1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውሐ ችግር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2010

ዛሬ ከሰዓት ሰዎች ውሐ በጉጉት እየጠበቁ ነው። የውሐ ቦቴውን የጫነው ከባድ መኪና ግን ወደ መንደሩ በመጓዝ ላይ ሳለ ጭቃ ውስጥ ተቀርቅሮ መንቀሳቀስ አልቻለም። መኪናው ሊነሳ የሚችለው ጭነቱን ካራገፈ ብቻ ነው። ያማለት የጫነው 10 ሺህ ሊትር ውሐ መፍሰስ ይኖርበታል ።

https://p.dw.com/p/2pP6J
Uganda Flüchtlingslager in Nakivale
ምስል DW/S. Schlindwein

የውሐ ችግር

ሰሜን ዩጋንዳ ውስጥ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች በሰዎች ተጨናንቀዋል። አሁንም  የርስ በርስ ጦርነትን ግጭትን እና ረሀብን በመሸሽ በየቀኑ ቁጥራቸው 300 የሚጠጋ ሰዎች ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረው ዩጋንዳ ይገባሉ። ዩጋንዳ ለስደተኞች ጥሩ አቀባበል ታደርጋለች። ሆኖም በአንዳንድ መጠለያዎች የመሠረተ ልማት ችግሮች እና የወሐ እጥረት ስደተኞችን ለችግር እየዳረጉ ነው።የዶቼቬለዋ ሊና ሽታውደ ላጠናቀረችው ዘገባ ኂሩት መለሰ
ዩጋንዳ ውስጥ ስደተኞች የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው የተጠበቀ ነው። መሬት እና ትምሕርትም በነፃ ያገኛሉ። ይሁን እና በአንዳንድ መጠለያዎች የውሐ እጥረት ትልቅ ችግር ነው። ዩጋንዳ  የሚገኙ አብዛኛዎቹ የስደተኞች መንደሮች መሠረተ ልማት አልተዘረጋላቸውም። ብቸኛው የመጠጥ ውሐ ምንጭ ነጭ አባይ ሲሆን ውሐው ለስደተኞች የሚከፋፈለውም በመኪና እየመጣ ነው። ብዙውን ጊዜም ውሐ የጫኑ መኪናዎች ጊዜያዊ መንገዶች ላይ ቆመው ይቀራሉ።
ኤሉሪክ ፍሌቭ  መኪና ላይ በተጫነ ውሐ ማጠራቀሚያ ቦቴ ውስጥ ወሐ እየሞላ ነው። ቦቴው 10 ሺህ ሊትር የሚደርስ ወሐ ይይዛል። በፍሌቭ መኪና ላይ የተጫነው ውሐ ሰሜን ዩጋንዳ ለሚገኙ ስደተኞች የሚከፋፈል ነው። በደቡብ ሱዳኑ ረሀብ እና የርስ በርስ ጦርነት በአጠቃላይ ወደ አንድ ሚሊዮን እንደሚሆኑ የተገመቱ ሰዎች ከሀገራቸው ተሰደዋል። አንቶን ኦፖካ ባለፈው ነሐሴ ነበር ከቤተሰቡ ጋር ከደቡብ ሱዳን ዩጋንዳ የሄደው። እዚያ በመሄዱም ደህንነት ይሰማዋል። ሆኖም እዚህም ችግር እንዳለ ይናገራል።
«ከመጀመሪያው አንስቶ ውሐ አንድ ችግር ነው። ምግብ ለማብሰል፣ልብስ ለማጠብ እና ለመፀዳጃ ውሐ ያስፈልገናል። ሦስት ጊዜ ከጉድጓድ ውሐ ለማውጣት ሞክረው ነበር። ግን ወሐ አልተገኘም።» 
ርዮ ለተባለው የስደተኞች መጠለያ ነዋሪዎች በቦቴ የሚመጣ ውሐ  ነው ብቸኛው የንጹህ ውሐ ምንጫቸው። ወሀው የሚቀዳውም ነጭ አባይ ዳርቻ ከሚገኝ የውሐ ማጣሪያ ነው። ከዚህ ስፍራ ወደ 70 ቦቴ ውሐ በየቀኑ ይጫናል። ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ውሐ መሆኑ ነው።    
ከወንዙ ዳርቻ ብዙም ሳይርቁ መንገዱ 20፣ 30 በሚሆኑ ምግብ የግንባታ እቃዎች እና ወሐ በጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ተዘግቷል። የሚንቀሳቀስ የለም። 
 «አሁን በመንገዱ ምክንያት ለመቆም ተገደናል። ለሁሉም በቂ ውሐ አለ። ሆኖም ችግሩ መንገዱ፣ ረዥሙ ጉዞ ነው። በተለይ መንገዱ።»
ኤሉሪክ ፍሌቭ ባልተጠረገ መንገድ ነድቶ መንገዱን የዘጋው መኪና አጠገብ ደረሰ። ሁሉንም ለሰዓታት እዚያ ያሰረው አንድ ሚኒባስ ጭቃ ውስጥ ገብቶ ነው። 
«በዝናብ ወቅት መኪናዎች መንቀሳቀስ አይችሉም። ወሐው ሦስት እና አራት ቀናት መንገዱን እንደሸፈነ ሊቆይ ይችላል። »
ኤቭሊን ጀምስ በሰፈራ መንደሯ በሚገኘው ትልቅ የውሐ ማጠራቀሚያ አጠገብ ሆና የውሐ ቦቴውን መምጣት እየተጠባበቀች ነው። ጠዋት ውሀ ነበር። ሆኖም 10 ሺህ ሊትሩ ወሐ አልቋል።
« በቂ ውሐ ባለመኖሩ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ይደባደባሉ። ውሐው ሁለት ወይም ሦስት ቀን ዘግይቶ ከመጣ ደግሞ ችግር ነው። ሁሉም ውሐ ይፈልጋልና»
ይላል ፒተር ኒንያኩኒ። ዛሬ ከሰዓት ሰዎች ውሐ በጉጉት እየጠበቁ ነው። የውሐ ቦቴውን የጫነው ከባድ መኪና ግን ወደ መንደሩ በመጓዝ ላይ ሳለ ጭቃ ውስጥ ተቀርቅሮ መንቀሳቀስ አልቻለም። መኪናው ሊነሳ የሚችለው ጭነቱን ካራገፈ ብቻ ነው። ያማለት የጫነው 10 ሺህ ሊትር ውሐ መፍሰስ ይኖርበታል ።ይህ ሲያጋጥም የስደተኞቹ ምርጫ አንድ ብቻ ነው። 
«እዚያ ቆሻሻ ውሐ ያለበት ኩሬ አለ። ከዚያ ውሐ አምጥተን ፣አፍልተን ለምግብ ማብሰያ እና ለመጠጥ ውሐ እንጠቀምበታለን።»
ትላለች ኤቭሊን ጀምስ

Uganda - Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/dpa/O. W. Solomon
Konflikt im Südsudan Flüchtlinge 17.01.2014
ምስል Reuters

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ