1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ምርጫ ሂደት ምን ይመስላል?

ሰኞ፣ ሰኔ 5 2009

በመጭዉ የጎርጎረሳዊ በመሰከረም 2017 ዓ.ም ጀርመኖች በአደባባይ እና በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች፣ መሪዎቻቸውን እና እደራሴዎቻቸውን "በነጻና ምሥጢር" አለ ምንም ተጽዕኖ ይመርጣሉ ። ጀርመናዉያን የምርጫ ሂደት እንዴት እና በምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/2eVMr
Deutschland Reichstag
ምስል picture-alliance/R. Goldmann

ሥልጣኔና እና አብሮ የመኖር ፍልስፍና

2017፡-  በጀርመን ምርጫና የምርጫ ሥነ-ሥርዓት  ለመሆኑ እንዴት ነው!...ምንስ ይመስላል!በየአራት ዓመቱ ጀርመን አገር ስለሚካሄደው የምርጫ  ሥነ-ሥርዓት ሲነሳ ሁልጊዜ እዚህ የሚጠቀስ አንድ ዓረፍተ ነገር  አለ፡፡

እሱም አንድ የሸንጎ አባል ፣ወይም የሕዝብ እንደራሴ  „…ነፃ እና ምሥጢራዊ በሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት በሕዝቡ ሙሉ ፍላጎትና ውሳኔ፣ እሱ ወይም እሱዋ የሸንጎ አባል ትመረጣለች፣…ይመረጣል“ ይላል፡፡

Deutschland Bundestagswahl 2013
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ይህም አረፍተ ነገር በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 38 ላይ ሰፍሮም ይነበባል፡፡ ይህም ማለት በሌላ አነጋገር ፣ ከአሥራ ስምንት ዓመት በላይ የሆነ ማንም የአገሪቱ ዜጋ፣….ንብረቱ ሳይታይ፣ወይም የትምህርት ዕውቀቱ ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ፣ወይም ደግሞ የፖለቲካ ዝንባሌው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የእሱ ማንነት ሳይገመገም፣ ይህ ሰው ለፈለገው ሰው በነጻ ውሳኔው ድምፁን እሱ ይወክለኛል ብሎ ሰጥቶ የሸንጎ አባሉን እንደፈለገው ይመርጠዋል፡፡

ጀርመን አገርን አሠራሩን ግልጽ ለማድረግ - እያንዳንዱ ሰው ሁለት ድምፅ አለው፡፡ አንደኛው በቀጥታ የፈገለገውን የሸንጎ አባል የሚመርጥበት ድምፁ ነው፡፡ ሌላው ሁለተኛው፣ በቀጥታ የፖለቲካ ደርጅቱን የሚመርጥበት ተጨማሪ መብቱ ነው፡፡ እላይ እንደተባለው በምሥጢር አንድ ሰው ድምፁን የሚሰጥበት የግል መብቱ  ነው፡፡

አስተዋይ አንባቢ እዚህ ላይ እንደሚረዳው የጀርመኑ የምርጫ ሥነ-ሥርዓት ከአሜሪካኖቹም ሆነ ከታላቁዋ ብርታኒያ ወይም ደግሞ ከጎረቤት አገር ከስዊዘርላንድ የሸንጎ ምርጫ፣ፍጹም የተለየ ነው፡፡

የጀርመኖቹ አስተዳደር ( የሕዝብ ተወካዮች ) የሕዝብ እንደራሴዎች ዲሞክራሲ ነው። የጀርመኖች የፓርላማ ዲሞክራሲ የተመሠረተው በቀጥታ ከላይ ወደ ታች በሚወርድ የአስተዳደር ሥርዓት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ይልቅስ የተገነባው በሕዝብ ተወካይ ፣በሕዝብ እንደራሴ በእሱ የሒሊና ፍርድ ላይ ነው፡፡

ይህ አሠራር ዋና ቦታውን በጀርመን ሸንጎ ውስጥ ይይዛል፡፡ የሕዝብ እንደራሴዎች ናቸው የሕዝቡን ሙሉ ፍላጎትና የሕዝቡን ጥቅም ሸንጎው ውስጥ ድምፅ በመስጠት በሥራ ላይ የሚተረጉሙት፡፡ ልዩነቱ ያለው እላይ ከተጠቀሱት አገሮች መካከል አንድ ቦታ ላይ ነው፡፡

Stimmzettel ausfüllen
ምስል Fotolia/MaxWo

የስዊዘርላንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚጠቀሙበት የአሠራር ዘዴ በጥንታዊ ዲሞክራሲ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡አንድ ሕግ ለማውጣት ሆነ የቆየውን ለመሻር ፣ወይም አሻሽሎ ለማውጣት፣ ወይም ደግሞ አንድ የጋራ ውሳኔ ለመድረስ ጀርመኖች እንደሚያደርጉት በሸንጎ ውስጥ ፖለቲከኞች ድምፅ የሚሰጡበት አካሄድ ሳይሆን፣ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ሓሳቡን በመደገፍ ሆነ በመቃወም በቀጥታ ቁርጥ ያለ ውሳኔ እዚያው እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ብዙሃኑ ከደገፉት ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ከጣሉት ደግሞ ውድቅ ይሆናል፡፡

በጀርመን አገር አንድ ሕግ ለማሳለፍ ሆነ ለመሻር ሸንጎ ውስጥ ተመርጠው የተቀመጡት የፓርላማ አባሎች በጉዳዩ ላይ ተከራክረውበት፣ ግራና ቀኙ የሚለው ሓሳብ ተሰምቶ በመጨረሻው ድምፅ እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡

ወሳኞቹ በሌላ አነጋገር ሕዝቡ ሳይሆን የተመረጡት የሕዝብ እንደራሴዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለእያንዳንዱ የሸንጎ አባል ከባድ ኃላፊነትን እንደ መሸከምም ነው፡፡

ሕገ-መንግሥቱ ላይ አንድ እንደዚህ የሚል ዓረፍተ ነገር ሰፍሮአል፡፡

እሱም „ ..የሸንጎ አባሎች የመላው የአገሪቱ ሕዝቦች ተወካዮች ናቸው፡፡ተጠያቂነታቸውም ለማንም ቡድን ሳይሆን እራሳቸው ትክክል ነው ብለው በሚያምኑበት በሕሊና ፍርዳቸው ላይ፣ ውሳኔአቸው የተመሠረተ እና በእሱም የሚመሩ ናቸው“ ይላል፡፡

ያም ሆኖ „…ማንም ሰው የመምረጥ ሆነ ወይም የመመረጥ መብት አለው“ የሚለው የጀርመን ሕግ፣ ያ ግለሰብ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን የምርጫ ሥነ-ሥርዓት „…የመቆጣጠር መብት እንደአለውም „ ያረጋግጥለታል፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ የምርጫው አካሄድና የምርጫ ውጤቱ „ትክክል አይደለም „ ብሎ ክሱን መሥርቶ የምርጫውን ሥነ-ሥርዓት  እንደገና እንዲደገም በሕግ፣ጉዳዩን ፍርድ ቤት እቅርቦ ሊያስወስን ይችላል፡፡

የጀርመን ሸንጎ (የቡንደስ ታግ ) የወንበሮች አከፋፈል።

እ.አ.አ.ከ2002 ዓ.ም.ወዲህ የጀርመን የሸንጎ አባሎች ቁጥር ከድሮው ከፍ ብሎ አሁን 598 ደርሶአል፡፡ ከዚያ ውስጥ ከፊሉ ሁለት መቶ ዘጣና ዘጠኙ ከተለያያዩ መንደሮችና አካባቢዎች ተወዳድረው ፣ አሸናፊ ሆነው ተመርጠው ተገቢ ወንበራቸውን ለሚይዙ ሰዎች የሚሰጥ መቀመጫ ነው፡፡ ማለት በቀጥታ እሱ ወይም እሱዋ እኛን ብትወክለን „…ያዋጣናል“ ተብለው ለሚመረጡ ፖለቲካኞች የተዘጋጀ ቦታ ነው፡፡

Infografik deutsches Wahlsystem The German electoral system

የተቀሩት 299 ወንበሮች ደግሞ መራጩ ሕዝብ ይህ የእኔ ድርጅት ነው ብሎ ለሚያምነው የፖለቲካ ፓርቲ በሚሰጠው የድምፅ ቆጠራ አሸናፊ ሆኖ ለሚወጣው ድርጅት የሚሰጥ መቀመጫ ወንበር ነው፡፡ ይህም ማን እንደሚሆን የሚታወቀው፣እያንዳንዱ ድርጅት እንደ ሰውዬው ታዋቂነት እና ተሰሚነት በቅደም ተከተል ተራ በተራ ለእሱ ወይም ለእሱዋ በሚሰጡት የቅደም ተከተል አቀማመጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

እያንዳንዱ የጀርመን ክፍላተ-አገራት ፣አሥራ ስድስቱም ፣እንደ መሬቱ የቆዳ ስፋት ፣ይህ ሰው በእኛ ድርጅት ስም ቢወዳደር ጥሩ ውጤት ያመጣልናል የሚለውን ሰው ሰይሞ የምርጫ ሥነ-ሥርዓቱ ውስጥ ድርጅቱ መርቆት፣መርጦት፣ይልከዋል፡፡

ለምሳሌ የጀርመኑዋ መራሂተ መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል የክርስቲያን ዲሞክራቱን ፓርቲ ወክለው የመጀመሪያውን ቦታ ሲይዙ፣ ተቀናቃኛቸው እጩ መራሄ መንግሥት  ሚስተር ማርቲን ሹልዝ የሶሻል ዲሞክራቱን ፓርቲ ቁንጮ መሪ ሁነው ድርጅታቸውን ወክለው ውድድሩ ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡

እዚህ ላይ አንድ መረሣት የሌለበት ነገር ቢኖር የጀርመን ሕዝብ አይደለም አዲሱን ወይም በሥልጣን ላይ የቆዩትን የአገሪቱን መሪ መራሄ መንግሥቱን ወይም የመራሄ መንግሥትዋን የሚመርጠው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉት በሕዝቡ ተመርጠው ሸንጎ ውስጥ ወንበራቸውን የያዙት የህዝብ እንደራሴ፣ የሸንጎ አባሎች ናቸው፡፡

የመጀመሪያ ድምፅና ሁለተኛ ድምፅ፡፡ 

በሕጉ መሠረት አንድ ሰው በጀርመን አገር ሁለት ድምፅ አለው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ የሚባል። አንድ መራጭ ወዶና ፈልጎ ከሚሰጠው ከሁለቱ ድምፆች መካከል ውስጥ ወሳኙ ደግሞ በጀርመን ፖለቲካ ዓለም ሁለተኛው ድምፅ ነው፡፡

ይህኛው ሁለተኛ የተባለው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ሸንጎ ውስጥ ገብተው ወንበራቸውን ለመያዝ ፖለቲከኞቹን የሚያስችል መንገድ ነው፡፡ እንበል አንድ ድርጅት በጀርመን አገር ምርጫ ከመቶ 35% ከአገኘ በሸንጎው ውስጥም ከሚደለደሉት ውንበሮች ውስጥ 35 ከመቶው የሚሆነው መቀመጫ አለጥርጥር ያገኛል፡፡

በሌላ አነጋገር በሸንጎ ውስጥ የብዙሃኑን ቁጥር ከፍና ዝቅ የሚያደርገው ይህኛው የድምፅ አሰጣጥ ውጤት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ በሁለተኛው የድምፅ አሰጣጥ ድጋፍ አግኝቶ ብዙውን ድምፅ የሰበሰበ ድርጅት አሸናፊም ነው፡፡

በነገራችን ላይ አንድ ሰው የመጀመሪያ የምርጫ ድምፁን ወይም የሁለተኛ የምርጫ ውሳኔውን እንደፈለገው ከፋፍሎ አንደኛውን ለአንዱ ድርጅት፣ ሌላውን ድምፁን ለሌላ ድርጅት ደስ እንደአለው ከፋፍሎ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ የመጀመሪያ ድምፁን ለአንዱ ሰጥቶ ሁለተኛ ድምፁን ለማንም ሳይሰጥ ሊተወዉም ይችላል፡፡ ወይም ከእነአካቴው ከምርጫው ሳጥንና ጣቢያ ርቆ እቤቱም በምርጫ ቀን ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ይህ አዲስ ያልሆነ ተደጋግሞ የሚታይ ሁኔታ ነው፡፡

Deutschland Sitzung des Bundestags in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

ትንሽ ግራ የሚያጋባና አሽቸጋሪ የሚሆነው ግን በድርጅታቸው ሰንጠረዥ ውስጥ ሳይገቡ አንዳንድ ፖለቲከኞች በቀጥታ የምርጫ ውድድር ውስጥ ገብተው ተመርጠው ብቅ ሲሉ ችግር ሊፈጠር ይቻላል፡፡ ይህም አካሄድ ሸንጎ ውስጥ የሚገቡትን ተመራጮች ቁጥር ቀደም ሲል 598 ያልናቸዉን ከፍ ሊያደርገዉ ይችላል፡፡

በዚህ ጉዞና በዚህ አካሄድ በዚህ ዓመት፣ በ2017 በመስከረም ወር በሚካሄደው የምርጫ ሥነ-ሥርዓት የሸንጎ አባሎች ቁጥር ከፍ ብሎ 700 ይደርሳል ተብሎ በአንዳዶቹ ዘንድ ይገመታል፡፡ ሸንጎ ውስጥ መግባት ግን ቀላል አይደለም፡፡

ትልቁ መሰናክል፣ የ5…መሰናክል

የጀርመኑን የምርጫ ሥነ-ሥርዓት ከሌሎቹ አገሮች የሚለየውና ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር „መሰናክል“ የሚባለው ነገር ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሸንጎው ውስጥ በሕዝብ ተመርጦ ለመግባት፣ ቢያንስ አምስት ከመቶ ድምፅ ማግኘት አለበት የሚለው ሕግ ጀርመኖችን ከሌሎቹ የአውሮጳ አገሮች ልዩ ያደርጋታል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ ደንብ ደግሞ ራቅ ያሉ አገሮችም ላይ ይታያል፡፡ በእሥራኤል አንድ የፖለቲካ ድርጅት ቢያንስ 3,25% ድምፅ እንዲሰበስብ ይጠይቀዋል፡፡ እንደዚሁ በቱርክ  አንድ ድርጅት 10 ከመቶ ድምፅ አምጥቶ መሰናክሉን ዘሎ ሸንጎ መግባት ይችላል ይላል፡፡ ለአንዳንድ ድርጅቶች 10% ድምፅ ማግኘት ከባድ ፈተና ነው፡፡

5 % የሚለው የጀርመኑ ሕግ የመጣው ደግሞ አገሪቱ ከአሳለፈችው የመከራ ጊዜና ከዚያ ከተቀሰመው ትምህርት ነው፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ዓመታት ላይ ንጉሡ እንደወረዱና  በ1920 በተገኘው የመደራጀትና የመሰብሰብ የዲሞክራሲ መብት በጥቂት ሰዎች አበረታችነት በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን በያለበት ፈልተው አገሪቱን አተራምሰው ነበር፡፡

ማንም ተነስቶ ጥቃቅንና ትናንሽ ተስፈንጣሪ ፓሪቲዎችን በመመሥረት አገሪቱን የሚመራ „…የብዙሃኑን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ጠንካራ መንግሥት“ በጀርመን አገር ለመመሥረት አስቸጋሪም ሁኔታ ፈጥረው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በሌላ መልኩ በአገሪቱ ላይ እንደገና ተመልሶ እንዳይመጣ ሕግ አውጪዎቹ „…ቢያንስ አምስት ከመቶ ድምፅ“ የሚለውን ደንብ እንደ መሰናክል አስቀምጠው ለአለፉት ዓመታት ሲሠሩበት ቆይተዋል፡፡

Infografik AfD Ergebnisse 2013-2017 ENG

አሁን ይህ ሕግ ይቀየር የሚሉ ተቺዎች ተነስተዋል፡፡ በብዙ ሺህና ሚሊዮን የሚቆጠሩ የመራጮች ድምፅ ሰሚ አጥቶ መሬት ላይ ወድቆአል ብለው መከራከራቸውን ቀጥለውበታል፡፡ በእርግጥ እ.አ.አ. በ2013 ዓ.ም. ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ መራጮች ድምፃቸውን የሰጡአቸው የተለያዩ ጥቃቅን ድርጅቶች 5% ማለፉን አቅቶአቸው ከሸንጎው በራፍ ላይ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ቀላል ቁጥር አይደለም፡፡

ግን አሁንም ቢሆን የጣሊያኑ ዓይነት የሸንጎ እጣ ዕድል ጀርመን እንዳይደርሳት ይህን ሕግና ይህን ደንብ ጀርመን ሳትቀይር እንደተለመደው ዘንድሮም በመጭዉ እ.አ.አ. መስከረም 24፤ 2017 ዓ.ም.በሚካሄደዉ ምርጫም ትቀጥልበታለች፡፡

ይልማ ኃይለሚካኤል

አዜብ ታደሰ