1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሁዱ ምርጫና ታዛቢዎች

ዓርብ፣ ግንቦት 14 2007

ኢትዮጵያ የፊታችን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007ዓ,ም አምስተኛዉን ብሔራዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ከአፍሪቃ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘዉ ሀገር በዘንድሮዉ ምርጫ ከ50 በላይ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ።

https://p.dw.com/p/1FUWA
EU Parlamentarier - Ana Maria Gomes
ምስል CC-BY-Security & Defence Agenda

[No title]

በምርጫዉ ድምፁን ለመስጠትም ከ36,8 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መመዝገቡን የሀገሪቱን የምርጫ አስፈፃሚ አካል የጠቀሱ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ምርጫዉን ለመታዘብ ከሀገር ዉስጥ ምርጫ ቦርድ ከሚያሰማራቸዉ ሌላ ከዉጭ የአፍሪቃ ኅብረት ታዛቢዎች ብቻ እንደሚገኙ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተካሄዱ ምርጫዎችን የታዘቡ የአዉሮጳ ኅብረትም ሆነ የአሜሪካዉ ካርተር ማዕከል ታዛቢዎች አይገኙም። የ1997ቱን ምርጫ የታዘቡት የአዉሮጳ ኅብረት ልዑካን መሪ ታዛቢ መላክ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ።

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
የገዢዉ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ደጋፊዎቹምስል Reuters/Tiksa Negeri

የዘንድሮዉ ምርጫ ከ1983 እስከ 2004,ም ድረስ በመንግሥት ስልጣን ላይ ከነበሩት ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያዉ ምርጫ ነዉ። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድምፁን ለመስጠት የተመዘገበዉ ሕዝብ ብዛት በሀገሪቱ የተሻለ ዴሞክራሲ ሰፍኖ እንደሁ የሚፈትንበት አጋጣሚ እንደሆነ መጠቆሙን የዜና ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ገዢዉ ፓርቲ የተቃዋሚዎችን ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞችን ይጫናል፤ እንዲሁም ፀረ ሽብር ሕጉን በመጠቀም የዜጎችን ድምፅ ያፍናል ተቺዎቹንም ያስራል ሲሉ ይከሳሉ። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ስልጣን ጨብጦ የሚገኘዉ ገዢዉ ፓርቲ በበኩሉ በምርጫዉ ስኬት ለማግኘት ያከናወናቸዉ የልማት ተግባራት በቂ እንደሆኑ እንደሚገልፅ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

Äthiopien Wahlen 2015
ምስል DW/E. Bekele

የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012,ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸዉ በመንበራቸዉ የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስርዓት ለቀቅ በማድረግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ስፍራ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸዉን መግለፃቸዉም እንዲሁ ተሰምቷል። ባለፈዉ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ በሰጡት መግለጫ «ትክክለኛ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በዚህች ሀገር ካልኖረ ሀገሪቱ እንደሶማሊያ ልትሆን ትችላለች» ማለታቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ጠቅሷል። ተቃዋሚዎች ግን መንግሥት በምርጫዉ ድሉን ለማረጋገጥ የፈላጭ ቆራጭነት ስልት ይጠቀማል ሲሉ ይከሳሉ። ፓርቲና መንግሥት አለመለየታቸዉ፤ መገናኛ ብዙሃን፤ የፀጥታ ኃይሎችና ገንዘብ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆናቸዉንም እንደዋና ችግር ይጠቅሳሉ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ እጩዎቻቸዉም መጠነሰፊ ወከባ እየደረሰባቸዉ ነዉ ሲሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቤቱታቸዉን ያሰማሉ። የምርጫዉ አስፈፃሚ አካል ግን እነዚህን አቤቱታዎች ሁሉ መሠረተ ቢስ ሲል ያጣጥላል። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የዘንድሮዉ ካለፉት ዓመታት እጅግ የተሻለ ነዉ፤ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመቻቸዉ ምህዳርም ልዩ ነዉ ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

ለእሁዱ ምርጫ የምርጫ ኮሚሽኑ 40 ሺህ የሚሆኑ የሀገር ዉስጥ ታዛቢዎችን በ45 ሺህ 795 የምርጫ ጣቢያዎች ያሰማራል። ዘንድሮ ብቸኛዉ የዉጭ የምርጫ ታዛቢ አካል የአፍሪቃ ኅብረት ነዉ። ኅብረቱ 59 ታዛቢዎችን ያሰማራል። የ1997ቱንና የ2002ቱን ምርጫ የታዘቡት የአዉሮጳ ኅብረትና የአሜሪካዉ የካርተር ማዕከል ግን ዘንድሮ አይገኙም። የዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ያነጋገራቸዉ በ1997,ም የአዉሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑካን መሪ የነበሩት አና ጎሜዥ ምርጫዉን ለመታዘብ መሄድ እንደማያስፈልግ መወሰኑን ይናገራሉ።

Ana Maria Gomes Mitglied des Europäischen Parlaments beim AFET committee Meeting
አና ጎሜዥምስል Europäische Union - Referat Audiovisuelle Medien

«ላለመሄድ በትክክል የወሰንነዉ የሀሰት ምርጫ እንደሚካድ እያወቅን ያንን ለማረጋገጥ ታዛቢ መላክ እንደሌለብን ስላመንን ነዉ። ቀልድ ነዉ የሚሆነዉ፤ ምክንያቱም ፍፃሜዉ ልክ በ2002 እና በ1997 እንደነበረዉ ነዉ የሚሆነዉ። ሕዝቡ በብዛት ድምፁን ሊሰጥ ወጣ በቆጠራዉ ላይ አጭበረበሩ።»

ፓርቱጋላዊቱ የአዉሮጳ ኅብረት አባል አና ጎሜዥ አያይዘዉም ኅብረቱ የምርጫ ታዛቢ ወደኢትዮጵያ ያልላከበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ።

«በዚህ የተነሳ ምክር ቤቱ ለሚስ ሙጌሪኒ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚታዘብ ተልዕኮ ሊኖር እንደማይገባ በማስታወቅ ደብዳቤ ጽፏል። የቲየስ በርመን እና የእኔ የ1997 የምርጫ ትዝብት ዘገባዎች በመንግሥት ተቀባይነት አላገኙም። ተግባራዊ ማድረግ ይቅርና እዚያዉ ተመልሰን እንኳን ዘገባችንን እንድናቀርብም አልፈቀደም። ምክንያቱን የሰሉ አስተያየቶችን በመያዛቸዉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የአዉሮጳ ኅብረት ለምርጫ መታዘብ ያልመጣዉ በገንዘብ እጥረት ነዉ ማለቱን አዉቃለሁ። ሆኖም ይህ ፍፁም እዉነት አይደለም። እኔ ራሴ ከአዉሮጳ ኅብረት የናይጀሪያን ምርጫ ለመታዘብ ሄጄ ገና መመለሴ ነዉ፤ በተለያዩ የአፍሪቃ ሆነ ከአፍሪቃ ዉጭ ሃገራትም የምርጫ ታዛቢ ልዑካን አሉን። ወደኢትዮጵያ የማንሄደዉ በበጀት ጉዳይ ሳይሆን በፖለቲካዊ ምክንያት ነዉ። ይህም ማለት ከእንግዲህ ቀልድ የሆኑ ምርጫዎችን አብረን ማፅደቅ የለብንም ብለን ስለወሰንን ነዉ።»