1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ይህን ለመሰለ ጊዜ ተብሎ የተቀመጠ ህግ አለ”- ሽታይንማየር

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2010

የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬ ባስተላለፉት የገና በዓል መልዕክታቸው የመንግስት ምስረታ የዘገየባቸውን የሀገሪቱ ዜጎች “በትዕግስት እንዲጠብቁ” አሳሰቡ፡፡ “ከዚህ ቀደም ያልተለመደ አይነት የመንግስት ቅርጽ ይኖራል” ለሚለው ጥርጣሬም ምስረታው የሚከናወነው “በህገ መንግስቱ መሰረት በተቀመጡ ህጎች” እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2pw18
Weihnachtsansprache Bundespräsident
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

“ይህን ለመሰለ ጊዜ ተብሎ የተቀመጠ ህግ አለ”- ሽታይንማየር

በጀርመን የርዕሰ ብሔርነቱን መንበር የያዙ መሪዎች ለገና በዓል የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ተጠባቂዎች ናቸው፡፡ መሪዎቹ በመልዕክቶቻቸው ከእንኳን አደረሳችሁ በዘለለ የወቅቱን አንገብጋቢ ጉዳዮች ያነሳሉ፡፡ በንግግሮቻቸው የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከቀናት በኋላ በሀገሬው በሚብተው አዲስ ዓመት የሚሆን፣ የሚታሰበውን ጠቋሚ ነው፡፡ የዘንድሮው የፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የገና በዓል መልዕክትም ከዚህ አልራቀም፡፡ ፕሬዝዳንቱ የጀርመናውያን ቁጥር አንድ አጀንዳ የሆነውን የመንግስት ምስረታ ጉዳይ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡

ጀርመን የምክር ቤት ምርጫ ካካሄደች ሶስት ወራት ቢቆጠርም እስካሁንም መንግስት መመስረት አልቻለችም፡፡ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በጊዜያዊነት አስተዳደራዊ ስራዎችን እየሰራ ቢቀጥልም ስራዎቹ ውሱንነት አለባቸው፡፡ አዲስ ተመራጩ የጀርመን ምክር ቤት (ቡንደስታግ)ም የተለመደ ስራውን መከወን አልቻለም፡፡ የምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጥረው መንግስት መመስረት ባለመቻላቸው ለምክር ቤቱ ስራ ወሳኝ የሆኑት የተለያዩ ኮሚቴዎች ስራቸውን አልጀመሩም፡፡

ይህ የሀገራቸው የፖለቲካ ሁኔታ በርካታ ጀርመናውያንን ግራ ቢያጋባም ፕሬዝዳንት ሽታይንማይር ግን በገና መልዕክታቸው ውጤቱን “በትዕግስት እንዲጠብቁ” አሳስበዋል፡፡ ሽታይንማይር የኢየሱስ ክርስቶስን የቤተልሄም ውልደት በማነጻሪያነት በመጥቀስ የሀገራቸው ዜጎች “ተስፋ ማድረጋቸውን” እንዲቀጥሉ መክረዋል ፡፡ በመሪዎቻቸው ላይ ያላቸው እምነት እንዳይሸረሸርም ጠይቀዋል፡፡ 

“የምንኖረው ያልታሰቡ ነገሮች በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙን ጊዜዎች ላይ ነው፡፡ እነዚህ አደናጋሪ ወቅቶች ናቸው፡፡ እኛ እንደ ህዝብ ካልጎበዝን እና ያልተጠበቁትን ነገሮች በግልጽ ካልተጋፈጥን የቤተልሄም እረኞች ከተልዕኳቸው ሳይደርሱ ይለያያሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡“ሳይታሰቡ የሚገጥሙ ነገሮች ሁሉ ፍርሃትን ሊወልዱ አይገባም” የሚሉት ሽታይንማይር ለዚህም የዛሬ ሰላሳ ዓመት ግድም በገና በዓል ወቅት የበርሊን ግንብ በፈረሰ ጊዜ የነበረውን ስሜት አስታውሰዋል፡፡ የያኔውን ጊዜ “የማይረሳ” ሲሉ የጠሩት ፕሬዝዳንቱ ወቅቱ በብዙዎች ዘንድ እርግጠኝነት የጎደለበት ነበር” ብለዋል፡፡ የበርሊን ግንብ መናድ የገና ተዓምር ሳይሆን የደፋር ሰዎች ስራ እንደነበር በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ የመንግስት ምስረታንም ጉዳይ በተመሳሳይ መልኩ መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

Weihnachtsansprache Bundespräsident
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

“ሁሉም ያልተጠበቁ ነገሮች፤ መፍራት እንዳለብን አላስተማሩንም፡፡ ይህ ባልተለመደ መልኩ ለዘገየው የመንግስት ምስረታም ይሰራል፡፡ ሀገሩ በመሰረታዊ ህጋችን በተቀመጠው መሰረት፣ በደንቡ መሰረት እየሰራ ነው፡፡ ምንም እንኳ በቅርብ አስርት ዓመታት ተግባራዊ ባናደርገውም ይህን ለመሰለ ጊዜ ተብሎ የተቀመጠ ህግ አለ፡፡ ስለዚህ ለመተማመን ምክንያት አለን” ሲሉ ጉዳዩ ሊያሳስብ እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡

ወደ ርዕሰ-ብሔርነቱ ከመጡ አንድ ዓመት ብቻ የሆናቸው ሽታይንማይር በስልጣን ቆይታቸው የተመዘገበውን ውጤት በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሳክሶኒ ግዛት የተመለከቱትን የወጣቶች ጥረት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ወደ ትልልቅ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰትን ለመግታት አነስተኛ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን አድንቀዋል፡፡ በየቦታው የሚደረጉት ጥረቶች ትንንሽ ቢመስሉም “ራሳችንን መርዳት የምንችል እንደሆነ” የሚያሳይ “ታላቅ መልዕክት አንግበዋል” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡ 

ጀርመን ባለፉት ዓመታት የተጓዘችበት መንገድ የገመገሙት ሽታይንማየር ተከታዩን ብለዋል፡፡  “በኢኮኖሚ ምክንያታዊነት እና በማህበራዊ ፍትህ መርኆዎች የተቃኙ ፖሊሲዎችን የምንከትል ሀገር ሆነን ቆይተናል፡፡ ትስስራችን እንደተጠበቀ እንዲቆይ ጥንካሬ እና ቆራጥነት ያለን ሀገር መሆናችን ይበልጥ ወደ አንድነት አምጥቶናል፡፡ በሁለቱም ጥረቶቻችን ግን አሁንም በርካታ የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የገና መልዕክታቸውን ያጠቃለሉት የክርስትና እምነት ተከታዮች ላልሆኑ እና ሃይማኖት አልባ ለሆኑት ጭምር መልካሙን በመመኘት ነው፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ