1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንሶዎች «የታሰሩ ይፈቱልን »ጥያቄ

ሰኞ፣ ሰኔ 18 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፈዉ ጥር ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሺህ የሚቆጠሩ ታሳሪዎችን እየፈታ ይገኛል። ይሁን እንጅ በደቡብ ክልል በኮንሶ ወረዳ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ «የሽብርተኝነት» ክስ ተመስርቶባቸዉ ከታሰሩት የብሄረሰቡ አባላት መካከል አንድም ሰዉ አለመፈታቱ ቅሬታ አሳድሮብናል ይላሉ አንድ የአካባቢው ተወካይ።  

https://p.dw.com/p/30F6i
Konso
ምስል by-nc-sa/Terri O'Sullivan

Complaint in« Konso» District - MP3-Stereo

በደቡብ ክልል በኮንሶ ወረዳ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ «የሽብርተኝነት» ክስ ተመስርቶባቸዉ ከታሰሩት የብሄረሰቡ አባላት መካከል «አሁንም ድረስ አንድም ሰዉ አለመፈታቱ ቅሬታ አሳድሮብናል » ሲሉ አንድ የአካባቢዉ ተወካይ ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል። በአካባቢዉ ወከባና እስር አሁንም ድረስ ቀጥሎ እንደሚገኝ ነዋሪዉ ጨምረዉ አመልክተዋል።  ለደህንነታቸዉ በመስጋት ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአካባቢዉ ተወካይና የሀገር ሽማግሌ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት በደቡብ ክልል የምትገኘዉ ኮንሶ  ከዚህ ቀደም ተጠሪነቷ ለክልሉ መንግሥት ሆና የምትተዳደር ልዩ ወረዳ ነበረች። ይሁን እንጅ ከመጋቢት 2003 አ/ም ጀምሮ ልዩ ወረዳነቷ ቀርቶ « በሰገን አካባቢ ህዝቦች» አስተዳደር ስር ተካታ ተጠሪነቷ ለዞን እንዲሆን መደረጉን ነዉ ያመለከቱት። ይህ ጉዳይ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብትን ይጋፋል በሚል ተቃዉሞ በ2008 አ/ም የኮንሶ ሕዝብ የ81 ሺህ ሶዎችን ፊርማ በማሰባሰብ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁሞ ለክልልና ለፌደራል መንግሥት አቤቱታ አቅርበዉ እንደነበር አስታዉሰዋል።  ይሁን እንጅ ለጥያቄዉ የተሰጠን ምላሽ «አመፅ አነሳስታችኋል »በሚል ኮሚቴዎቹን ለማሰር በመሞከሩ፤ የአካባቢዉ ኅብረተሰብ የኮሚቴዎቹን ዉክልና በማንሳት ሌላ 23 አባላት ያሉት ኮሚቴ በመንግሥት መቋቋሙን ገልፀዋል። ያምሆኖ ግን መልስ ከመስጠት ይልቅ ካላ ገዛኸኝ የተባሉ የጎሳ መሪን ጨምሮ በርካታ ሰዎች «በሽብር ክስ» ለእስር መዳረጋቸዉን ነዉ ያመለከቱት። የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃም በወቅቱ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።
እንደ ተወካዩ ገለፃ በእኝህ የጎሳ መሪ መዝገብ የተከሰሱትን 43 ተከሳሾች ጨምሮ 467 ሰዎች ላለፉት 2 አመታት በኮንሶ ፣ በጊዶሌ፣ በአርባ ምንጭና በተለያዩ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ታስረዉ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከመንግሥት የሥራ ገበታቸዉ የተባረሩ ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ፤ ከሀገር የተሰደዱ ፤ የተገደሉና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸዉ መኖራቸዉን ይናገራሉ።
መንግሥት በመላዉ ሀገሪቱ ታሳሪዎችን እየለቀቀ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት መብታቸዉን በመጠየቃቸዉ ብቻ የኮንሶ ተወላጆች አሁንም ድረስ ክሳቸዉ ቀጥሎ እስር ላይ መሆናቸዉ «እኛ ኢትዮጵያዉያን አይደለንም ወይ »የሚል ቅሬታ በአካባቢዉ ነዋሪዎች ዘንድ መፈጠሩንም የሀገር ሽማግሌዉ ያመለክታሉ።
ጉዳዩን በተመለከተ ከ42ቱ የኮንሶ ቀበሌዎች የተዉጣጡ የአካባቢዉ ሽማግሌዎች በድጋሚ ለመንግሥት አቤቱታ ቢያቀርቡም መልስ አለመገኘቱን ነዉ የገለፁት። ይልቁንም «መብታችን ይከበርና የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ »ጥያቄ በማቅረባችን በአካባቢዉ የፀጥታ ኃይሎች ወከባ ማስፈራሪያና እስር እየደረሰብን  ነዉ ያሉት። በሀገሪቱ ለዉጥና ማሻሻያ እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኮንሶ እስር፤ ማስፈራራትና ማንገላታት መቀጠሉ አሳዛኝ መሆኑን አመልክተው መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸዉ ተወካዩ ጠይቀዋል። ጉዳዩን በተመለከተ የክልሉን ቃል አቀባይ ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson
Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ

ሸዋዬ ለገሠ