1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ጀነራል ከስራ ለቀቁ

ማክሰኞ፣ የካቲት 7 2009

በደቡብ ሱዳን አንድ ከፍተኛ ጀነራል የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት በመቃወም ስራ መልቀቃቸዉ ተሰማ። ሌተናንት ጀነራል ቶማስ ቺሬሎ ስራቸዉን ለመልቀቅ ያቀረቡት ምክንያት በፕሬዝዳንቱና የዲንካ ጎሳ አባላት በሆኑ ከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸዉ ይፈጸማል ያሉትን የዘር ማጥፋት በመቃወም ነዉ ።

https://p.dw.com/p/2XYoE
Südsudan Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/J. Lynch

SSGen./CMS/ - MP3-Stereo

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ግን ጀነራሉ ያቀረቡት ክስ መሰረተ ቢስ ነዉ ብለዉታል።

በጎርጎሮሳዊዉ ዘመን ቀመር ከ2013 ጀምሮ በእርስበርስ ጦርነት የምትታመሰዉ አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ገጥሟታል።  ባለፍዉ ቅዳሜ የሀገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዥ የሆኑት 
ሌትናል ጀነራል ቶማስ ቺሪሎ ስዋካ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት በመቃወም ከስራ ለቀዋል።ጀነራሉ በሀገሪቱ ብሄራዊ ጦር ዉስጥ  የጠቅላላ የሎጅስቲክ  ምክትል ዋና አዛዥ በመሆን ይሰሩ ነበር።በሀገሪቱ የዉጭ አጋሮች ዘንድ ከበሬታና ተቀባይነት አንዳላቸዉ የሚነገርላቸዉ ጀነራል ቶማስ ቺሪሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና የዲንካ ጎሳ አባላት የሆኑ ከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸዉ የሚያሳዩት ምግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ትግስታቸዉ እንዲሟጠጥ እንዳረጋቸዉ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።
 የሱዳን ህዝቦች አርነት ሰራዊት በምህጻሩ ኤ ስ ፒ ኤል ኤ ከፍተኛ የጦር አዛዦችና ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር  የዲንካ ጎሳ አባል ባልሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸሙ ነዉ የሚል ክስ ማቅረባቸዉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የጀኔራሉን የመልቀቂያ ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል ።
 እንደ ጀነራሉ በሀገሪቱ የተከሰተዉን የእርስበርስ ግጭት ለማስቆም በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር በ 2015 የተፈረመዉን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ካላቸዉ ስልታዊ ፍራቻ የተነሳ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር   አጀንዳዉን ወደ የዲንካ ጎሳ  አባላት አዙረዉታል ብለዋል።
አጀንዳዉ የዲንካ ጎሳ አባላት ያልሆኑ ሰወችን  ከኖሩበት ቀዬ በግዳጅ በማፈናል ዘር ማጥፋት ላይ ያነጣጠረና የአንድ ጎሳ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ በሰዉ ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነዉ ሲሉ የዲካ ጎሳ ተወላጁን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና ባለስልጣኖቻቸዉን ወንጅለዋል።
ጀነራል ቶማስ ቺሪሎ ይህን ይበሉ እንጅ አቲኒ ወኪ አቲኒ የተባሉ የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ግን የሳቸዉን  ክስ እንዲህ ሲሉ ያጣጥሉታል።
«በስራ መልቀቂያዉ ላይ ያቀረባቸዉ ክሶች በሙሉ መሰረት ቢሶች ናቸዉ። እዉነታዉ ከ1991  አመተ ምህረት ጀምሮ ስራዉን እስከለቀቀበት ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ድረስ ለበርካታ አመታት  አሁን እሱ ሚሊሺያ እያሉ የሚጠሩት የዚህ  የጦር ሰራዊት አዛዥ ነበር። በሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ጦርም ዉስጥ የዉሳኔ ሰጭ አካል ነበር። ስለዚህ  ሰራዊቱ  ለሰራዉና ስራዉን ተከትሎ የመጣዉ ነገር ሁሉ እሱንም ይመለከታል። »

Südsudan Präsident Salva Kiir und Vizepräsident Riek Machar
ምስል picture-alliance/dpa/P. Dhil

ሌትናል ጀነራሉ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንትና የጎሳ አባሎቻቸዉን የሚወነጅሉት  በሃላፊነት ባስተዳደሩት የሎጅስቲክ ክፍል ዉስጥ ከሰሩት የሙስና  ወንጀል ለማምለጥ መሆኑን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጨምረዉ ገልጸዋል።
ዘግይተዉ በወጡ መረጃወች መሰረትም ሌትናል ጀነራሉ የት እነደሄዱ ባይታወቅም ሀገሪቱን ለቀዉ መዉጣታቸዉ ተሰምቷል።
 ከ 60 በላይ ጎሳወች መኖሪያ የሆነችዉና በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር ነጻነቷን ያገነችዉ አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን፤ የሶስተኛ አመት የነጻነት በአሏን በወጉ ሳታከብር በዲንካዉ ጎሳ አባል ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና  በኑዌሩ ጎሳ በምክትላቸዉ ሪክ ማቻር መካካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሀገሪቱን ወደ እርስበርስ ግጭት  ከቷት ቆይቷል።
የርስበርስ ግጭቱን ለማስቆም በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ስምምነቶች ቢደረጉም   ግጭቱ እያደር በማገርሸቱ በሀገሪቱ  እስካሁን ሁነኛ መፍትሄ ሳይገኝ ቆይቷል።በዚህም የቀድሞዉን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን ጨምሮ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰወችን ለስደትና በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ዘገባወች ያመለክታሉ።

  ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ