1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምርጫ ጊዚያዊ ዉጤትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች

ሰኞ፣ ግንቦት 24 2007

በልማዱ፤ በሕጋዊዉም አሠራር ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫዉን ዉጤት አንቀበልም ካሉ፤ በየደረጃዉ ላሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፅሕፈት ቤቶች አቤት ማለት፤ አቤቱታቸዉ ተቀባይነት ካጣ የመክሰስ መብት አላቸዉ። የመድረክና የሠማያዊ ፓርቲ ባለሥልጣናት ግን ሁለቱንም ለማድረግ የተዘጋጁ አይመስሉም።

https://p.dw.com/p/1FaKT
ምስል DW/Y.-G. Egziabhare

የኢትዮጵያ ምርጫ ጊዚያዊ ዉጤትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ አብቅቶ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ዉጤት ገዢዉ ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ማሸነፉ ተነግሮ፤ ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘበት ሃያ-አራተኛ ዓመትም ተከበረ። የተቃዉሚ ፓርቲዎች ትችት ወቀሳ፤ ዉግዘት፤ የደጋፊዎቻቸዉ ቅሬታ ግን እንደቀጠለ ነዉ። ሌላ ሳምንት። ግን አሮጌ ዑደት።የተቃዋሚዎች ትችት ወቀሳ መነሻ፤ የወደፊት ዕቅድ፤ ተስፋ ሥልታቸዉ መድረሻችን ነዉ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈዉ ሮብ-ይፋ ባደረገዉ ጊዚያዊ ዉጤት መሠረት ኢሕአዴግ እና «አጋር» የሚባሉት የፖለቲካ ማሕበራት መቶ በመቶ አሽንፈዋል። የምርጫዉ ሒደትም በቦርዱ ሊቀመንበር በፕሮፌሰር መርጋ በቃና ቋንቋ የተረጋጋ ነበር።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ ባጭሩ) አመራር አባል ዶክተር መረራ ጉዲና ግን «ምርጫ መች ነበር» ይላሉ-እስከነአክታቴዉ?

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሥለሺ ፈይሳም ነፃነት በሌለበት ምርጫም፤ አማራጭም ሊኖር አይችልም ነበር። አልነበረምም ባይ ናቸዉ።የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ሥለ ምርጫዉ ሒደትና ዉጤት እስካሁን በይፋ ያወጣዉ መግለጫ የለም። የፓርቲዉ ሊቀመንበር አቶ አበባዉ መሐሪ እንዳሉት ፓርቲያቸዉ አቋሙን ነገ-በይፋ ያሳዉቃል። በግላቸዉ ግን የምርጫዉን ሒደትና ዉጤት አይቀበሉትም።

Pressekonferenz Merga Bekana
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የገዢዉ ፓርቲ (የኢሕአዲግ)ም የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሥለሚሰነዘርባቸዉ ወቀሳና ትችት መልስ እንዲሰጡ በሥልክ ለማነጋገር ሞክረን ነበር። አንዳዶቹ ሥልካቸዉ አይነሳም፤ የሌሎቹ ዝግ ነዉ፤ ሌሎቹ ደግሞ «ሥብሰባ ላይ ነን» የሚል መልስ ሰጥተዉናል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች በምርጫዉ ማግሥት የገለፁት፤ ጫና፤ ወከባና ማጭበርበር ከነበር፤ እንደሚኖር በምርጫ ዘመቻ ወቅት እንዴት መገመት አልቻሉም-ወይም ከገመቱ ደግሞ በምርጫዉ ለምን ተወዳደሩ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሥለሺ ፈይሳ መልስ አላቸዉ።የመድርክ አመራር አባልና የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ያክሉበታል። ሕዝብን ማንቃት፤ በደሉን ማጋለጥ ችለናል እያሉ።ዶክተር መረራ እንደሚሉት በኦፌኮና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥረት ለመብቱ መከበር መታገል የጀመረዉ ሕዝብ በተለይም የዩኒቨርሲርስቲ ተማሪዎች ድምፅ በተሠጠበት ዕለት የጀመሩት መብትን የማስከበር ትግል በአንዳድ አካባቢዎች እስካሁንም እንደቀጠለ ነዉ። በወጣቶቹ ላይ የሚደርሰዉም በደል እንዲሁ።

Äthiopien Blue party Pressekonferenz
ምስል DW/Yohannes G/Egziabher

እስካሁን በሥልጣን ላይ ባለዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛዉ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉ ባለፈዉ ሳምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከእንግዲሕ «አንድም አንድ ሆነዉ ጥንካሬያቸዉን ማሳየት፤ አለያም ጨርሶ መፍረስ አለባቸዉ» ብለዉ ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባንድ መቆሙን እንደሚያምኑበት ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። የሞከሩም አሉ። ዳር ሲያዘልቁት ግን አልታዩም።

የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባዉ መሐሪ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለዉን ልዩነት እንደ ትልቅ ድክመት ይቆጥሩታል።

ዶክተር መረራም ይሕን ድክመት «ቀዳዳ» ይሉታል።አቶ ሥለሺ ግን በአሰልቺዉ አገላለፅ «ተባበርንም ተሠባበርንም» የገዢዉን ፓርቲ ጫና ለማስወገድ ለዉጥ-የለዉም ባይ ናቸዉ።

በልማዱ፤ በሕጋዊዉም አሠራር ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫዉን ዉጤት አንቀበልም ካሉ፤ በየደረጃዉ ላሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፅሕፈት ቤቶች አቤት ማለት፤ አቤቱታቸዉ ተቀባይነት ካጣ የመክሰስ መብት አላቸዉ። የመድረክና የሠማያዊ ፓርቲ ባለሥልጣናት ግን ሁለቱንም ለማድረግ የተዘጋጁ አይመስሉም።

ይላሉ ዶክተር መረራ። አቶ ስለሺም ቀጠሉ።የምርጫዉ አጠቃላይ ዉጤት በርግጥ ገና አልተነገረም። ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም፤ ብዙ ታዛቢዎችም እንደሚሉት አጠቃላዩ ዉጤት ባለፈዉ ሮብ ከተገለፀዉ ብዙም የተለየ አይሆንም። መቶ በመቶ ወይም እንደ 200299,6 በመቶ ለኢሕአዴግና ለተባባሪዎቹ። በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ምንም ወይም ከ0,5 በታች ድምፅ ያስመዘገቡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቶ ግርማ ሰይፉ እንዳሉት ባይፈርሱ እንኳን የወደፊት ዕጣ-ፈንታቸዉ አጠያያቂ ነዉ።

Äthiopien Medrek PK Wahlen
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የመኢአድ ፕሬዝደንት አቶ አበባዉ መሐሪም ሠላማዊዉ ትግል በነበረበት መቀጠሉን ይጠራጠራሉ።አቶ ሥለሺ ፈይሳ ተቃራኒዉን ነዉ የሚሉት። አዲሱ ፓርቲያቸዉ (ሠማያዊዉ) በሠላማዊዉ ትግል እስካሁን ያስገኘዉ ዉጤት ብዙ ነዉ። ሠላማዊ ትግል ምርጫ ብቻ አይደለም። ወደፊት ይቀጥላልም።

ዶክተር መረራም መድረክ የእስካሁን ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ባይ ናቸዉ።መጪዉን ለማየት ያብቃን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ