1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅ ተጎጂዎች እና የርዳታ አቅርቦቱ 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 30 2009

የዓለም ምግብ ድርጅት፣ WFP፣ የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ ፋኦ፣ የዓለም አቀፍ የግብርና እድገት እርዳታ ድርጅት፣ ኢፋድ እና የዓለም አቀፍ የምግብ መርሀ ግብር ተወካዮች በኢትዮጵያ ድርቅ ያጠቃቸውን አካባቢዎች ጎበኙ። ለድርቅ ተጎጂዎች ርዳታ የማቅረቡ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀጥል እንደሚገባ የተመድ መስሪያ ቤቶች ተወካዮች አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/2jOVM
Äthiopien | FAO Director General Jose Graziano Da Silva und IFAD Präsident Gilbert Houngbo
ምስል DW/G. Tedla

ድርቅ

ይሁን እንጂ፣ ለርዳታ የሚቀርበው ገንዘብ በመላ ዓለም በሚታየው የተለያየ ውዝግብ ሰበብ እያደገ ከሄደው የተረጂዎች ቁጥር ጋር አለመመጣጠኑ ችግር እንደፈጠረ ተወካዮቹ ገልጸው፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ርዳታ እንዲያቀርብ ግፊት እንደሚያደርጉ ትናንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

ሦስቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ኃላፊዎች የሶማሌ ክልልን በሳምንቱ መጨረሻ ጎብኝተዋል፡፡ ከባለስልጣናቱ አንዱ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ኃላፊ ሆዜ ግራዚያኖ ደ ሲልቫ “ይህ ዓመት በተለይ ከባድ የሆነው በዚህ አካባቢ ለሦስተኛ ወይም አራተኛ ጊዜ ድርቅ በመደጋገሙ ነው” ብለዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የግብርና እድገት እርዳታ ድርጅት (IFAD) ፕሬዝዳንት ዤልቤር ሁግቦ “ድርቅ የግድ አስቸኳይ አደጋ መሆን አይጠበቅበትም” ሲሉ ከኢትዮጵያ ጉብኝት በኋላ በጣሊያን ሮም በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ወደፊት የሚከሰት ድርቅን ለመቋቋም የሚረዱ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች እንደሚያስፈልጉም ጠቁመዋል፡፡ አስከፊ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅትም ቢሆን ማኅበረሰቡ ራሱን እና ከብቶቹን ለመጠበቅ የሚረዳው የመስኖ፣ የውኃ ማከፋፈያዎች፣ የገጠር ገንዘብ ተቋማት፣ የጤና እና እንስሳት ህክምና አገልግሎቶች ማስፈለጋቸዉንም አመልክተዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለሦስት ተከታታይ የዝናብ ጊዜያት ባለመዝነሙ የተከሰተው ድርቅ ረሃብ ማስከተሉን የረድኤት ድርጅቶች አስታወቀዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ያለው ድርቅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎችን በሚለኩበት ባለአምስት ደረጃ መለኪያ መሠረት ከጠኔ በአንድ ደረጃ ብቻ ዝቅ ያለ ረሃብ ማስከተሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዳናን በተሰኘ የሶማሌ ክልል ያሉ ነዋሪዎች እንደተናገሩት አሁን የሚያገኙት እርዳታ ራሳቸውን እና ከብቶቻቸውን ለመመገብ በቂ አይደለም፡፡

 

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ 

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ