1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወደቀዉ የዚምባቡዌ ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ ግንቦት 12 2007

በፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤና የገዢ ፓርቲያቸዉ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ምክንያት የዚምባቡዌ ኤኮኖሚ ወድቋል። ዛሬ በሀገሪቱ ከ16ቱ አንዱ የዚምባብዌ ዜጋ ብቻ ነዉ ቋሚ ሥራ እንዳለዉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚህ ምክንያትም በመቶና ሺዎች የሚቆጠሩ ዚምባቡዌያዉያን ሥራ ፍለጋ ወደደቡብ አፍሪቃ ይሰደዳሉ።

https://p.dw.com/p/1FTFs
Simbabwe 15 Jahre Landreform
ምስል picture-alliance/dpa/O. Andersen

[No title]

በዚህ ሁሉ ዉጥንቅጥ ዉስጥ ጥቂት ወጣት ባለሃብቶች ልምዳቸዉን በማካፈል ሀገራቸዉን መልሰዉ ለመገንባት እየሞከሩ ነዉ።

«በልቤ የያዝኩት አንድ ራዕይ አለኝ። ይህ ራዕይም ይህ ኩባንያ የእድሜ ልክ እንዲሆንና እንዲያድግ ያደርጋል። በቅርቡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ እጠብቃለሁ። ይህም የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነዉ።» ይላል ፓትሪክ ሚታንድዋ በቀልድ፤ በዉኃ የምትሠራ አዉቶሞቢል እንደፈለሰፈ።

ሰማያዊ ቱታዉን ለብሶና ጠፍጣፋ የፀሐይ መከላከያ ባርኔጣዉን አድርጎ በሃራሬ አጎራባች መንደር የመኪና ማቆሚያ ባዶ ጠርሙሶች በተከመሩበት ስፍራ መካከል ቆሟል። የተጣሉት ጠርሙሶች የፓትሪክ የገንዘብ ምንጮች ናቸዉ። በትላልቅ የፕላስቲክ ከረጢት የተሞሉት ባዶ ቆርቆሮዎችና ፕላስቲክ ጠርሙሶችም ካፒታሎቹም ጭምር። የፓትሪክ ምኞት ጥቅም ላይ የዋሉ እንዲህ ያሉ እቃዎች ተመልሰዉ ዳግም ሥራ ላይ እንዲዉሉ ማድረግ በሚያስችለዉ የንግድ መስክ መሥራት ነዉ። ይህ የስራ ዘርፍ ዚምባቡዌ ዉስጥ ያን ያህል ያደገ አይደለም።

Recycling von Plastikflaschen in China
ምስል picture-alliance/dpa

«ባዶ ቆርቆሮዎቹን ወደደቡብ አፍሪቃ ልኬ በማሽን እንዲሰሩ የማጠራቅምበት ስፍራ እየፈለኩኝ ነዉ ። ቻይና ዉስጥ እንዲህ ካሉ ጠርሙሶች ጡቦችና የመሬት ንጣፎችን እንደሚሰሩባቸዉ አዉቃለሁ፤ እናም የትኛዉ ኩባንያ ያንን እንደሚሠራ እያፈላለግን ነዉ።»

የፓትሪክ አዎንታዊ ምኞትና ዓላማ በጣም አስገራሚ ነዉ። ላለፉት 25ዓመታት ገደማ ምን ዓይነት ቋሚ ሥራ የለዉም። ኑሮዉን ለመግፋትም እራሱ የሰፋቸዉን ልብሶች ይሸጥ ነበር። ጥቅም ላይ የዋሉ ጠርሙስና ቆርቆሮዎችን መልሶ ሥራ ላይ እንዲዉሉ ለማድረግ የሚንቀሳቀሰዉ የሥራ መስኩም አዝጋሚ ነዉ፤ ያም ሆኖ ግን ከቆሻሻ ዉስጥ ተፈላጊዎቹን ጥሬ እቃዎች እሱና፤ በሥሩ የቀጠራቸዉ አራት ሠራተኞች በጋራ እየሰበሰቡ የማፅዳቱን ተግባር ያከናዉናሉ። ይህን ለማጓጓዝም አሮጌ በእጅ የሚገፋ ጋሪ ይጠቀማል። ምክንያቱም ትልቅ እቃ ጫኝ ተሽከርካሪ ለመግዛት ብድር ማግኘት አልቻለም። በዚህ ሁሉ ሥራዉ ከጎኑ የቆመና ፕሮጀክቱን የሚደግፍለት ትልቁ የዚምባቡዌ የቢራ ፋብሪካ ነዉ። ይህም ሆኖ ለዚህም ዚምባዌ ዉስጥ የተለመደ ሌላ ችግር ገጥሞታል።

«ባለፈዉ የከተማዉ ከንቲባ ይህን የእኔን ፕሮጀክት በመሠረዝ ለራሳቸዉ ለመሥራት መሞከራቸዉን ደርሼበታለሁ። ከዚህ ፕሬጀክት ለራሳቸዉ ገንዘብ ለማግኘት ማለት ነዉ። እንደመታደል ሆኖ የቢራ ፋብሪካዉ ከሌላ ጋ መሥራት እንደማይፈልግ ገልፆ ከእኔ ጎን መቆሙን አረጋገጠ።»

ችግሩ እዚህ ላይ ይጀምራል። የዚምባቡዌ ኤኮኖሚ በግልፅ ወድቋል ማለት ይቻላል። ባለፉት አራት ዓመታት ዉስጥ ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ሥራቸዉን አጥተዋል። ይህ ሁሉ ግን አዎንታዊ አመለካከት የታደለዉን ፓትሪክ ሚታንድዋን አልረበሸዉም። እንደዉም ስኬታማ ባለሃብት እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለዉ።

«ይህ ፕሮጀክት ረዥም ዘመን የሚዘልቅ ሥራ ነዉ። ከዕለት አንድ ቀን የልጅ ልጆቼ ይህን ኩባንያ ይረከቡታል። ከዚያ ደግሞ የእነሱ የልጅ ልጆች። ሰዎች እንዲህ የታሸጉ መጠጦችን መጠጣታቸዉን እስካላቆሙ ድረስ ይኼም ፕሮጀክት መኖሩን ይቀጥላል።»

Wirtschaft in Simbabwe
ምስል picture-alliance/ZB

ፓትሪክ ያገለገሉ ጠርሙስና ቆርቆሮዎችን ለዳግም ሥራ ከሚያመቻችበት አካባቢ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ራቅ ብሎ በዋና ከተማ ሀራሬ ዉስጥ በአትክልት ስፍራ የተዋበ አንድ ቤት አለ። በአትክልት ስፍራ ወንበሮች ላፕቶፓቸዉ ላይ ያተኮሩ ወጣቶች ቁጭ ብለዋል። «ሃይፐርከብ ሀብ» ይብላል ስፍራዉ። ለተከራዮቹ ሁለት ወሳኝ ነገሮችን ያቀርባል። ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎትና፤ የነፃ ቡና።

የዚህ ባለቤት ደግሞ የ25ዓመቱ ሻዉን ነዉ። ናሾ በተሰኘዉ በዚህ ድርጅቱ አማካኝነትም ድረገፆችን ለመክፈት፤ የኮምፕዩተር ፕሮግራሞችን መጫንና ከምንም በላይ በወቅቱ ዘመናዊ በሆኑት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይም ፕሮግራሞችን ይጭናል።

«እስከዛሬ ድረስ የተንቀሳቃሽ ስልክ የተለያዩ ፕሮግራሞችን መጠቀም ዚምባቡዌ ዉስጥ ያን ያህል የዳበረ አልነበረም። የተንቀሳቃሽ ስልክ የመገናኛ መስመር በጣም ጠገምተኛ ነበር። እናም ሰዎችም ስማርት የሚባሉትን የእጅ ስልኮች የመግዛት አቅም አልነበራቸዉም። ነገር ግን ከያዝነዉ ዓመት ጀምሮ በዚህ ዘርፍ አንዳንድ ነገሮች እየተሠሩነዉ። በሞባይላቸዉ ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እንዳደርግላቸዉ እጅግ በርካታ ጥያቄዎች ናቸዉ የሚቀርቡልን።»

ገና በ17ዓመቱ ነዉ ሻዉን የኮምፕዩተር ፕሮግራሞችን በግሉ ይሠራ የነበረዉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮምፕዩተር ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ከሚፈጥሩ አካላት ጋ የመሥራት እድልም አግኝቷል። ለዉጭ ኩባንያዎችም በግሉ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ሠርቷል። አሁን በሥሩ አራት ሠራተኞችን ቀጥሮ ዚምባብዌ ዉስጥ በመስኩ ጥሩ ሥራ እየሠራ ነዉ። ባለዉ እዉቀትና ችሎታ በአዉሮጳም ሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ያለምን ችግር ጥሩ ሥራ ማግኘት እንደሚችል የሚናገረዉ ሻዉን ከሁሉም በሀገሩ ቢሠራ እንደሚመርጥ ይገልፃል።

Wirtschaft in Simbabwe
ምስል DESMOND KWANDE/AFP/Getty Images

«ለእኔ ዚምባቡዌ ይሻለኛል፤ ምክንያቱም የግሌ መሆኑ ይሰማኛል። የማገለግላቸዉ ሰዎች አብሬያቸዉም የምሠራዉ ወገኖችን ስመለከት ረዥም ጊዜ ሳይወስድ የምጨብጠዉ የሆነ ነገር እየገነባሁ ያለሁ ይመስለኛል። የሀገሪቱን አቅጣጫ የመቀየር ኃላፊነት የወጣቶች ድርሻ ነዉ ብዬ አምናለሁ፤ በዚህ ዉስጥም የድርሻዬን ላበረክት እፈልጋለሁ።»

ምንም እንኳን ወጣቱ ባለሃብት ይህን መሰል እቅድና ፅናት ይዞ ቢሠራም ዚምባብዌ እንዲህ ያለዉን ሥራ ዉጤታማ ለማድረግ ቀላል አይደለም። ባንኮች ብድር አይሰጡም፤ እያንዳንዱን ወጪ በጥሬ ገንዘብ መክፈል ይኖርበታል። እንደሌሎች መሰል ሃገራት ሁሉ እንዲህ ያለዉ ቴክኒዎሎጂ ላይ ያተኮረ ሥራ ብዙም የተለመደ አይደለም። ሻዉን ግን በዚሁ ለመግፋት ወስኗል። ስኬት ካስመዘገበም የዘርፉ መንገድ ከፋች ለመሆን ይበቃል።

ያን ፊሊፕ ሽሉተር/ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ