የኢትዮጵያዉያን የሥነ-ጥበብ ድግስ በጀርመን
ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2008የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ጀርመን ፉልዳ ከተማ ባለች አንዲት አነስተኛ ከተማ በሚገኝ ታሪካዊ ኢግዚቢሽን ዉስጥ ለሦስት ወራት የሚዘልቅ የሥዕል አዉደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ- ስርዓት ላይ የተገኘዉ የአርቲስት ስለሺ ደምሲ ወይም በመድረክ ስሙ ጋሽ አበራ ሞላ፤ ዓዉደ ርዕዬን ለመጎብኘት የመጣዉ ታዳሚን አስደሞም ነበር።
ፉልዳ የተሰኘችዉ ሰፋ ያለች ከተማ አዋሳኝ ላይ የምትገኘዋ አነስተኛዋ የጀርመን ክላይን ዛሰን ከተማ፤ ጥንታዊ የእግዚቢሽን ማዕከል በመያዝዋ በዓለም ታዋቂ የሆኑ ሰዓልያን ይጎበኝዋታል፤ የሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸዉንም ያቀርባሉ። የዛሬ ሦስት ሳምንት ግድም ኢትዮጵያዉያን ሰዓልያንን ጨምሮ ቆይታቸዉን በኢትዮጵያ አድርገዉ ኢትዮጵያን በሥነ-ጥበብ ስራዎቻቸዉ ያስቀመጡ ጀርመናዉያን ሥራዎቻቸዉን ለሦስት ወራት በሚቀርበዉ ዓዉደርዕይ አቀርበዋል። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያዉያን ሠዓሊዎች በቪዛ ችግር ምክንያት በአካል ባይገኙም ሥራዎቻቸዉ በዚሁ ዓዉደ ርዕይ ላይ ቀርቦአል። ከኢትዮጵያዉያን ጋር የቆየ ግንኙነት ስላላቸዉ ለሃገሪቱ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸዉ የሚናገሩት የኤግዚቢሽኑ ዋና ተጠሪ ሞኒካ ኤበርቶቭስኪ፤ በሚኖሩበት አካባቢ የኢትዮጵያን ገፅታ ማሳየት የሚመኙት ነበር።
«ይህን አዉደ ርዕይ ለማዘጋጀት ሳስብ ብዙ ጊዜያትን ወስዶብኛል ይህን የእግዚቢሽን ማዕከል በአስተዳዳሪነት ስመራም አንድ ዓመት ሆነኝ ። ከአንድ ዓመት በፊት ረዘም ላለ ጊዜ እኖር የነበረዉ በበርሊን ነዉ። በርሊን ሳለሁ እራስንህ ርዳ በሚል ኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዉስጥ በንቃት ስሳተፍ ቆይቻለሁ። ማኅበሩ የኢትዮጵያዉያን እና የጀርመናዉያን ስለነበር ከኢትዮጵያዉያን ጋር ብዙ ለመገናኘትና ለመተዋወቅ በቅቻለሁ። ኢትዮጵያዉያኑን በቅርበት እያወኩዋቸዉ ስሄድ ስለሃገሪቱና ስለህዝቧ የማወቅ ጉጉት እያደረብኝ መጣ ደሞ ከዝያ ሌላ ኢትዮጵያዉያን በጥሩነታቸዉ ከዓለም አንደኛ ናቸዉ።»
በአካባቢዉ ላይ በርካታ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርታራዉያን እንደሚኖሩ የገለፁልን ሞኒካ ኤበርቶቭስኪ በተለይ በከተማዋ በሚገኘዉ የስደተኞች መኖርያ ዉስጥ የሚኖሩ ኤርትራዉያን እና ኢትዮጵያዉያን ያዘጋጁት ባህላዊዉ ምግብ እንጀራና ወጥ በሽያጭ መልክ ቀርቦአል። ገቢዉም የስደተኞች ጣብያዉ ወጭ የሚዉል መሆኑ ተመልልክቶአል። ሞኒካ ስለዓዉደ ርዕዩ በመቀጠል።
«ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር ሰርቻለሁ ለምሳሌ ሊስትሮ የተባለዉን ድርጅት የማዉቀዉ ከምስረታዉ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ጀምሮ ነዉ። ይህን የእግዚቢሽን ማዕከል በመሪነት ማገልገል ስጀምር ስለኢትዮጵያ ማቅረብ እንደምችል ለኔ ግልፅ ነበር። በዚህም በኢትዮጵያ የሚገኙ ሥነ-ጥበባትና የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ሥራቸዉን እንዲሁም በጀርመን የሚኖሩ ሰዓልያንና ሥራቸዉን በጋራ እቅድ ይዤ ይኸዉ ለእይታ በቅቶአል። ይህን የስዕል አዉደ ርዕይ ያየ ብዙ ይጠይቃል፤ ብዙ ያዉቃል፤ ይተዋወቃል እጅግ ጥሩ ነገር ነዉ። በኢትዮጵያ ያሉ ሰዓሊዎች እዚህ ካሉት ኢትዮጵያዉያን ሥራዎች ጋር ሌላ አይነት ዘዴና አያያዝ እንዳላቸዉ መረዳት ይቻላል።»
ሠዓልያኑ በቀለማቸዉ ኢትዮጵያን በተለያየ መልክዋ ባለ ክራሩ ስለሺ ደምሴ እንዲህ በክራሩ በአማርኛ እያዜመ በእንጊሊዘኛ እየተረጎመ የተሰበሰበዉን ሕዝብ አጀብ ሲያሰን ማየቱ አይደለም ኢትዮጵያዉያኑን ብቻ ይህ አዉደርእይ እንዲዘጋጅ የፈቀዱትን እንደፈንዲሻ ሲያስፈነድቅ ማየቱ በጣም ያስደስታል።
ከያኒ ስለሺ ደምሴ 19 ሰዓልያን የሥዕል ሥራዎቻቸዉን ባቀረቡት አዉደ ርዕይ መክፈቻ ላይ ባቀረበዉ ሦስት እና አራት ሙዚቃ ብቻ የሙዚቃ ድግሱ አላበቃም። የክላይን ዛስን ከተማ ሕዝብ አርብ ለቅዳሜ አጥብያ በስለሺ ደምሴና በአንድ ክራሩ ጥበባዊ ችሎታዉ ሲዝናና በሳቅ ሲፈርስ ነዉ ያመሸዉ። በአዉደ ርዕዩ መክፈቻ እለት ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ የከተማ ነዋሪና በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ነበር የተገኙት ። ተቀማጭነቱን በበርሊን ያደረገዉ የበርሊኑ የሊስትሮ ድርጅት የዚህ አዉደ ርዕይ ተባባሪ አዘጋጅም ነበር። የድርጅቱ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሻንቆ፤ የሊስትሮ ሳጥን አዉደርዕይ ዘርግተዉ ሳለ ከዛሬ አስራ ሦስት ዓመት በፊት የተዋወቅዋት የኢግዚቢሽኑ ዋና ተጠሪ የኢትዮጵያዉያን ሥነጥበብን ለማሳየት በመፈለጋቸዉ፤ ሊስትሮ ድርጅት ሠዓልያኑን በማሰባሰብ መርዳታቸዉን ነግረዉናል። በዓዉደርዕዩ ላይ የተለያዩ የሊስትሮ ሳጥኖች፤ የሊስትሮን ማንነት በመግለፅ የተመልካቹን ቀልብ ስበዉ ነበር። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ