1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓይነ-ማዝን ማጥፋት ይቻላል

ማክሰኞ፣ የካቲት 8 2008

የዓይነ-ማዝ (ትራኮማ) በበሽታዉ ከተያዘ ሰዉ በተለያዩ መንገዶች ዝንቦችን ጨምሮ በቀላሉ የሚተላለፍ የዓይን ህመም ነዉ። በዚህ በሽታ ይበልጥ የሚጠቃዉና ለዓይነ-ማዝ የተጋለጠዉ ደግሞ ንፁህ ዉኃ የማግኘት ዕድል የሌለዉ እና የአካባቢ እና የግል ንፅህናን ለመጠበቅ ተገቢዉን ጥንቃቄ የማያደርግ ወገን ነዉ።

https://p.dw.com/p/1HwMA
Symbolbild Auge
ምስል Colourbox

የዓይነ-ማዝን ማጥፋት ይቻላል

የዓይነ- ማዝ ወይም ትራኮማ በሞቃት አካባቢ ከሚገኙና የተዘነጉ ከሚባሉ 17 በሽታዎች አንዱ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ድርጅቱ የዓይነ-ማዝን ጨምሮ 17ቱንም በሽታዎች እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020 ድረስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ወይም ፈፅሞ ለማጥፋት አቅዷል።

የዓይነ-ማዝ በመላዉ ዓለም በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ 1,8 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ለዓይነ ስዉርነት የዳረገ በተለይም ድህነት ባጠቃቸዉ የተለያዩ ሃገራት ገጠራማ አካባቢ የተስፋፋ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያስረዳሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓይነ-ማዝ የተስፋፋባቸዉን አካባቢዎች በካርታ ለማስፈር ቅኝት ያካሄደዉ ፕሮጀከት እንደሚለዉ፤ በሽታዉ ከአንዱ ሰዉ ወደሌላዉ በልብስ፤ በእጅ ንክኪ ወይም በዝንብ አማካኝነት በቀላሉ ይተላለፋል። ለመስፋፋቱ በዋነኛ ምክንያት የንፁሕ ዉኃ አቅርቦት ማጣት እና የአካባቢ እና የግል ንፅሕና አለመጠበቅ ይጠቀሳሉ። እንደዘገባዉ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ በበሽታዉ በሚያዙት ቁጥር በአስደንጋጭ መልኩ እየጨመረ ነዉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጂ በዓይን ህክምና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ትልቅ ሰዉ ተሾመ የዓይነ-ማዝ በሀገሪቱ ዋነኛ የዓይነስዉርነት መንስኤ መሆኑን ቢገልፁም ቁጥሩ እየጨመረ ነዉ የሚለዉ ለማለት ግን ያዳግታል ይላሉ።

zum Thema - Dorfälteste in Afghanistan - Symbolbild
ምስል Getty Images/Afp/Shah Marai

ሳይትሴቨር የተሰኘዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያካሄደዉ ጥናት እንደሚለዉ የዓይነ-ማዝ ሊስፋፋባቸዉ ይችላል ተብለዉ በተገመቱ እንደናይጀሪያ፤ ላኦስ፣ ካምቦዲያ እና ግብፅ የመሳሰሉ ሃገራት በበሽታዉ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ቀንሶ ነዉ የተገኘዉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይም በአንዳንድ አካባቢ ከማኅበረሰቡ ሃምሳ በመቶዉ የዓይነ-ማዝ ተጠቂ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። ዶክተር ትልቅ ሰዉ ተሾመ ዘገባዉ ትክክል ነዉ ይላሉ።

ትራኮማ ወይም የዓይነ-ማዝን በቀጣይ አምስት ዓመታት ዉስጥ ፈፅሞ ለማጥፋት የተቆረጠ ይመስላል። በሽታዉ የሚገኝባቸዉን አካባቢዎች በማጥናት ይዞታ እና የጉዳት ስፋቱን የመዘገቡት ወገኖች ይህን ማድረጉ አይከብድም የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። ዋቢም ይጠቅሳሉ፤ ፈንጣጣን ከዓለም ማጥፋት ተችሏል፤ ባይ ናቸዉ። እናም የዓይነ-ማዝም ከጥቂት ዓመታት በኋላ የዓይን ብርሃን የማሳጣት አቅም አይኖረዉም። ይቅናቸዉ። ዝርዝሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ