1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ እና የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር

ረቡዕ፣ የካቲት 15 2009

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ድርድር ከጀመረች 14 አመታት ተቆጠሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ ከሁለት አመታት በፊት ይጠናቀቃል የሚል እቅድ ነበረው። ድርድሩ ግን ላለፉት አምስት አመታት ከነበረበት ፈቅ አላለም። 

https://p.dw.com/p/2Y5E3
Logo Welthandelsorganisation WTO

 የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ማመልከቻ የት ደረሰ?

ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. የዓለም የንግድ ድርጅትን እንደምትቀላቀል የሐገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር። በኢትዮጵያ የንግድ ሚኒስቴር የበይነ-ንግድ ግንኙነት (Multilateral Trade Relations) ቢሮ ኃላፊ አቶ ልሳነወርቅ ዘርፉ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2013 ዓ.ም በአገሪቱ የእድገት እና ለውጥ እቅድ መሰረት በ2015 ዓ.ም. ሶስተኛ የበጀት አመት ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር የሚደረገው ድርድር እንደሚጠናቀቅ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር። በወቅቱ የባለስልጣኑን አስተያየት «ፌዝ» ያሉት አልጠፉም። ኢትዮጵያ ውስብስብ አሰራሮች ከሚከተለው ድርጅት ጋር የምታደርገው ድርድር ባለስልጣኑ ባሉት ቀነ-ገደብ አልተጠናቀቀም። እንዲያውም ከነበረበት ፈቅ አላለም። 

የድርድሩን ሒደት በቅርበት ከሚከታተሉት መካከል ቢኬፒ የተሰኘው ከእድገት ጥናት እና አማካሪ ተቋም መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ዴርክ ቢይነን ናቸው። ጀርመናዊው ቢይነን ባለፈው ጥቅምት ኢትዮጵያ ለአለም ንግድ ድርጅት ያስገባቸው የአባልነት ማመልከቻ ከመስቀለኛ መንገድ ላይ ተገትሯል የሚል ፅሁፍ አስነብበው ነበር። 
«ለማናቸውም አባል አገራት የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሒደት ከ10-25 አመታት ይወስዳል። ስለዚህ አሁንም ተስፋ አለ። ይኸ የመጀመሪያው ነው። በሌላ ወገን የወሰደው ጊዜ ሳይሆን ኃሳብ የገባኝ ባለፉት ሶስት፤ አራት ፤ አምስት አመታት ምንም አለመፈጠሩ ነው። ሒደቱ ሙሉ በሙሉ ቆሟል። የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ዒላማ ከሆነ ይኸ አሳሳቢ ነው።ስለዚህ ድርድሩ የወሰደው ጊዜ ሳይሆን የሚያሳስበው ባለፉት ጥቂት አመታት ምንም አለመፈጠሩ ነው።በእኔ መረጃ መሰረት ለአለም የንግድ ድርጅት በማንኛውም ጊዜ መቅረብ የሚችሉ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰነዶች በቴክኒካዊ ደረጃ ተዘጋጅተዋል። ነገር ግን ከፖለቲካዊው አካል ፈቃድ አልተሰጠም። ሒደቱን እየጎተተው ያለው ይህ ነው።»
ኢትዮጵያ የአባልነት ማመልከቻዋን እስክታስገባ ድረስ ከጎርጎሮሳዊው 1997-2002 ዓ.ም. ድረስ የአለም ንግድ ድርጅት ታዛቢ ሆና ቆይታለች። በድርጅቱ ደንብ መሰረት አገራት በታዛቢነት ከአምስት አመት በላይ መቆየት አይችሉም። አጠቃላይ የታሪፍ እና የንግድ ስምምነት (General Agreement on Tariffs and Trade) በጎርጎሮሳዊው 1995 ዓ.ም. ለተመሰረተው የአለም ንግድ ድርጅት መሰረት ነው። በ23 አገራት የተጀመረው አጠቃላይ የታሪፍ እና የንግድ ስምምነት በንግድ ልውውጥ ላይ የሚጣሉ ታሪፎችን ለመቀነስ ያለመ ነበር። ኢትዮጵያ ለአባልነቷ የሚደራደር ኮሚቴ ያቋቋመችው  በጎርጎሮሳዊው 2003 ነበር። የአለም የንግድ ድርጅት ድረ-ገፅ እንደሚጠቁመው በዴንማርካዊው አምባሳደር ስቴፋን ስሚድት የሚመራው ኮሚቴ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘው በጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2012 ዓ.ም. ነበር። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ ሙሴ ደለለኝ ናቸው። አቶ ሙሴ የዓለም አቀፍ ንግድ ባለሙያ አይደሉም። በሥራቸው ምክንያት በመልማት ላይ ያሉ ኢትዮጵያን መሰል አገሮች ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር የሚያደርጉትን የአባልነት ድርድር በቅርበት የሚታዘቡት አቶ ሙሴ በሸቀጦች ግብይት ላይ የሚጣሉ ቀረጦችን ለመቀነስ የተደረጉ ረጅም ድርድሮች በሒደት ውስብስብ መሆናቸውን ይናገራሉ። 

ታዛቢዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ በፋይናንስ እና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ከአለም የንግድ ድርጅት መርኅ ጋር እጅጉን ይጣረሳል። የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍን ለውጭ ኩባንያዎች  እንደማይፈቀድ በተደጋጋሚ አሳውቋል። የዓለም ባንክን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት የፋይናንስም ይሁን የቴሌኮምን የመሰሉ ዘርፎች ለውጭ ገበያ ክፍት እንዲሆኑ ዛሬ ድረስ ይወተውታሉ። ዶ/ር ዴርክ ቢይነን ይኸው ጉዳይ በኢትዮጵያ እና የአለም ንግድ ድርጅት መካከል በሚደረገው ድርድር ቁልፍ ቦታ እንዳለው ይናገራሉ። 

«ቁልፉ ጉዳይ እንዲሁም ድርድሩን ወደ ኋላ የጎተተው ይኸው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎት ገበያዋን እንድትከፍት የሚወተውቱ የአለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት አሉ። ኢትዮጵያ እነዚህን መስኮች ለውጭ ገበያ የመክፈት አዝማሚያ ካላሳየች የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን አትችልም። በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ቸልተኛ ሆኗል። የፋይናንስ አገልግሎቱን ለውጭ ባለወረቶች የመክፈት አነስተኛ ምልክቶች ቢኖሩም ማለት ነው። ይኸ በአለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ፍላጎት እና በኢትዮጵያ መንግስት አቋም መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ረገድ መልካም ምልክት ነው። ሁለተኛው መሰናክል የቴሌኮም አገልግሎቱ ላይ ያለው ነው። ይኸ በነበረበት እንደ ቆመ ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አንዳች እንቅስቃሴ ካልኖረ በቀር የአገሪቱ የአባልነት ማመልከቻ ወደፊት ይንቀሳቀሳል ብዬ አላስብም። ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለወረቶች ክፍት መሆን አለበት ማለት አይደለም። ሙሉ በሙሉ ለባለወረቶች በተከፈተ አሊያም በተዘጋ የሥራ ዘርፍ ላይ በርካታ ገደቦች ማስቀመጥ ይቻላል። ይሁንና ሙሉ በሙሉ ዘግቶ መቀመጥ የአለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ማመልከቻውን ውድቅ ያደርገዋል። »
አቶ ሙሴ ደለለኝ እንደሚሉት የአለም የንግድ ድርጅት መመሪያ ኢትዮጵያ ሁሉንም ዘርፎች ለውጭ ባለወረቶች በአንድ ጊዜ ትክፈት ብሎ እንደማያስገድድ ይናገራሉ። 

ያላቻ ጋብቻ

Symbolbild Bahnbaustelle
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughan


ኢትዮጵያ ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር የፈለገችውን ጥምረት ያላቻ ጋብቻ ሲሉ የሚተቹ ጥቂቶች አይደሉም። ነፃ ገበያ እየሰራ አይደለም የሚሉ የአለም ንግድ ድርጅት ተቺዎች ተቋሙ ኢ-ፍትኃዊነትን ከማማባስ የተሻለ  ሚና የለውም ሲሉ ይተቹታል። ዓለም ፈጣን ኤኮኖሚያዊ እድገት ባስመዘገበችባቸው ዓመታት (ከጎርጎሮሳዊው 1960-1998) በአገራት ውስጥም ይሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኢ-እኩልነት ጨምሯል። የተባበሩት መንግስታት ድጅት የልማት ፕሮግራም እንደገለጠው 20 በመቶው የዓለም ህዝብ የምድሪቱን 86 በመቶ ሐብት ይጠቀማል ። ቀሪው 80 በመቶ ደግሞ 14 በመቶውን ይቀራመታል። የአለም ንግድ ድርጅት ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሐ አገሮችን ለባለጠጎቹ ገበያ እና መዋዕለ ንዋይ በመክፈት ይኸው ኢ-እኩልነት እንዲከር አስተዋፅዖ አበርክቷል የሚል ትችት ይቀርብበታል። አቶ ሙሴ ግን በዚህ አይስማሙም። 
በኢትዮጵያ እና በአለም ንግድ ድርጅት መካከል የሚደረገው ድርድር በእኩዮች መካከል ላለመሆኑ ዶክተር ዴርክ ቢይነንም ይስማማሉ። ኢትዮጵያ አባልነቱን አጥብቃ ከፈለገች የምትጠየቀውን መስጠት እንደሚኖርባትም ዶክተር ዴርክ ቢይነን ያምናሉ። 
«እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ኢትዮጵያ ምን ታገኛለች? የሚገኝ ነገር አለ ብዬ አስባለሁ። ለየትኛውም የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገር  የገበያ አድማስ በማስፋት ረገድ ማለት አይደለም። ሌሎች አገራት ኢትዮጵያን ከሌሎች በተለየ መንገድ አያስተናግዷትም። የአውሮጳ ኅብረት እና ቻይና የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ጠቃሚ ገበያዎች ናቸው። በእድገት ኋላ ከቀሩ አገራት መካከል እንደ መሆኗ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከጦር መሳሪያ ውጪ ሁሉንም ለመነገድ የአውሮጳ ኅብረት እንዲሁም ከቻይና ጋር በተፈጸመ ሥምምነት ተጠቃሚ ነች። እነዚህ ግን በአንደኛው ወገን ፍላጎት በየትኛውም ጊዜ ሊሰረዙ ይችላሉ። ይኸ አሁን የሚሆን አይመስልም ሊባል ይቻላል። ነገር ግን ለምሳሌ «አፍሪካን ጎሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት» በአሕጽሮት «አጎዋ» የተባለው የንግድ ትብብር በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በየትኛውም ጊዜ ላለመሰረዙ እርግጠኛ አይደለሁም። የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ የውጭ ንግዱን ማሳደግ ነው። ወጣም ወረደ አሁን ወደ ውጭ የምንልከው ትንሽ ነው ለሚለው መከራከሪያ እስማማለሁ የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ፋይዳ የለውም። ለኢትዮጵያ ግን ጉዳዩ እሱ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ንግድን በፍጥነት ማሳደግ ይሻል። አላማው ይኸ ከሆነ እና ስኬታማ የመሆን እቅድ ካለው የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ከፍ ያለ ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል።»

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherin
ምስል Jeroen van Loon

አቶ ሙሴ ደለለኝ ኢትዮጵያ ከአለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ጋር የምታደርገውን ድርድር በከፍተኛ ጥንቃቄ ማካሔድ ይጠበቅባታል ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ሙሴ አባልነትን የተመለከቱ ደንቦችን በጥልቀት በማጥናት እና አጋዥ አንቀፆችን በመጠቀም ድርድሩ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።  
ዶክተር ዴርክ ቢይነን በበኩላቸው «የአለም ባንክ ማመልከቻው ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ በባንክ እና የቴሌኮምዩንኬሽንስ አገልግሎቶች ላይ ትልልቅ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።» ብለዋል። ሒደቱን የሚያፋጥኑት የኢትዮጵያ መንግሥት በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ናቸው ያሉት ቤይነን  «ውሳኔዎቹን ለመወሰን አንድም ልበ-ምሉዕ የሆነ ሰው ከጠፋ በአባልነት ለመመዝገብ በተጀመረው ሒደት ላይ የረባ እንቅስቃሴ አይኖርም ስል እፈራለሁ።» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 


እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ