1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የቀጠሉት ተቃውሞዎች ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል

ዓርብ፣ ጥር 18 2010

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ሳምንቱን ያሳለፉት በወቅታዊ ጉዳዮች ተጠምደው ነው፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የነበሩ ተቃውሞዎች ከፍተኛ ትኩረት ስቧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ኃላፊ በአንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግርም መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ዝግጅት የብዙዎች መወያያ ነበር፡፡

https://p.dw.com/p/2rYwG
Äthiopien Polizei
ምስል imago/Xinhua

በኢትዮጵያ የቀጠሉት ተቃውሞዎች ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል

የእስረኞች ፍቺ፣ የጥምቀት በዓል፣ የቴዲ አፍሮ የሙዘቃ ዝግጅት በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ የመደሰት እና የመዝናናት ስሜትን አረብቦ ነበር የከረመው፡፡ ይህ ስሜት ሳይቀዘቅዝ ነበር ከወደ ወልድያ የተለመደው አሳዛኝ የተቃውሞ እና ሞት ዜና የተሰማው፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም በጥምቀት ማግስት የሚውለውን የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር አደባባይ በወጡ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸው በአጭር ጊዜ ከዳር ዳር ተዳረሰ፡፡ 

ግጭቱ የተቀሰቀሰው በዓል አክባሪዎቹ እንዳይጨፍሩ በጸጥታ ኃይሎች ከተከለከሉ በኋላ መሆኑ ተነገረ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ የኢንተርኔት ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት በግጭቱ ምን ያህል ሰው እንደሞተ እና እንደቆሰለ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም ብዙዎች ሀዘናቸውን እና ቁጣቸውን ገለጹ፡፡ በማግስቱ የጸጥታ ኃይሎች ለቀብር ከወጡ ሰዎች ጋር መጋጨታቸው ብዙዎችን «የሰው ግድያ ማብቂያው የት እንደሆነ?» እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡ 

በተለይ የሰሜን ወሎ ዞን የፖሊስ ኃላፊ በክልሉ እና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀርበው የሰጡት ገለጻ ለብዙዎች ዋነኛ መነጋገሪያ ነው የሆነው፡፡ «ሰዎች መንግሥት ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንዴት በጥይት ለመቆጣጠር ይሞከራል?» ሲሉ የሞገቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል «ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?” ሲል ረቡዕ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ ባስነበበው ጽሑፉ ጠይቋል፡፡ 

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

“የጸጥታ ኃይሎች በወልድያ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት ግድያ በምንም ዓይነቱ መመዘኛ ከውግዘት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ በኃይል የሚፈታ ችግር እንደሌለ መንግሥት ራሱ ከማናችንም በላይ የሚያውቀው ነገር ነው፡፡ የዛሬውን መንግሥት የመሠረተው ኢሕአዴግ ወደ በረሓ እንዲገባ ያደረገው ደርግ ችግሮችን ሁሉ በውይይት ሳይሆን በኃይልና በኃይል ብቻ ለመፍታት በመፈለጉ መሆኑን በየግንቦት ሃያ በዓሉ ስንሰማው ኖረናል፡፡ ለሰው የሚጠላውን ኃጢአት ራሱ ከመሥራት በላይ ውድቀት የለም፡፡ በዓሉ የአንድ ቀን በዓል ነው፡፡ ቢታገሡት ያልፍ ነበር፡፡ ሌላ ችግር ይከሰታል ተብሎ ከተጠረጠረና መረጃ ከተሰበሰበ እንኳን አያሌ የችግር መፍቻ አማራጮች ነበሩ፡፡ ‹የጸጥታ ችግርም› ‹የጸጥታ ኃይሎች›ም እኛ ሀገር ብቻ አይደለም ያሉት፡፡ ባለ ሥልጣኖቻችንም ለልምድ ልውውጥ በየሀገሩ ሲሄዱ ነው የሚኖሩት፡፡ ምነው ታድያ የተሻለ አማራጭ መማር አቃታቸው?

እንዲህ ላሉ ችግሮችስ ጥይት መፍትሔ አለመሆኑን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ያለፈችበት ሁኔታ ብቻ እንዴት አያስተምረንም? ይልቅ ለምን የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ አንሠራም? ‹የሚያስለቅስ ነገር ነግሮ አታልቅስ ይለኛል› የሚል የትግርኛ አባባል አለ፡፡ ሕዝቡ ለምን ሆድ ባሰው? ወጣቶቹ ለምን ተቃወሙ? የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩስ ምንድን ነው? ብሎ መሥራት አይሻልም፡፡ ለምን ሕዝብን ከሕዝብ ወገንን ከወገን የሚያጋጭና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቂም እንዲቋጠር ይፈለጋል? ለምንስ የዘርና የጎሳ መልክ እንዲይዝ ይፈለጋል? ወንጀለኞችስ ለምንድን ነው በጎሳ ካባ ውስጥ እንዲደበቁ ሁኔታዎች የሚመቻቹት? ከመሬት መንቀጥቀጡ (shock) በላይ ድኅረ መንቀጥቀጡ (aftershock) ውጤቱ የከፋ መሆኑን አናውቅምን? ችግሩንስ ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?”

የማነ ምትኩ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም ተመሳሳይ ይዘት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡  “በዓል ነው። በዓሉ በየቤትህ ተቀምጠህ የምትፈስክበት ዓይነት አይደለም። ማህበራዊ በዓል ነው። ሰው ተሰብስቦ ያከብረዋል። አጋጣሚውን ተጠቅመው የታፈኑ ድምፆች ይደመጡበታ። የግድ ነው። አፈና በበዛበት ስርዓት ህዝብ እነዚህን አጋጣሚዎች ይጠቀማል። አጋጣሚውን ተጠቅሞ ህዝብ ብሶቱን ሲገልፅ መሰማት ነበረበት። ለመሆኑ [ኢህአዴግ]፥ ህገመንግስታዊ መብታቸውን ማክበርስ ተወው፡፡ የተሰበሰብን ሁሉ በጥይት በትነህ እስከመቼ ትዘልቀዋለህ? አስለቃሽ ጭስ፥ ውሃ፥ ወዘተ የሚባሉ ሰልፍ በታኝ ነገሮችን መጠቀም የምትጀምረው መቼ ነው? ጥይትስ ቢሆን ለማስፈራራት ወደ ሰማይ ይተኮሳል እኮ? አስር የተኩስ እሩምታ ከተሰማ ዘጠኝ የሚወድቀው እስከመቼ ድረስ ነው? ይህ እኮ ጦር ሜዳ አይደለም፡፡ ከዜጎች ህይወት ይልቅ ጥይት እንዳይባክን መጨነቅህ ለምን ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ዮናስ ሐጎስ በበኩላቸው “በወልድያው ተቃውሞ እንደታየው አይነት በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መዘዙ ብዙ ነው” የሚል መልዕክት ያዘለ ጽሁፍ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ “መንግስትንና ስርዓትን መቃወም አንድ ነገር ነው። ተቃዋሚዎች ፖሊስ ጣቢያ ሊያጠቁ፣ የመንግስት ተቋማትን ሊያጠቁ ይችላሉ። ይሄ በየትኛውም ዓለም ላይ በሚካሄድ ተቃውሞ የተለመደው አሰራር ነው። ግን የሰውን ስም እየለዩ በብሔር ብቻ ተንተርሰው የግለሰብ መኖርያዎችንና የንግድ ተቋማትን ማጥቃት ሲጀመር መንገዳችን ወዴት እንደሆነ በግልፅ እያሰመርን መሆኑ ይታወቅ። በሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የመንግስት አሊያም የስርዓት ተቃውሞ ሳይሆን የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ደወል ነው። ይሄ ፍጥጥ ያለ ሐቅ ነው” ብለዋል፡፡ 

ጉደታ ገለልቻም “ነገሮች እንዳይወሳሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል” በሚል ርዕስ ተከታዩን ማሳሰቢያ ረቡዕ ዕለት በፌስ ቡክ አስተላልፈዋል፡፡ “ሰሞኑን በአማራ ክልል ወልዲያ አካባቢ በደረሰው አሰቃቂ ግድያዎች ምክኒያት ከደረሰብን ጥልቅ አዘን ሳናገግም ሌላ ግድያ በኦሮሚያ ክልል መቂ አካባቢ መፈፀሙን ሰማን! በጣም ያሳዝናል በጣምም አዝነናል! ጎበዝ ምን ይሻላል? ነገሮቻችን አንድ እርከን ወደ ፊት ይጎዙና ሁለት እርከን ወደ ኋላ ይመለሳሉ! የትግላችን አቅጣጫ ጠራ ብለን ሰናበቃ ነገሮቹ ተመልሰው ይወሳሰቡብናል! ለማንኛውም ማንም ሆነ ማን ከፌዴራልም ሆነ ከክልል ውድ የሰው ልጅ ላይ አነጣጥሮ በመተኮስ የሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳት ያደረሱት አካላት ጉዳያቸው ተጣርቶ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ለመሳሰብ እንወዳለን!”

አቶ ጉደታ እንደጠቀሱትም በመቂ አቅራቢያ ባለችው የዓለም ጤና ከተማ ማክሰኞ ዕለት ሰዎች መገደላቸው በማኅበራዊ መገናኛዎች መረጃው ተሰራጭቷል፡፡ የዓለም ጤናው ክስተት መነሾ በከተማይቱ ያሉ ተማሪዎች በወልድያ እና ሰኞ ዕለት በሞያሌ የሞቱ ሰዎችን ለመዘከር ሲሞክሩ ነው ተብሏል፡፡ በቆቦ ከተማም እንዲሁ በወልድያ ሰዎች መገደላቸውን የተቃወሙ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ሀዘንን አስከትሏል፡፡ በቆቦ ረቡዕ የተጋጋለው ተቃውሞ እና ግድያው ሐሙስም ቀጥሎ እንደዋለ በቪዲዮ እና ፎቶ ጭምር ተደግፈው በማህበራዊ ድገጾች የተሰራጩ መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ 

Äthiopien Adama - Oromia TV headquarter
ምስል Tesfalem Waldyes

በኢትዮጵያ አልበርድ ያለው የተቃውሞ እና የሰዎች ሞት በሀገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሃንን እና ባለስልጣናትንም ለውይይት በአዳራሽ አሰባስቦ ነበር፡፡ «በወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ የብሮድካስት ሚዲያ አዝማሚያ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይሄው ውይይት የተካሄደው ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ኃላፊ አቶ ዘርዓይ አስገዶም በውይይቱ ወቅት የሰነዘሩት ሀሳብ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አቶ ዘርዓይ በውይይቱ መገናኛ ብዙሃንን በስም እየጠሩ እንዲህ ወርፈዋል፡፡ 

“ከቴሌቪዥን ሁሉም ሞኒተር ያደረግናቸውን እዚህ ማቅረቡ ሌላ ትርጉም እንዳይሰጠው ስጋት አለኝ፡፡ አንዳንዶቹን ላቅርብ፡፡ ከሚሊኒየም አዳራሽ በቅርቡ የተላለፈው የኦሮሞ ወጣት ተነስ እና አዲስ አበባ አራት ኪሎ ግባ የሚለው የሃጫሉ [ሁንዴሳ] ዘፈን እንዴት በቀጥታ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይተላለፋል?  ጸረ- ህዝብ የሆነ ዘፈን ነው፣ የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር የሚያጋጭ ነው፡፡ ዘፈኑ ፈረስህን ቀልብ፣ ተዘጋጅ፣ ታጠቅ፣ አራት ኪሎ ግባ ነው፡፡ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ቀጥታ ለቀቀው፡፡ በነጋታውም ደገመው፡፡ ያ ዘፈን ሲለቀቅ ከፍተኛ ስጋት ነው የፈጠረው፡፡  

አማራ ቴሌቪዥን የወልቃይት እና የጎንደርን ጉዳይ እንዴት ነው የዘገበው? ምን ያህል ጊዜ ነው የዘገበው? ጎንደሬዎች መቀሌ ሄደው [ትግሬዎችን] መልሱልን ሲሉ ለምንድነው ያልዘገበው? ተዘጋጅቶ ተልኮለት እያለ፡፡ ባንዲራ ሲቃጠል ምን ሰራ የአማራ ቴሌቪዥን ?ህገመንግስት ሲቃጠል ማለት ነው በሌላ አነጋገር፡፡ በትልቁ ኢቢሲ ሞኒተር አድርገን የተረዳነው ኢቢሲ ሀገር ስትበጣበጥ የዳር ተመልካች ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ መረጃ አይሰጥ፣ ወይ አይተነትን፡፡ ሁነቶችን ብቻ ነበር ሲዘግብ የነበረው” ሲሉ አቶ ዘርዓይ ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።

ይህን አመልክተው በማኅበራዊ መገናኛዎች ከተሰጡ አስተያየቶች፤ ኡቱባ ጋዲሳ በፌስ ቡክ “የሃጫሉን ዘፈን ለማስተርጎም የወጣችው በጀት መቶ ሺህ ትሆናለች” በማለት በቀልድ ይንደረደራሉ፡፡ “ወጣቱ የተመከረው አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ እንዲገባም ነው፡፡ ቄሮ ተምሮ ሀገሩን እንዲያሻሽል ነው” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አሞን ግርማ በበኩላቸው “አቶ ዘርዓይ አስገዶም በእኛ ግምገማ  ሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ የድሮዋን ኢትዮጵያ፣ የጠፋችውን ነው የሚመስለው፡፡ ያሁኗ ኢትዮጵያ እንዳልጣማቸው በግልጽ ነው የሚታየው ብለዋል፡፡ እኔ ደግሞ ያሁኗ ኢትዮጵያ እንዳልጣመችን ስላወቁልን ብቻ ደስታችን የላቀ ነው” ሲል ተሳልቋል፡፡ የጋዜጠኝነት መምህሩ ዳግም አፈወርቅ “የሸገር ጥፋቱ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አብዝቶ መጨነቁ ነው” ብሏል፡፡ ስለ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እና ኃላፊው ደግሞ በፌስ ቡክ ገጹ ተከታዩን ጽፏል፡፡

“በቅርቡ በባለስልጣኑ የሚሰጡ መግለጫዎች የሚዲያ ህጎችን እየጠቀሱ የሚዲያዎችን ጥፋት ከመዘርዘር ይልቅ ማስፈራሪያ ይበዛባቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የተለመደውን አይነት ህጋዊ ሳይሆን አስተዳደራዊ እርምጃ (administrative measures) ለመውሰድ እያኮበኮቡ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ጋዜጠኛ በስራው በሚታሰርባት እና በሚሰደድባት ሀገር፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ሀላፊዎች የህዝቡን የማወቅ መብት (the public’s right to know) ከቁብ ሳይቆጥሩ ጋዜጠኞችን መረጃ በሚከለክሉባት ሀገር፣ ነፃ ድምፆች እየጠፉ የመንግስት ሚዲያ እና የመንግስት ተቆርቋሪ ሚዲያ በበዛባት ሀገር ባለስልጣኑን የሚያስጨንቀው ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግር በሚዲያዎች መዘገቡ ነው፡፡ ያሳዝናል!!! በፖለቲከኛ ሳይሆን በባለሙያ የሚመራ፣ ለፓርቲ ወይም ለመንግስት ጥቅም ሳይሆን የህዝብን የማወቅ መብት ለማስከበር የቆመ፣ በሚዲያ ላይ ያለው የመንግስት ጠቅልሎ የመያዝ (government monopoly) ቀንሶ ወይም ጠፍቶ ነፃ ድምፆች እንዲበዙ የሚሰራ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲኖር እመኛለሁ” ሲል ደምድሟል፡፡ 

የሕግ ባለሙያው በትሩ ዲባባ  በሕገ መንግስቱ የፌደራል መንግሥት ስልጣን እና ተግባር በተዘረዘረበት አንቀጽ 51 የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን በግልጽ አለመጠቀሱን በፌስ ቡክ ጽሁፉ አንስቷል፡፡ “ከህዝብ የተሰረቀ ስልጣን፣ የግለሰብ ስልጣን ነው” ሲል የሚከራከረው በትሩ ስለ ባለስልጣኑ እንዲህ ይላል፡፡ “የብሮድካስቲንግ ስልጣን የክልሎች ስልጣን ነው። ታዲያ በፌዴራል ደረጃ እራሱን 'ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን' ብሎ የሚጠራው አመጣጡና አመሰራረቱ ሕገ መንግስታዊ መሰረት የለውም። ከክልሎች የተሰረቀ ስልጣን ነው። የተሰረቀ ስልጣን ብቻም ሳይሆን ክልሎች ላይ ስልጣን አለኝ ይላል፡፡ ‘እንዲህ ብለህ ፃፍ፤ እንዲህ ካልተናገርህ’ ይላል። ከባዶ ተነስተው ወቃሽ!”  ሲል ይተቻል፡፡

Artist Thewodros Kasahun
ምስል CD Album Foto Via Mantegaftot Sileshi

የዛሬው መሰናዷችንን የምንቋጨው በድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጉዳይ ይሆናል፡፡ አዲሱን አልበሙን ካወጣ ወዲህም ሆነ ላለፉት አራት ዓመታት በሀገር ውስጥ የሙዚቃ ዝግጅት እንዳያካሂድ ተከልክሎ የነበረው ቴዲ አፍሮ ባለፈው እሁድ በባህር ዳር ከተማ አድናቂዎቹን በሥራው አዝናንቷል፡፡ የሙዚቃ ዝግጅቱ በዋዜማው በወልድያ የተከሰተው ግጭት እና ሞት ጥላ አጥልቶበታል፡፡ የተወሰኑ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እንደውም ቴዲ በሀዘኑ ምክንያት የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲሰርዝ እስከመጠየቅ ተጉዘዋል፡፡ ይህን የታዘበ የመሰለው ጸሀፌ ተውኔቱ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ሁኔታውን በራሱ በድምጻዊ እውቅ ዘፈን ርዕስ “እያነቡ እስክስታ” ሲል ገልጾታል፡፡ 

ብዙ የተባለለት የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ዝግጅት በሰላም ቢጠናቀቅም በማኅበራዊ ድረገጾች የመነታረኪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የንትርኩ ማጠንጠኛ ደግሞ ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን “ጃ ያስተስርያል የሚለውን ዘፈኑን ለምን በመድረክ ሳይጫወት ቀረ” የሚል ነው፡፡ ብሌን መስፍን ይህን ስሜት የሚያንጸባርቅ ጽሁፏን በፌስ ቡክ አካፍላለች፡፡  

“ቴዲን ከሌሎች ዘፋኞች ልዩ ያደረገው በድፍረት ይሄንን ስርዓት መናገር መቻሉና ታሪክን ማውሳቱ ነው። ደፍሮ ይሄንን ስርዓት በዋናነት የነቀፈበት ዘፈኑ ደግሞ ‘ጃ ያስተሰርያል’ ነበር፡፡ የታወቀበትን፣ የተገፋና የታፈነ ሕዝብ ልብ ውስጥ ዙፋን ያሰጠውን ይሄን ዘፈን በልመና እንኳ መዝፈን የተሳነው ለምን ይሆን? "የሕዝብ" ልጅ ቴዲ፣ ልቡ ለደማው ሕዝብ፣ በአንድ ዘፈን ሊያውም በራሱ ዘፈን የእናንተው ነኝ ቢል ምን ነበረበት? ለ‘ማራኪዬ’ እና ለ‘ሳማት ሳማት አለኝ’ ሚሊኒየም አዳራሽ ጥጋብ ልባቸውን ያሳበጣቸውን ባለጊዜዎች ማስጨፈር ማን ከልክሎት፡፡ ወገኑ እየረገፈ ዳንኪራ አምሮት የሄደ የለ፤ የልቤን ይናገርልኛል ብሎ እንጂ” ስትል ጽፋለች።

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ