1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደኅንነት ዋሥትና የጠፋባት ካቡል

ሰኞ፣ ግንቦት 14 2009

በአፍጋኒስታን ታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜ በፈጸሙት ጥቃት አንዲት ጀርመናዊት እንስት እና የአገሬውን የጸጥታ ጠባቂ ሲገድሉ ሌላ የፊንላንድ ዜጋ አግተው ወስደዋል። እስካሁን ለእገታው እና ግድያው ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። ካቡል የሚገኙት የዶይቼ ቬለዎቹ ሳንድራ ፒተርስማን እና ብሪግታ ሹልከ ጊል በአፍጋኒስታን የደኅንነት ዋስትና ጠፍቷል ብለዋል። 

https://p.dw.com/p/2dOpp
Afghanistan Birgitta Schülke-Gill und Sandra Petersmann in Kabul
ምስል DW

Kabul: Es gibt keine Sicherheitsgarantien - MP3-Stereo

በአፍጋኒስታን ታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜ በፈጸሙት ጥቃት አንዲት ጀርመናዊት እንስት እና የአገሬውን የጸጥታ ጠባቂ ሲገድሉ ሌላ የፊንላንድ ዜጋ አግተው ወስደዋል። እስካሁን ለእገታው እና ግድያው ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። ካቡል የሚገኙት የዶይቼ ቬለዎቹ ሳንድራ ፒተርስማን እና ብሪግታ ሹልከ ጊል በአፍጋኒስታን የደኅንነት ዋስትና ጠፍቷል ብለዋል። ጋዜጠኞቹ የጻፉትን እሸቴ በቀለ አቀነባብሮታል።

ቅዳሜ ዕለት በአፍጋኒስታኗ ካቡል ሳንድራ ፒተርስማን እና ብሪግታ ሹልከ ጊል ከጀርመን የተባረሩ ስደተኞችን ታሪክ በማንበብ እና ማድመጥ ሥራ ተጠምደዋል። የዶይቼ ቬለዎቹ ጋዜጠኞች  አሚር፤ ኑሪ፤ሙጅታባ እና ኢሳ በካቡል መኖር የፈጠረባቸውን ሥጋት እያደመጡ ነው። በካቡል የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት መረጃ «ኦፐሬሽን ሜርሲ» የተባለው የግብረ-ሰናይ ድርጅት ሲያቀብላቸው ከጀርመን ወደ አፍጋኒስታን ከተጠረዙ ተመላሾች ጋር በአንድነት ተቀምጠው ነበር። ጋዜጠኞቹ «በወቅቱ ሥጋት ገብቶን ፍርኃትም ተጭኖን ነበር።» ይላሉ ከጥቃቱ ሁለት ቀናት በኋላ በጻፉት ሐተታ። በኹከቱ የተደናገጡት ጋዜጠኞች በቅድሚያ ያደረጉት የበለጠ መረጃ ፍለጋ በካቡል ወደሚያውቋቸው ሰዎች መደዋወል ነበር።  በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የአፍጋኒስታን ጋዜጠኞች የዘገቡትን ማሰሳቸውም አልቀረም። 

በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት

በዕለተ ቅዳሜ በካቡል ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ያነጣጠረው በውጭ አገር ዜጎች ላይ ነው። በምዕራባዊ ካቡል በሚገኘው የግብረ-ሰናይ የእንግዳ ማረፊያ ላይ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸሙት ታጣቂዎች አንዲት ጀርመናዊት ወይዘሮ እና የአፍጋኒስታን የጸጥታ ጥበቃ አባል ሲገድሉ ሌላ ፊንላንዳዊት እንስት አግተው ወስደዋል። የእንግዳ ማረፊያ በማዕከላዊ እስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከስደተኞች፤የአካል ጉዳተኛ እንስቶች እና ሕፃናት ለመርዳት የሚሰራው «ኦፕሬሽን ሜርሲ» የተባለ የስዊድን የግብረ-ሰናይ ድርጅት ንብረት ነበር። የአፍጋኒስታን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒሥቴር ምክትል ቃል-አቀባይ ናጂብ ዳኒሽ የካቡል የጸጥታ ኃይሎች በአጋቾች እጅ የወደቀችውን ፊንላንዳዊት እንስት ፍለጋ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

«እንዳለ መታደል ሆኖ ቅዳሜ ዕለት ምሽት በቀበሌ 7 በተፈጸመው ጥቃት አንዲት ጀርመናዊት እና የአፍጋኒስታን የጸጥታ ጥበቃ አባል ሲገደሉ የፊንላንዳዊቷ እንስት እጣ ፈንታ አይታወቅም። መላው የካቡል የጸጥታ ጥበቃ ቡድን ፊንላንዳዊቷን ለመታደግ አሰሳ ጀምረዋል።»

Afghanistan Tatort Deutsche getötet Taliban
ምስል Reuters/O.Sobhani

ጀርመናዊቷ እንስት ከአስር አመት በላይ በአፍጋኒስታን የኖሩ ሲሆን ኦፕሬሽን ሜርሲ ለተባለው የግብረ-ሰናይ ድርጅት መስራት የጀመሩት በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ነበር። ጀርመናዊቷ የተገደሉበት ፊንላንዳዊቷ የታገቱበት የካቡል ጥቃት የሽብር ድርጊት ይሁን ሌላ እስካሁን በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ወገንም አልተገኘም። ቃል-አቀባዩ ናጂብ ዳኒሽ ግን ጉዳዩ እየተመረመረ ነው ብለዋል። ፊንላንድ ስለ እገታው አሁንም ከአሉባልታ የዘለለ መረጃ እንደሌላት አስታውቃለች።የፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር የቆንስላ አገልግሎቶች ኃላፊ ፓሲ ቱሚነን የታገቱትን እንስት ለማስለቀቅ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
«ከታገቱት ሰው ቀጣሪ ድርጅት እና የቅርብ ባልንጀሮች ጋር ግንኙነት ጀምረናል። በመገናኛ ብዙኃን በርካታ ግምቶች ቢኖሩም የፊንላንድ መንግሥት ለደኅንነት እና የምርመራ ምክንያቶች ሲባል ስለተፈጠረው ነገር እና ስለታገቱት ሰው መረጃ መስጠት አይችልም። እጅግ ሥጋት ገብቶናል። በመሆኑም በዚህ ወቅት ዋንኛ ዓላማችን የታገቱትን ግለሰብ ማስለቀቅ ነው።»

የደኅንነት ተንታኞች ድርጊቱን የፈጸመው የካቡል የተደራጀ የወንጀል ቡድን(ማፊያ) ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው። የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ከዚህ ቀደምም ሕንዳዊ፤አሜሪካዊ እና አውስትሬሊያዊን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች እና የአገሬው ነጋዴዎች የአፍጋኒስታን ከፍተኛ ፖለቲከኞች ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት ማፊያ ገፈት ቀማሽ ሆነው ያውቃሉ። 

እንዲህ አይነት ጥቃቶች በዚህ አመት በካቡል ሲፈጸሙም የመጀመሪያው አይደለም። ጋዜጠኞቹ ሳንድራ እና ብሪግታ እንደሚሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጎዱባቸው ሰባት ጥቃቶች በከተማዋ ተፈጽመዋል። ታሊባን አሊያም ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለሚፈጸሙት ጥቃቶች ኃላፊነት ሲወስዱ ተስተውሏል። 

ካቡል ሰላማዊ እና አስደሳች ነበረች የሚሉት እነ ሳንድራ በከተማዋ የደኅንነት ዋስትና እንደሌለ ግን አይሸሽጉም። «ዛሬ ሰላማዊ የሆነው ቦታ ነገ ይቀየራል» ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጣሉ። ጋዜጠኞቹ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በጥብቅ የጸጥታ መመሪያዎች ውለው ማደር ጀምረዋል። ሥጋቱ ግን ለጋዜጠኞች ብቻ አይደለም። ሳንድራ እና ብሪግታ ያነጋገሯቸው ያገሬው ሰዎች ዩናይትድ ስቴትስ እና የሰሜን ቃል-ኪዳን ጦር (ኔቶ) ወታደሮች ከታጣቂዎቹ ጋር ካልተዋጉ የሚፈይዱት ነገር የለም ባይ ናቸው።

 
ሳንድራ ፒተርስማን እና ብሪግታ ሹልከ ጊል/እሸቴ በቀለ


አርያም ተክሌ