1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኦሮሚያ ክልል የ122 ኩባንያዎች ፈቃድ ሰረዘ

ረቡዕ፣ የካቲት 7 2010

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የ122 ኩባንያዎችን የሥራ ፈቃድ መሰረዙን አስታውቋል። ሌሎች 200 ገደማ ኩባንያዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/2shx8
Äthiopien, Adama
ምስል DW/M. Yonas Bula

የኦሮሚያ ክልል የ122 ኩባንያዎች ፈቃድ ሰረዘ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የ122 ኩባንያዎችን የሥራ ፈቃድ መሰረዙን አስታውቋል። ሌሎች 200 ገደማ ኩባንያዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቡሌ አበጋዝ ናቸው።ኩባንያዎቹ የፈጸሟቸው ጥፋቶች በርካቶች ናቸው ብለዋል። አቶ አቡሌ የቃል እና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው  እንደነበርም አንስተዋል። በፈቃዳቸው መሠረት የተሰጣቸውን ቦታ ለሁለተኛ እና ሦስተኛ ወገን ያስተላለፉም ይገኙበታል። አብዛኞቹ የግንባታ ግብዓቶች በማምረት ዘርፍ የተሰማሩ እንደነበሩም ኃላፊው ጠቁመዋል። 
አቶ አቡሌ አበጋዝ ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው መካከል ከጥበቃ እስከ አስተዳደር ባሉ የሥራ እርከኖች በውጭ አገር ባለሙያዎች ሥራውን ሲያከናውን የነበረ ኩባንያን በምሳሌነት በመጥቀስ የችግሩን ውስብስብነት አስረድተዋል። ባለሙያው እንደሚሉት በኢትዮጵያዊ ስም በተከፈተው ኩባንያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞች የሥራ ፈቃድ ጭምር አልነበራቸውም።
የሥራ ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው አብዛኞቹ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ናቸው።  አቶ አቡሌ እርምጃው የዘገየ እንደሆነ ይናገራሉ። ተቋማቱ ባለባቸው የአቅም ውስንነት ኩባንያዎቹ በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ሥራ መስራታቸውን እንዳልተከታተሉ ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እርምጃ ሲወስድ ከፌድራል ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ መሆኑን አቶ አቡሌ አበጋዝ ተናግረዋል። 

ሙሉ መሰናዶውን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ
እሸቴ በቀለ 
ሸዋዬ ለገሠ