1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የእስራኤል እና የኢራን ቁርቁስ ወዴት ያመራል?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

የኢራን እና የእስራኤልን ቁርቁስ በአንክሮ የሚከታተሉ ጉምቱ ዲፕሎማቶች እና ተንታኞች መካከለኛው ምሥራቅን የሚያዳርስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ሰግተዋል። በደማስቆ የተፈጸመ ጥቃት የሁለቱን ሀገራት የበርካታ አስርት ዓመታት የእጅ አዙር ፍልሚያ ገሀድ ቢያወጣውም በመካከላቸው በቂ ቂም እና አለመተማመን አለ።

https://p.dw.com/p/4f0oi
የእስራኤል ጸረ-ሮኬት ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳይሎቾ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሊያከሽፍ
በደማስቆ በተፈጸመ ጥቃት በኋላ ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳይሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ወደ እስራኤል ስታስወነጭፍ በቀጠናው ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት በርትቶ ነበር። ምስል Amir Cohen/REUTERS

ማሕደረ ዜና፦ የእስራኤል እና የኢራን ቁርቁስ ወዴት ያመራል?

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል የመካከለኛው ምሥራቅን ፍጥጫ ከቼዝ ጨዋታ ያመሳስሉታል። “አንዱ ሌላውን ያጠቃል፤ የተጠቃው ይመልሳል። እንደገና ሌላው ይመልሳል” ሲሉ የ76 ዓመቱ ዲፕሎማት የኢራን እና የእስራኤልን ፍጥጫ ይገልጹታል።

ጆሴፕ ቦሬል ባለፈው ሣምንት በቡድን ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ለመሳተፍ ከጣልያኗ ካፕሪ ደሴት ሲደርሱ “በዚህ ጨዋታ የእያንዳንዱ እርምጃ፤ የምላሹ ደረጃ እየጨመረ ከሔደ በጨዋታው መጨረሻ ሙሉ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” የሚል ሥጋታቸውን ገልጸው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተመሳሳይ ሥጋት እንደተጫናቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ዋና ጸሀፊው ባለፈው ሣምንት በጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “መካከለኛው ምሥራቅ ከገደል አፋፍ ላይ ነው። በቃላት እና በተግባር ባለፉት ጥቂት ቀናት አደገኛ ማባባስ ታይቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

ጉቴሬዝ “አንድ የተሳሳተ ስሌት፣ አንድ የተሳሳተ ግንኙነት፣ አንድ ስህተት ሊታሰብ ወደማይችል የለየለት ቀጠናዊ ጦርነት ሊመራ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የለየለት ጦርነት ቢቀሰቀስ “ለተሳታፊዎቹ እና ለመላው ዓለም አውዳሚ ይሆናል” ያሉት ዋና ጸሀፊው “አደገኛ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት መሆን አለበት” የሚል ምክር ለግሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “አንድ የተሳሳተ ስሌት፣ አንድ የተሳሳተ ግንኙነት፣ አንድ ስህተት ሊታሰብ ወደማይችል የለየለት ቀጠናዊ ጦርነት ሊመራ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ምስል Charly Triballeau/AFP/Getty Images

በጋዛ ጦርነት የተቀሰቀሰውን ውጥረት ወደባሰ ቀውስ የገፋው የእስራኤል እና ኢራን ግብግብ ነው። በሶርያ ዋና ከተማ ደማስቆ በሚገኝ የኢራን ቆንስላ ላይ የተፈጸመው እና የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች የተገደሉበት ጥቃት ሁለቱን ባላንጦች በቀጥታ ወደ ግጭት ይምራቸው እንጂ ለዘመናት የዘለቀ በቂ ቂም እና አለመተማመን በመካከላቸው ይገኛል።

በቻታም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ሳናም ቫኪል “በእስራኤል እና በኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ሲጋጩ የታዘብንበት በመሆኑ ይኸ አደገኛ ወቅት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ይኸ ግጭት ለበርካታ ዓመታት ከጀርባ በጦርነት ጥላ ሥር ሲካሔድ የቆየ ነው። አሁን ግጭቱ ከሸፈነው ጥላ ወጥቷል” የሚሉት  ሳናም ቫኪል “ግጭቱ በመላ ቀጠናው ሊስፋፋ፣ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ሀገራትን ሊያሳትፍ ይችላል” የሚል ሥጋት አላቸው።

ኢራን እና እስራኤል ባላንጦች ከመሆናቸው በፊት ወዳጆች ነበሩ። እስራኤል እንደ ሀገር ስትቆም ዕውቅና ከሰጡ ቀዳሚ ሀገራት አንዷ ኢራን ስትሆን  ሁለቱ ወታደራዊ እና የደሕንነት ትብብርም ነበራቸው።

በጎርጎሮሳዊው 1979 የተካሔደው የኢራን አብዮት ግን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በአፍጢሙ ደፋው። የኢራኑ ሻሕ ሞሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ተባረው ሥልጣኑን የተረከቡት አያቶላ ሩሆላሕ ኾሚኒ “ዕብሪተኛ” የሚሏቸው የዓለም ኃያላን በጽኑ የሚቃወሙ ነበሩ።

በኾሚኒ ዘመን አሜሪካን “ትልቅ” እስራኤል “ትንሽ ሴይጣን” እየተባሉ ይጠሩ ነበር። በ1980ዎቹ የሁለቱ ሀገሮች ትብብር እጅግ ቢቀዛቀዝም ቀስ በቀስ ግን በመካከላቸው ጠላትነት የተጫነው ፉክክር ሥር እየሰደደ ነበር።

የኢራን አብዮት አያቶላ ሖሚኒ
ኢራን እና እስራኤል ጠበኛ የሆኑት በጎርጎሮሳዊው 1979 ከተካሔደ የኢራን አብዮት በኋላ ነው። ምስል picture-alliance/dpa/AFP/G. Duval

የኢራን የኑክሌር ግንባታ መርሐ-ግብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን አለመተማመን እና መጠራጠር አካሮ አይን እና ናጫ ያደረጋቸው ጉዳይ ነው። ኢራን የኑክሌር ግንባታ መርሐ-ግብሯ ሙሉ በሙሉ ለሰላማዊ ግልጋሎት የሚውል እንደሆነ በተደጋጋሚ ብትገልጽም ማብራሪያው በእስራኤል በኩል ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። የኢራን የኑክሌር ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ከመርሐ-ግብሩ ግንኙነት ያላቸው ሁሉ የእስራኤል ጥቃት ዋንኛ ዒላማ ሆነው ቆይተዋል።

ኢራን በእስራኤል እና በአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ታጣቂ ቡድኖችን በሶርያ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና የመን ትደግፋለች እየተባለች ትወነጀላለች። በ1980ዎቹ የተመሠረተው ሒዝቦላሕ በደቡባዊ ሊባኖስ ከእስራኤል ጋር የሚዋጋ ነው። በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ መስከረም 26 ቀን 2016 ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ሒዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶች ይተኩሳል።

ኢራን የሶርያው ፕሬዝደንት ባሽር አሳድን መንግሥት ስትደግፍ እስራኤል በተደጋጋሚ ጎረቤቷን በጦር ጄቶች እና ሚሳይሎች ትደበድባለች። ኢራን በሶርያ በኩል ለሒዝቦላሕ የጦር መሣሪያ ታቀርባለች ስትል እስራኤል ትወነጅላለች።

በእስራኤል ላይ በመስከረም መገባደጃ የተፈጸመውን ጥቃት በዋንኛነት በመምራት እና በማስተባበር የሚወነጀለው ሐማስ ሌላው በኢራን የሚደገፍ ታጣቂ ቡድን ነው። በእስራኤል መንግሥት መረጃ መሠረት መስከረም 26 ቀን 2016 በተፈጸመው ጥቃት ከ1 ሺሕ 200 በላይ እስራኤላውያን ሲገደሉ ከ200 በላይ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።

እስራኤል በጋዛ የምታካሒደውን ወታደራዊ ዘመቻ በመቃወም ከፍልስጤማውያን ጎን የቆሙት የሑቲ ታጣቂዎች በኢራን የሚደገፉ ናቸው። ሰንዓ፣ ሰሜን ምዕራብ የመን እና የሀገሪቱን የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የሚቆጣሩት ሑቲዎች እስራኤል፣ አሜሪካ እና ምዕራቡን ዓለም ለመቋቋም ሐማስ እና ሒዝቦላህ ያበጁት ጥምረት (Axis of Resistance) አባል ናቸው። ሑቲዎች በቀይ ባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው ኤይላት የተባለች ከተማ ሮኬቶች የተኮሱ ሲሆን ከእስራኤል ግንኙነት አላቸው ባሏቸው መርከቦች ላይም ጥቃት ፈጽመዋል።

በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የወደመችው የኻን ዩኒስ ከተማ
እስራኤል በጋዛ በምታካሒደው ወታደራዊ ዘመቻ ከ34 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን እንደ ኻን ዩኒስ ያሉ ከተሞችን አውድሟል። ምስል Ali Jadallah/Anadolu/picture alliance

ከስድስት ወራት በላይ ባስቆጠረው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከ34 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። በጋዛ የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች በእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሆነው ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የጋዛ ነዋሪዎች ከግብጽ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ራፋሕ ተፈናቅለዋል። እንዲያም ሆኖ እስራኤል ሐማስን “ለማጥፋት” ያቀደ የምትለው ወታደራዊ ዘመቻ እስካሁን አልቆመም። ጋዛ ፈርሳ ነዋሪዎቿ ለኃይለኛ ሰብአዊ ቀውስ ቢዳረጉም እስራኤል ዘመቻዋን በራፋሕ የመቀጠል ውጥን አላት።

የጋዛ ቀውስ መፍትሔ ሳያገኝ ኢራን እና እስራኤል የገቡበት ቁርቁስ ለፍልስጤም ሰዎች በጎ ዜና አይደለም። የቻታም ሐውስ ባልደረባ የሆኑት ሳናም ቫኪል “ውይይቱ እጅግ በጣም ከጋዛ ጉዳይ ተቀይሯል። በጋዛ የሚካሔደው ጦርነትም ቀጥሏል። በጋዛ ረሐብ እንዳለ አሁንም ሪፖርት ይቀርባል። ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረግ ድርድር የለም” ሲሉ የእስራኤል እና የኢራን ፍጥጫ የዓለምን ትኩረት እንዳናጠበ አስረድተዋል።

ሳናም ባኪል “አደገኛ” የሚሉት ወቅት ላይ የተደረሰው በሶርያ ዋና ከተማ ደማስቆ በሚገኝ የኢራን ቆንስላ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሳቢያ ነው። የደማስቆው ጥቃት የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሁለት ወራት በፊት የታቀደ በመጨረሻም የእስራኤል የጦርነት ጊዜ ካቢኔን ይሁንታ ያገኘ ወታደራዊ ተልዕኮ ነበር።

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫንን ጨምሮ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢራን አብዮታዊ ዘብ ሥር የሚገኘው የቁድስ ኃይሎች የሶርያ እና የሊባኖስ ክንፍ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሞሐመድ ረዛ ዛሔዲ እና ምክትላቸው የተገደሉበትን ጥቃት ሊፈጸም መሆኑ ከእስራኤሎች የተነገራቸው በመጨረሻው ሰዓት እንደነበር ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጥቃት የተፈጸመበት በደማስቆ የኢራን ቆንስላ
በደማስቆ የኢራን ቆንስላ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ተገድለዋልምስል MAHER AL MOUNES/AFP

እስራኤል በይፋ ኃላፊነት ባትወስድም ኢራን “ሁሉንም ዓለም አቀፍ ግዴታዎች እና ሥምምነቶች የጣሰ” ላለችው ጥቃት ከመወንጀል አላመለጠችም። በደማስቆ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ እስራኤል ብቻ ሳትሆን የቅርብ አጋሯ አሜሪካ ጭምር ለኢራን ምላሽ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ነበሩ። 

ከጥቃቱ በኋላ በተደረጉ ውይይቶች የተሳተፉ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “ኢራን ጠንከር ያለ ምላሽ አትሰጥም የሚል የተሳሳተ ስሌት” ከእስራኤል ዘንድ ነበር። የኢራን ግብረ-መልስ የማይቀር እንደሆነ አሜሪካ እና እስራኤል ከተገነዘቡም በኋላ ቢሆን ጥቃቱ ምን ያክል ብርቱ ይሆናል የሚል ግምታቸውን ደግመው ደጋግመው ለመከለስ ተገደዋል።

መጋቢት 23 ቀን 2016 የተጠበቀው የኢራን የአጸፋ እርምጃ ዝግ ብለው በሚበሩ 185 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተጀመረ። ከዚያ ክሩዝ ሚያሳይሎች ተከተሉ። ከሁሉም አስቸጋሪ የነበሩት በድምጽ ፍጥነት የሚወነጨፉት 110 የኢራን ባሊስቲክ ሚሳይሎች ናቸው።

አብዛኞቹ የኢራን ሚሳይሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ እስራኤል የአየር ክልል ከመግባታቸው በፊት በአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስ የጦር ጀቶች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶች እየተመቱ ከሽፈዋል። ወደ እስራኤል የገቡትም ቢሆን በአንድ ወታደራዊ የጦር ማረፊያ ላይ ያደረሱት ጉዳት አነስተኛ ነበር።

ኢራን ጥቃቱ “አነስተኛ ጉዳት ለማድረስ” የታቀደ እንደነበር ብትገልጽም ወደ እስራኤል ያስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአሜሪካ የጦር ጄቶች እየተመቱ መክሸፋቸው ግን አልተዋጠላትም።

ኢራን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈችው ሚሳይል ቅሪት
ኢራን ወደ እስራኤል ካስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች አብዛኞቹ በጦር ጄቶች እና የአየር መከላከያ እየተመቱ ከሽፈዋል። ምስል Tsafrir Abayov/AP/picture alliance

በእስራኤል ጥያቄ በተካሔደው የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ስብሰባ “ኢራን በቀጠናው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የመጋጨት ፍላጎት የላትም” ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የኢራን አምባሳደር አሚር ሳዒድ ኢራቫኒ “የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በበኃይል በተያዘው የፍልስጤም ግዛቶች በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ያነጣጠሩ የኢራን ድሮኖች እና ሚሳይሎችን ጣልቃ በመግባት ሲያከሽፍ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰድ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት አሳይተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ይኸ ውጥረቱን ለማርገብ እና የግጭቱን መስፋፋት ለማስወገድ ያለንን ጽናት ያሳያል። ይሁንና ዩናይትድ ስቴት በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ዜጎቿ እና የጸጥታ ፍላጎቷን ለመጠበቅ ኢራን ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት ተፈጥሯዊ መብቷን ትጠቀማለች” ሲሉ የኢራን አምባሳደር ተናግረዋል።

አሜሪካ በደማስቆ የተፈጸመውን ጥቃት በዝምታ ብታልፍም የኢራንን የአጸፋ እርምጃ በጽኑ አውግዛለች። ኢራንም ሆነች አጋሮቿ በአሜሪካ ጦር አሊያም በእስራኤል ላይ ሌላ ጥቃት ቢፈጽሙ “ተጠያቂ” መሆናቸው እንደማይቀር በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ዉድ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በኢራን ቆንስላ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማውገዝ ሩሲያ ለጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ያረቀቀችውን የውሳኔ ሐሳብ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ውድቅ አድርገዋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በእጅ አዙር ከምትፋለማቸው ኢራን በቀጥታ በተሰነዘረባቸው ጥቃት በዝምታ የሚያልፉት አልሆነም።

“ይኸ ጥቃት ሁሉንም ቀይ መስመር ተላልፏል። እስራኤል የአጸፋ እርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ መብት አላት” ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳን “በሚፈላ ውኃ ውስጥ ያለ እንቁራሪት አይደለንም። የአንበሶች ሀገር ነን” በማለት ሀገራቸው የአጸፋ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ፍንጭ ሰጡ።

እስራኤል የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ካስጠነቀቀች በኋላ ኢራን በተራዋ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ቆይታለች። አርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 እስራኤል በኢራን ላይ በሚሳይል ጥቃት መፈጸሟን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሲቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። እስራኤል ስለ ጥቃቱ ምንም ያለችው ነገር የለም።

በኢራን ኢስፍሀን ከተማ የሚገኝ የዩራኒየም ማብለያ ጣቢያ
ኢስፍሀን የኢራን የኑክሌር ማብለያ ጣቢያ እና የሀገሪቱ አየር ኃይል የጦር ሠፈር የሚገኝባት ቁልፍ ከተማ ነች። ምስል epa/dpa/picture alliance

የኢራን መንግሥት የሚቆጣጠረው ብሔራዊ የዜና አገልግሎት በኢስፍሀን ሰማይ ሦስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በኢራን የአየር መከላከያ መመታታቸውን ዘግቧል። ኢስፍሀን የሠፈረው የኢራን ጦር አዛዥ ጄኔራል ሲያቫህ ሚሐንዶስት “ዛሬ ማለዳ የተሰማው ድምጽ የፍንዳታ አይደለም። ኃይለኛው የአየር መከላከያችን በአጠራጣሪ ቁሶች ላይ ሲተኩስ የተፈጠረ ነው። ምንም አይነት ጉዳት አላስከተለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የጦር አዛዡ  “የአየር መከላከያው እና ኩሩ ሠራተኞች በእስላማዊ ኢራን ምድር ወይም ሰማይ የተንኮል ዕቅድ ያላቸው ማናቸውም ጠላቶች ለመጋፈጥ ተዘጋጅተዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢስፍሀን የሀገሪቱ ዋንኛ አየር ኃይል የጦር ሠፈር የሚገኝባት ቁልፍ ከተማ ነች። ከአቅራቢያዋ የምትገኘው ናታንዝ የኢራን የኑክሌር ማብለያ ጣቢያዎችን ይዛለች። ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቋል። የእስራኤል መንግሥት በኢራን ጥቅሞች ላይ አዲስ ጥቃት እስካልሰነዘረ ድረስ ኢራን ምላሽ እንደማትሰጥ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሑሴይን አሚር አብዶላሒን ተናግረዋል።

የቻታም ሐውስ ባልደረባ የሆኑት ሳናም ቫኪል በኢስፍሀን ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ጉዳት እንዳይደርስ እና ሌላ የአጸፋ ምላሽ ከኢራን በኩል እንዳይኖር የታቀደ እንደሆነ ያምናሉ።

ሐሚድሬዛ ጎሎምዛዴ የተባሉ ኢራናዊ ተንታኝ እንደሚሉት በኢስፍሀን የተከሰተው ፍንዳታም ይሁን ጥቃት ይኸ ነው የሚባል ጉዳት ባያደርስ እንኳ “ሁለቱ ሀገሮች ለኃይል ሚዛን በሚያደርጉት ትግል ማዕቀፍ የሚታይ” ነው። ቀጠናው ቀውስ ውስጥ ገብቷል ብለው የሚያምኑት ሐሚድሬዛ በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

እሸቴ በቀለ