1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የብር የምዛሪ ተመንን እንድትከልስ አሳስቧል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2009

በኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ መካከል የሚታየውን ጉድለት ለማስተካከል አገሪቱ የብር የምንዛሪ ተመንን እንድታስተካክል የዓለም ባንክ ጥቆማ አቅርቧል። ኢትዮጵያውያን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ግን ከሚገባው በላይ ይመነዘራል የሚባለውን የብር የምንዛሪ ተመን ማስተካከል ውስብስብ ችግሮች ያሉበትን የወጪ ንግድ አይታደግም ባዮች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/2UH1g
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

የብር የምንዛሪ ተመን እና የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ጉድለት

ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የውጪ ንግድ የከፋ አፈፃጸም ማሳየቱን የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ጠቁሟል። ባንኩ የወጪ ንግድ ጉድለቱ በጎርጎሮሳዊው 2015/2016 የበጀት ዓመት ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን 10.4 በመቶ መድረሱን ጠቁሟል። የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በዳሰሰበት ዘገባው ጉድለቱ በወጪ እና ገቢ ንግድ እና አገልግሎቶች መካከል የሚታየው አለመመጣጠን አንደኛው ምክንያት እንደሆነ አትቷል። በወጪ እና ገቢ ንግድ መካከል ያለው አለመመጣጠን ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን 19.8 በመቶ ድርሻ እንዳለው የጠቆመው የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ለውጭ የሚቀርቡ ሸቀጦች መጠንም ሆነ ዋጋ ጫና አሳድረዋል ብሏል።

ባንኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሽቆለቁለውን የውጭ ንግድ ለመታደግ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለመጠበቅ የብር የምንዛሪ ተመንን እንድታስተካክል ጥቆማ ሰጥቷል። ባንኩ አሁን የኢትዮጵያ ብር ያለው የምንዛሪ ተመን እውነተኛውን የኤኮኖሚ አቅም አያሳይም ባይ ነው። ወይም በዓለም ባንክ አባባል የኢትዮጵያ ብር ምንዛሪ ከሚገባው በላይ ተተምኗል። የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም «የኢትዮጵያ ብር ምንዛሪ ከሚገባው በላይ ተተምኗል ሲባል ገበያው ለገንዘቡ ያለውን የፍላጎት እና የአቅርቦት መጠን ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ እየተመነዘረ ነው።» ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ቁጥጥር የሚደረግበት የገንዘብ ፖሊሲ ትከተላለች። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት በዚህ የቁጥጥር ፖሊሲ የገበያው ተዋናዮች የምንዛሪ ተመንን የመወሰን አስተዋፅዖ የተገደበ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሙራይ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የማክሮ ኤኮኖሚክስ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር ሰዒድ ሐሰን የኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት የሚገለገሉበት የብር የምንዛሪ ተመን እውነተኛ ዋጋውን አያመለክትም የሚል እምነት አላቸው።

Äthiopien Schuhfabrik Fabrik Herstellung Schuhe
ምስል Getty Images/Z. Abubeker

የኢትዮጵያ ባንኮች አንድ የቻይና ዩዋን ሶስት ብር ከሃያ ሦስት ሳንቲም ገዝተው ሦስት ብር ከሐያ ዘጠኝ ሳንቲም ይሸጣሉ። ዩሮ በሃያ ሦስት ብር ከአምሳ ስድስት ሳንቲም ገዝተው ሃያ አራት ብር አካባቢ ይሸጣሉ። ሃያ ሁለት ብር ከሠላሳ ሁለት ሳንቲም የሚገዙትን የዩናይትድ ስቴትስ ዶላር ሃያ ሁለት ብር ከሰባ ስድስት ሳንቲም ገደማ ይሸጡታል። ይኸ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የታኅሳስ አራት ቀን 2009 ዓ.ም. መረጃ ነው። የብር የምንዛሪ ተመኑ ከኢ-መደበኛው የእጅ በእጅ ምንዛሪ እጅጉን የተራራቀ ነው።

የብር የምንዛሪ ተመንን የመወሰን ሥልጣን የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ሌሎች ባንኮች ናቸው። ባንኮቹ ከተቀመጠላቸው ዕለታዊ ምንዛሪ ተመን ባነሰ መልኩ ይገበያያሉ። የውድድሩ የመጨረሻው ከፍ ያለ የምንዛሪ ተመን የዕለቱ የምንዛሪ ተመን ሆኖ ይወሰናል። አቶ ጌታቸው ተክለማርያም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ቁጥጥር የሚደረግበት የገንዘብ ፖሊሲ በሚከተሉ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እና አቅርቦትን ለመለየት የእጅ በእጅ አልያም ጥቁር ገበያን እንደ አማራጭ መጠቀም የተለመደ ቢሆንም ትክክለኛ ነው ማለት ግን አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

የውጭ ንግዳቸው ግብርና ተኮር እሴት ያልተጨመረባቸው ምርቶች ላይ የተንጠጠለ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከሚገባው በላይ የተተመነ የመገበያያ ገንዘብ ለነጋዴዎች አሉታዊም አዎንታዊም ጎን አለው። አቶ ጌታቸው እንደሚያስረዱት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከሚገባው በላይ የተተመነ የመገበያያ ገንዘብ ላኪዎች ከፍ ባለ ዋጋ የገዙትን ምርት በርካሽ እንዲሸጡ ይገደዳሉ። በርካሽ የገዙትን ምርት በውድ ዋጋ የመሸጥ አጋጣሚ ለሚፈጥርላቸው አስመጪዎች ግን መልካም እድል ነው።

Dschibuti Tankwagen
ምስል Getty Images/S. Gallup

የዓለም ባንክ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ዳሰሳ አምስተኛ እትም የብር ምንዛሪ ከሚገባው በላይ በመተመኑ ምክንያት አገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ይሳናታል ብሏል። ባንኩ በኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የብር የምንዛሪ መጠንን ማስተካከል ሁነኛው መፍትሔ ነው የሚል የፖሊሲ ጥቆማ አቅርቧል። ረዳት ፕሮፌሰር ሰዒድ ሐሰን ግን የዓለም ባንክን ጥቆማ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና ከመጽሐፍ የተቀዳ ሲሉ ይተቹታል።

አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያምም የዓለም ባንክ የመፍትሔ ጥቆማ ሃሳባዊ ነው የሚል ትችት አላቸው። አቶ ጌታቸው በብር ላይ የሚደረግ የምንዛሪ ለውጥ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ተሞክሮ ያመጣው ለውጥ የለም ሲሉ የወጪ ንግድ ሥርዓቱ መፍትሔ የሚሹ በርካታ ችግሮች አሉበት የሚሉት የኤኮኖሚ ባለሙያው ቁልፉ ለችግሮቹ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ነው ይላሉ።

የገንዘብ የምንዛሪ መጠንን የዓለም ባንክ በሰጠው ጥቆማ መሠረት ማስተካከል ለኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ ስርዓት የአጭር ጊዜ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ አቶ ጌታቸውም ይሁኑ ረዳት ፕሮፌሰር ሰዒድ ሐሰን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች በአይነት እና በመጠን ማሳደግ፤ የግብይት ሥርዓቱ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት ቀዳሚዎቹ እርምጃዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ሁለቱ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ