1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በውጭ ባለሙያዎች ላይ ጥገኛ የሆኑት የስሚንቶ ፋብሪካዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል ይነጣጠቃሉ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2009

በአንድ ወቅት የሐገር ዉስጥ ምርት በእጥረት በመኖሩ ስሚንቶ ከውጭ ለመሸመት የተገደደችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የምርት እና ፍጆታ አለመመጣጠን ገጥሟታል። ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የስሚንቶ ፋብሪካዎች በውጭ አገር ባለሙያዎች ላይ ጥገኛ ሆነዋል ሲሉም ይተቻሉ። 

https://p.dw.com/p/2bySe
Afrika Klinker-Werk der Firma HeidelbergCement
ምስል HeidelbergCement

የስሚንቶ ፋብሪካዎች ጋሬጣዎች

በዚህ ወር ኢትዮጵያ አዲስ የስሚንቶ ፋብሪካ አስመርቃለች። በ16,500 ኢትዮጵያዉያን ባለ አክሲዮኖች እና በሁለት የደቡብ አፍሪቃ ኩባንያዎች  የተገነባው ሐበሻ ስሚንቶ ፋብሪካ በቀን 4,500 ቶን በአመት 1.4 ሚሊዮን ቶን ስሚንቶ ያመርታል ተብሏል። ከአዲስ አበባ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ የተገነባው ፋብሪካ ሁለት አመት እና 155.3 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቷል።የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ንብረት የሆነው የንግድ ልማት ባንክ (TDB) ለሐበሻ ስሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በብድር ሰጥተዋል።ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. አመታዊ የስሚንቶ ምርቷን ወደ 27 ሚሊዮን ቶን የማሳደግ እቅድ አላት። ለዚህም ግዙፎቹን የሚድሮክ ደርባ እና የአሊኮ ዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የአገሪቱ ማምረቻዎች ቁጥር 16  ሆኗል።የሐበሻ ስሚንቶ ፋብሪካ ሲመመረቅ በሆለታ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ «የአገሪቱን ፍላጎት አሟልተን ወደ ጎረቤት አገራት መላክ ጀምረናል» ሲሉ ተደምጠዋል።የሐበሻ ስሚንቶ ፋብሪካ በማምረት አቅሙ ከሚድሮክ ደርባ፤ሙገር፤መሰቦ፤ናሽናል እና ዳንጎቴ ጎራ ተሰልፏል። አምስቱ ግዙፍ ፋብሪካዎች ወደ 70% የሚጠጋውን ስሚንቶ ያመርታሉ። መካከለኛ የማምረት አቅም ያላቸው አራት ፋብሪካዎች ደግሞ ከአጠቃላዩ ምርት ከ12-13 በመቶ ድርሻ አላቸው።

የኢትዮጵያ አመታዊ የስሚንቶ ምርት ባለፉት አስርት አመታት ከ1.6 ሚሊዮን ቶን ወደ 15 ሚሊዮን ቶን አድጓል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት እና የአይ-ካፒታል አፍሪቃ ማዕከል ኃላፊው ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ ግን የኢትዮጵያ አመታዊ የምርት መጠን ከአፍሪቃ አገራት የነፍስ ወከፍ የስሚንቶ ፍጆታ አኳያ ሲመዘን እጅጉን አነስተኛ ነው ባይ ናቸው።

Äthiopien Addis Abeba im Bau
ምስል DW/E. Bekele

ኬንያ፤ዩጋንዳ እና ታንዛኒያን በመሳሰሉ አገራት እንደ ሆነው ሁሉ በኢትዮጵያ የተስፋፋው ግንባታ ለስሚንቶ ፍላጎት ማሻቀብ ዋንኛው ገፊ ምክንያት ነው። በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2008‐2011 ዓ.ም. ባሉት አመታት የተከሰተው የስሚንቶ እጥረት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ፈጥሮ ኢትዮጵያ ከውጭ በምታስገባው ምርት ላይ ጥገኛ እንድትሆንም አስገድዷት ነበር። የኢንዱስትሪ ሚኒሥቴር ከሶስት አመታት በፊት ይፋ ያደረገው የስሚንቶ ኢንዱስትሪ እቅድ እንደሚጠቁመው በጎርጎሮሳዊው 2007/2008 ዓ.ም. 1.24 ሚሊዮን ቶን ስሚንቶ ከውጭ አገር ሸምታለች።  ከጎርጎሮሳዊው 2015-25 ባሉት አመታት የኢትዮጵያን የስሚንቶ ኢንዱስትሪ ልማት እድሎች እና ፈተናዎች የሚፈትሸውን ሰነድ ካጠናቀሩት ባለሙያዎች መካከል ዶ/ር ገመቹ አንዱ ናቸው። ዶ/ር ገመቹ የስሚንቶ እጥረት የወለደው የማምረቻዎች መስፋፋት መልሶ ከአገሪቱ የፍጆታ አቅም በላይ ምርት መፍጠሩን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የስሚንቶ ምርት እና ፍጆታ እድገት ቢያሳይም ፋብሪካዎቹ ካላቸው የማምረት እቅም 50 በመቶውን ብቻ ይጠቀማሉ። ምጣኔው ከዓለም አቀፍ መለኪያዎች አኳያ ሲነፃጸር እጅጉን አናሳ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አማካኝ የማምረት አቅም ከ60-70 በመቶ ሲሆን ዘላቂ እና አዋጪ የሚባለው ደግሞ ከ80-85 በመቶ ከፍ ይላል። እነ ዶ/ር ገመቹ ያዘጋጁት ሰነድ የኢትዮጵያ መንግሥት አገራዊውን ፍጆታ በማነቃቃት ከስሚንቶ የምርት መጠን ጋር የተፈጠረውን ክፍተት ሊያጣጥም ይገባዋል የሚል ጥቆማ አቅርቧል።

የስሚንቶ አገራዊ ምርት እና ፍላጎት ባልተጣጣመባት ኢትዮጵያው መጪው ጊዜለ አምራቾች ፈታኝ ይመስላል። ግዙፎቹ ፋብሪካዎች ላለው ውስን የገበያ ፍላጎት እርስ በርስ መወዳደር እስኪ ጀምሩ ድረስ በትናንሾቹ ላይ ይበረታሉ። ውስን የማምረት አቅም፤ገንዘብ እና የሰው ኃይል ያላቸው አነስተኛ ኩባንያዎች ሁለት አማራጮች አሏቸው። አንደኛው ውድድሩን ለግዙፎቹ አምራቾች በመተው ወደ አማራጭ ምርቶች መሸጋገር አሊያም ትልልቆቹ የማይደርሱባቸውን ገበያዎች መቃኘት።

Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele

ዶ/ር ገመቹ የኢትዮጵያ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ባለፉት አስር አመታት ጥገኝነት ጠንቶባቸዋል ሲሉ ይተቻሉ። በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤የውጭ ምንዛሪም ያስገኛሉ የሚል ተስፋ የተጣለባቸው ፋብሪካዎች አካሔዳቸው በውጭዎቹ ባለሙያዎች እጅ ላይ ጥሏቸዋል። ዶ/ር ገመቹ «ብልጠት የጎደለው» እና የአገር «ጥቅምን» አሳልፎ የሚሰጥ «አደገኛ» ውሳኔ ሲሉ ይናገራሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ላይ የተካሔደው የምሥራቅ አፍሪቃ የስሚንቶ፤ኮንክሪት እና ኃይል ሁለተኛ ጉባኤ የኢትዮጵያ የስሚንቶ ኢንዱስትሪ በገጠመው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ላይ መክሯል። በጉባኤው የአይ-ካፒታል አፍሪቃ ማዕከል ኃላፊው የኢትዮጵያ የስሚንቶ ፋብሪካዎች የሚጠገኑት፤የሚተዳደሩት እና የምርታቸውን ጥራት የሚቆጣጠሩት የውጭ ባለሙያዎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። በቁጥር ወደ 1,000 የሚጠጉት የውጭ ባለሙያዎች በወር በነፍስ ወከፍ በአማካኝ 4,500 ዶላር ይከፈላቸዋል። ክፍያው በአመት ሲሰላ ወደ 60 ሚሊዮን እንደሚደርስ ዶ/ር ገመቹ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሐበሻ ስሚንቶ ፋብሪካን መርቀው ሲከፍቱ አገራቸው ፍጆታዋን አሟልታ ለጎረቤት አገራት መላክ መጀመሯን እንደ በጎ ዜና ተናግረዋል። ጅቡቲ፤ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የመጀመሪያዎቹ ገበያዎች ናቸው። ይሁንና በኢትዮጵያ እና በአገራቱ መካከል ያለው ደካማ የመሰረተ-ልማት እና ውድ የማጓጓዣ ዋጋ ግብይቱ አዋጪ እንዳይሆን አድርጎታል። አገራቱ የየራሳቸውን የስሚንቶ ማምረቻዎች ለማበረታታት መወሰናቸው እና ግብይቱ የሚገዛባቸው ሕግጋት ሌሎች ፈተናዎች ናቸው። በተቃውሞ ሲናጡ የከረሙት የኦሮሚያ እና አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የስሚንቶ ፋብሪዎች ለመገንባት አቅደዋል፤የመሰረት ድንጋይም ጥለዋል። አዋጪነቱን በአግባቡ ስለመፈተሻቸው ግን የሚታወቅ ነገር የለም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ