መመሪያዉ አፍሪቃ ዉስጥ ያለዉን ለዉጥና ዕዉነት አላገነዘበም።

Deutschland Angela Merkel & Uhuru Kenyatta in Berlin
ምስል Imago/Zuma Press

«ሥልታዊ ሠነዶቹ (መመሪያዉ) የጀርመንን ሥልታዊ ጥቅም በጣም በትንሹ ነዉ-የሚያንፀባርቁት። በአሐጉሪቱ የተደረጉ ለዉጦችንና መሠረታዊዉን ዕዉነታም በተገቢዉ መንገድ አያንፀባርቅም።»

ካፔልስ «መሠረታዊ ዕዉነት» የሚሉት በአፍሪቃ ሐገራት መካከል ያለዉን ልዩነት ነዉ።በአንዳድ የአፍሪቃ ሐገራት ምጣኔ ሐብቱና የሰዉ ኑሮ ሲሻሻል በሌሎቹ እየከፋ ነዉ።በጣም የከፋዉ ግን የተጨናገፉ መንግሥታት እና በቀዉስ የሚታመሱ ሐገራት መበራከታቸዉ ነዉ።በ2006 ብቻ አስር የአፍሪቃ ሐገራት በግጭትና ጦርነት ሲወድሙ ነበር።

በዚሕም ሰበብ የፖለቲካ ተንታኝ ካፔልስ እንደሚያምኑት ጀርመን ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር የምታደርገዉ ትብብር ከተለመደዉ ርዳታ ይልቅ ቀዉስን ለማስወገድና የምጣኔ ሐብትን ለማሳደግ የሚረዳ መሆን አለበት።በተለይ እንደ ደቡብ አፍሪቃ ኬንያ፤ናይጄሪያና ጋና ከመሳሰሉ ሐገራት ጋር የሚደረገዉ ግንኙነት በምጣኔ ሐብት ትብብር ላይ ያተኮረ መሆን አለበት።

ሐኬንሽ በዚሕ ይስማማሉ።ግን የተለመደዉ ርዳታም በተለይ ለደኸዩት ሐገራት መቀጠል አለበት ባይ ናቸዉ።

«የተለመደዉ የልማት ተራድኦ ትብብርም በተለይ ከደኸዩት ግን በአንፃራዊ መመዘኛ የተረጋጋ ፖለቲካዊ መዋቅር ካላቸዉ ሐገራት ጋር ለሚደረገዉ ግንኙነት ትልቅ ሚና ይጫወታል።ጥያቄዉ ግን ጠንካራ መዋቅር ከሌላቸዉ ሐገራት ጋር የልማት መርሕን፤ ርዳታን እና ፀጥታ የማስከበርን ሥራ እንዴት ማካሄድ ይቻላል ነዉ።»

ካፔልስ ፀጥታን ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል ባይ ናቸዉ።በዚሕ ረገድ ጀርመን ያለፈ ታሪኳን ከግምት በማስገባት ፀጥታን ለማስከበር ወታደሮቿን ከማዝመት ይልቅ በአፍሪቃ ሕብረት በኩል የየሐገራቱን ወታደሮች ማሰልጠኑ ነዉ-የሚሻለዉ።ባሁኑ ወቅት በርካታ የጀርመን ወታደሮች የሠፈሩበት የማሊዉ ተልዕኮም ከማሰልጠን እንዳያልፍ ካፔልስ ይመክራሉ።

Berlin Präsident Mosambik Nyusi bei Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

ካፔልስ እንደሚያምኑት ጀርመን አጠቃላይ ግንኙነቷን ከሌሎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካላቸዉ ጋር ይበልጥ ማጠናከር አለበት።

«የሆነ ዋጋ አለዉ።ዴሞክራሲያዊ ሐገራት ከሌሎቹ ይበልጥ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት አለባቸዉ። ይሕ ማለት ኢትዮጵያ ወይም አንጎላን ከመሳሰሉ አምገነናዊ ሥርዓቶች ጋር ከሚደረግ ግንኙነት ይልቅ ከደቡብ አፍሪቃ፤ኬንያ እና ጋና ጋር ይበልጥ አብሮ መስራት ያስፈልጋል።»

የጉብኝት ልዉዉጡ ሰሞኑን መደጋገሙ ግን የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት ከዚሕ ቀደም ከነበረዉ የተለየ አይደለም።ዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በምዕራብ አፍሪቃ የሚያደርጉት አሸባሪነትም አሸባሪነትን የመዋጋቱ ዘመቻ አካል ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ