1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ወቅታዊ ሁኔታ

ሐሙስ፣ ግንቦት 2 2010

የመን ዛሬም በሳውዲ መራሹ ጥምር ኃይል በደረሰባት የአየር ድብደባ የሰዎች ሕይወት እየተቀጠፈባት ነው። በዛሬዉ ዕለት በአየር ድብደባው ሰባት ሰዎች መገደላቸውን በጦርነት የተተራመሰችዉ የመን ባለስልጣናት ተናግረዋል። በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሁቲ አማፅያን በበኩላቸው ትናንት ወደሪያድ ሚሳኤል መተኮሳቸው ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/2xV9l
Jemen Luftangrif auf Sanaa
ምስል picture-alliance/dpa/Xinhua News Agency/M. Mohammed

የአካባቢዉ ሰላም አሁንም አሳሳቢ ነው

የመን በመካከለኛው ምሥራቅ በጎራ ተከፋፍሎ በእጅ አዙር በሚካሄደው የአረብ ሃገራት ውጊያ መለብለብ ከጀመረች ዓመታት እንደዋዛ ነጉደዋል። ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፕሬዝደንት አብዱ ራቡ መንሱር ሃዲ መንግሥት የሳውድ አረቢያ እና አጋሮቿ ድጋፍ እንዳለው ቢነገርም ከሰሞኑ ከተጓዳኞች አንዷ ከሆነችው የተባበረው አረብ ኤሜሬት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኤሜሬቶች ወደ የመኗ ስኮትራ ደሴት ወታደራዊ ኃይል በማጓጓዝ የአየር ማረፊያ እና ወደቧን ተቆጣጥረዋል። ይህን ርምጃ ያወገዘው ፕሬዝደንት መንሱር ሀዲ አስተዳደር በበኩሉ በተጠቀሰችው ደሴት ላይ የፀጥታ ተቋማቱን ለማጠናከር ማሰቡን አመልክቷል። ከየአቅጣጫው በጦርነት ወደተወጠረችው ወደዚች ሀገር በየዕለቱ 7 ሺህ የሚሆኑ አፍሪቃውያን ተሰዳጆች እንደሚገቡ ደግሞ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካቹ ድርጅት IOM ይገልጻል። የሁለት ወገን ኃይሎች ኃይል መፈተኛ የሆነችው የመን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ጅዳ የሚገኘው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክን በስልክ አነጋግሬዋለሁ።

ነብዩ ሲራክ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ