1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ቀንና የሜድትራንያን ባሕር ጉዞ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 13 2009

የዓለም ስደተኞች ቀን ዛሬ በመላዉ ዓለም ታስቦ ዉሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከ65.5 ሚሊዮን ከሚበልጠዉ የዓለም ስደተኛ አብዛኛዉን የሚያስተናግዱት ከዓለም እጅግ የደኸዩት ሐገራት ናቸዉ።ወደ በለፀጉት ዓለማት በተለይ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ከሚሞክሩ ስደተኞች መካከል በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ በየበረሐዉ እና ባሕር ዉስጥ ይሞታሉ።

https://p.dw.com/p/2f3Mf
Libyen spanische Patrouille überwacht Flüchlingsboot für eine Rettungsaktion
ምስል picture-alliance/AA/M. Drinkwater


 ከአደጋ ተርፈዉ ተርፈዉ  አዉሮፓ የሚገቡት ስደተኞችም ቢሆን የተገን ጥያቄ ተቀባይነት ከማጣት ጀምሮ የሚገጥማቸዉ ችግር ቀላል አይደለም።ስደተኞቹን በሚያስተናግዱት ሀገራት ጉዳዩ አወዛጋቢ ርዕስ ሆኗል።
ከሊቢያ የነዳጅ ማጣሪያ አጠገብ ከሚገኘዉ መቃብር የሚወጣዉ ሽታ እንደተበላሸ እንቁላል ይቆንሳል።በአካባቢዉ  1500 የሚሆኑ  ስደተኞች ተቀብረዉበታል።አብዛኞቹ በጅምላ ነዉ የተቀበሩት።«እንደ አለመታደል ሆኖ በክፍያ ማግኘት የቻልነዉ ሥፍራ ይሕ ብቻ ነዉ» ይላሉ የሊቢያ የቀይ ጨረቃ ማሕበር ባልደረባ ሳዲቅ ይአሽ።ይአሽ ወደ አዉሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ የሞቱ ሰዎችን የመቅበር እና ማስቀበር ኃላፊነት አለባቸዉ።
አጥብቆ አማኙ የሊቢያ ሕዝብ ሟች ስደተኞች ከመቃብር ሥፍራዉ እንዲቀበሩ አይፈቅድም።«ለነዚሕ ሙታን የተሻለ ነገር ማድረግ ነበረብን» ይላሉ የቀይጨረቃዉ ባልደረባ ሳዲቅ ይአሽ ይቅርታ በሚጠይቅ ስሜት።ግን ተጨባጩ ሁኔታ እና ሰብአዊነት አልተጣጣሙም።
ካለፈዉ ጥር ወዲሕ ብቻ የሜዲተራንያንን ባህር አቋርጠዉ አዉሮፓ ለመግባት  ሲሞክሩ ከ2000 በላይ ሰዎች ሊቢያ ጠረፍ አጠገብ ባሕር ዉስጥ ሰምጠዋል።የብዙ ሰወችን ሕይወት  የሚቀጥፈዉ ስደት፤ለሰዉ አሸጋጋሪዎች ጥሩ የገቢ ነዉ።ሰዉ ማሸጋጋር በዓመት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገኝበት ኢንዱስትሪ ሆኗል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ተራ «ነጋዴ» የነበሩት አሸጋጋሪዎች በአሁኑ ወቅት  የተደራጁና ስደተኞች በማሸጋገር የሰለጠኑ ቡድኖች ሆነዋል።በተለያዩ ሀገራት የሚደረገዉ ጦርነት፣ የፓለቲካ አለመረጋትና ድህነት መባባሱም ለአሸጋጋሪዎቹ «የደራ ገበያ» ምንጭ ነዉ።
ሁለተኛ አመቱን የደፈነዉን የጅምላ ፍልሰት ችግሮች ለማቃለል የአዉሮፓ መንግስታት ተባብረዉ ለመስራት አለመቻል ወይም አለመፍቀዳቸዉም ሌላዉ ለስደተኞቹ ተጨማሪ መከራ፤ ለአሸጋጋሪዎቹ ጥሩ ሲሳይ ነዉ።
አዉሮፓ ከጎርጎሮሳዊዉ 1990 ጀምሮ የጋራ የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ሕግ እንዲኖራት ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረግም አባል ሐገራት የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ ሥለሌላቸዉ ሙከራዉ በየጊዜዉ እንደከሸፈ ነዉ።
የአዉሮጳ ሕብረት አሁንም ሁሉንም አባል ሐገራት የሚያስማማ የጋራ ደንብ የለዉም።የጀርመኑ የድሬስደን ዩንቨርሲቲ የፍልሰት ጉዳይ አጥኚ  ኦሊቨር አንጌሊ እንደሚሉት የአዉሮጳ መንግስታት በፍልሰተኞች ጉዳይ የሚመርጣቸዉን ሕዝብ ፈርተዉታል።
ፓላንድን ቼክ ሪፐብልክ፤ አንዳንዴ ሐንጋሪን እና የመሳሰሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት ስደተኞችን  የማስተናገዱን ጥያቄ አይቀበሉትም። የስደተኞች ጉዳይ በብዙ ሐገራት የርዕዮተ-ዓለም አካል ሆኗል።በዚሕም ምክንያት የአዉሮጳ ሕብረት በየአባል ሐገራት እንዲሰፍሩ ከሚወስንላቸዉ ስደተኞች ቁጥራቸዉ አነስተኛ የሆነ በነዚሕ ሐገራት ቢመደቡ እንኳን መንግሥታቱ የየራሳቸዉን መራጭ ሕዝብ ሥለሚፈሩ መቀበሉን አይፈቅዱትም።»

Mittelmeer - Flüchtlinge – Boot
ምስል Getty Images/AFP/A. Messinis

አንጌሊ  ሥለ ጀርመን መንግሥት የስደተኞች መርሕ አንስተዉም «አዉሮጳ አቀፍ ደንብ አለን ግን የጀርመን ብቻ ሎተሪም አለን» ይላሉ።ጀርመን ስደተኞችን በማስተናገድ «የተሻሉ» ከሚባሉት ሐገራት አንዷ ናት።ይሁንና ስደተኞች ተቀባይነት የማግኘታቸዉ ጉዳይ ከግዛት ግዛት ይለያያል።
በመሠረቱ ለስደተኞች ጥገኝነት የሚሠጠዉ ጦርነት፤ሽብር፤ ፖለቲካዊ ጭቆናን እና የሠብአዊ መብት ረገጣን ሸሽቶ የመጣ ከሆነ ነዉ።ተመሳሳይ ምክንያት የሚያቀርቡ ስደተኞች ከአንዱ ግዛት ተቀባይነት ሲያገኙ ሌላዉ ጋ ጥያቄያቸዉ ዉድቅ መሆኑን የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ይቃወሙታል። 
«ፕሮ አዙል » የተባለዉ የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት መሪ ካርል ክኖፕ ምሳሌ አላቸዉ።
«በጎርጎሮሳዊዉ 2015 ከአፍጋናዉያን አመልካቾች 70 በመቶዉ ጥገኝነት ያገኙ ነበር።ከሁለት አመት በሁዋላ ወደ 50 በመቶ ወርዶ፤ ብዙዎቹ ጥያቄያቸዉ ዉድቅ ሆነ።በሀገራቸዉ የሚደረገዉ ግጭትና ጥቃት ግን እየተባባሰ ነዉ።ጥገኝነት ለማግኘት ምክንያቱ በመጡበት ሀገር ያለዉ ቀዉስና ችግር ካልሆነ እንግዴሕ ሌላ ምክንያት መኖር አለበት ማለት ነዉ።በኛ እምነት ይሕ አስቀድሞ የሚወሰን ፖለቲካዊ እርምጃ ነዉ።»
በጀኔባ የስደተኞች የስምምነት መሰረት በኢኮኖሚ ምክንያት የሚሰደዱ ሰወች ከለላ አያገኙም።ይሁንና ብዙዎች እንደሚገምቱት አዉሮጳ ከሚገቡት ስደተኞች ግማሽ ያሕሉ የኤኮኖሚ ስደተኞች ናቸዉ።ከምዕራብ አፍሪቃ የሚመጡ አብዛኞቹ ስደተኞች ለዚሕ እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ።ይሁንና  የጥገኝነት ፍቃድ የሚከለከሉ ስደተኞችን ወደ ሐገራቸዉ  ከመመለስ ይልቅ  በገቡበት ሐገር እንዲቆዩ ይደረጋል።አንዳድ የስደተኛ ጉዳይ አጥኚዎች እንዲሕ አይነቱን አሰራር ሥደተኛ አሸጋጋሪዎችን የሚበረታታ ይሉታል። ብራስልስ ቤልጅግ የሚገኘዉ ጥናት ተቋም ባልደረባ  ጉትራም ቮልፍ አንዱ ናቸዉ።
በእርግጥ ህጋዊ የስደት መንገዶችን እደግፋለሁ። ህጋዊ ስደትን ከፈቀድን ህገ ወጥ ስደት እና የአሸጋጋሪዎችን ንግድ ማስወገድ እንችላለን።ይሕ በተጨባጭ ገቢር ሥለሚሆንበት ሥልት መወያየት አለብን ።ለስደተኞች ሕጋዊ  መንገድ  የሚሰጠዉ በጣም ለተማሩ ሰወች መሆን ነዉ አለበት? ለሰብዓዊ ጉዳዮችስ የተወሰነ ፈቃድ መስጠት አለብን? ወይስ  በሎተሪ መልክ ነዉ መሆን ያለበት ። እኔ  የሜድትራኒያ ብሕርን ሕገ-ወጥ የስደት ጉዞ ለመወጋት ከሁሉም የተቀየጠ ሥልት መከተሉ ጥሩ ይመስለኛል።
ቮልፍን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት ሕገ-ወጥ ስደትንና የስደተኞችን ሞትን ለማስወገድ መፍትሔዉ፤ ህገወጥ አሸጋጋሪዎችን መቆጣጠር፤ ህጋዊ የስደት መንገዶችን መክፈት፤ በየሀገራቱ የፓለቲካ መረጋጋት እንዲኖር ማገዝና  የመሳሰሉትን መፍትሄወች ደባልቆ መጠቀም ጠቃሚ ነዉ።

 

ፀሐይ ጫኔ/ያን ፊሊፕ ሾልስ 

ነጋሽ መሐመድ