1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥትና ኦብነግ ድርድር

ማክሰኞ፣ የካቲት 6 2010

በኬንያ ባለስልጣናት አደራዳሪነት በሚስጢራዊ ቦታ የተከወነው የሁለቱ ወገኖች ንግግር ከ30 ዓመታት በላይ ለቆየው ጠብ፣ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል ሰበብ ለሆነው ፍጥጫ እልባት ከመስጠት አልፎ በመላው የአፍረቃ ቀንድ የሰላምና ደህነት ሁኔታ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለው የገመቱ ተንታኞችን ትኩረት ስቧል-ሙሪዚ ሙቱጋ አንዱ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2sdX2
Kenia Skyline Nairobi
ምስል picture-alliance/World Pictures/Photoshot/P. Phipp

የኢትዮጵያ መንግሥትና ኦብነግ ድርድር

የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ሶስት ቀናትን የፈጀ ድርድር በኬንያ ናይሮቢ አድርገዋል፡፡

በኬንያ ባለስልጣናት አደራዳሪነት በሚስጢራዊ ቦታ የተከወነው የሁለቱ ወገኖች ንግግር ከ30 ዓመታት በላይ ለቆየው ጠብ፣ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል ሰበብ ለሆነው ፍጥጫ እልባት ከመስጠት አልፎ በመላው የአፍረቃ ቀንድ የሰላምና ደህነት ሁኔታ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለው የገመቱ ተንታኞችን ትኩረት ስቧል-ሙሪዚ ሙቱጋ አንዱ ናቸው፡፡

ሙሩዚ ሙቱጋ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንዳይከሰቱ  በከላለከል፣ቁጥራቸውን በመቀነስ እና ተፈጥረው ሲገኙም መፍትሄ በመፈለግ ስራ የተሰማራው የኢንተርናሽናል ክራይስ ግሩፕ የአፍሪቃ ቀንድ ከፍተኛ ተንታኝ ናቸው፡፡የሁለቱ ወገኖች የአሁን ንግግር ዓመታትን ከፈጀው ግጭት አንጻር ያለውን አንድምታ አጋርተውኛል፡፡

‹‹ይሄ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ፣የተወሳሰበና ጥልቅ ስር መሰረት ያለው ግጭት መሆኑን እናውቃለን፡፡ባለፉት ጊዜያት ሰለማዊ መፍትሄ ለማግኘት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ በጦር ሊፈታ እንደማይችል ወደ መገንዘቡ እንደመጡ አስባለሁ፡፡ስለሆነም የአሁኑን ጥረት በመልካምነት ሊቀበሉት የሚገባ ነው፡፡››

የኢትዮጵያ መንግስት እና የአቦነግ ግጭት ለብዙ ንጹሃን ሞት፣አካል መጉደል እና ማፈናቀል ምክንያት ስለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በመብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘንድ ተተንትኗል፡፡የሁለቱ ወገኖች ድርድር በተሰማበት ወቅት -ድርድሩ ከፖለቲካዊ አጀንዳው ጎን ለጎን የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ወገኖች ዕጣ እና ፍትህ ጉዳይም ሊያካትት ይገባል የሚሉ አስተያየቶች በተለያዩ ገጾች ላይ ተነበዋል፡፡

Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden
ምስል DW/J. Jeffrey

ሙሩቲ ሙቱጋ እንዲህ ያለውን ነጥብ መነሳቱን በአወንታዊነት ይቀበሉታል ፡፡ሆኖም ጥያቄው ሰላም ይቅደም ወይስ ፍትህ? ከሚለው የተሻለውን ቅደም ተከተል ከመምረጥ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ የቅደም ተከተል ጥያቄ ይመስለኛል፡፡መጀመሪያ ሰላም እንዲረጋገጥ አድርገህ ቆየት ብለህ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ እንደሁለተኛ ርምጃ በተፈጸሙ የከፉ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ዙሪያ ችሎት እንዲቋቋም ትጥራለህ ወይስ ሌላ፡፡ሰላም እና ፍትህ ተነጣጥለው የሚቆሙ ጉዳዮች አይደሉም ሁኔታው የትኛው ይቅደም የሚል የቅደም ተከተል ጥያቄ ነው፡፡››

የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦብነግ የድርድር ዜና የተለያዩ ስጋቶች ተደቅነውበታል፡፡የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በአደጋ ውስጥ ይጥላል የሚሉ ድምጾች ከኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ ተሰምተዋል፡፡ሊታረቅ የማይችል የሚመስለው የሁለቱ ቡድኖች ፍላጎት በምን ሁኔታ ወደ አንድ መዳረሻ ሊመጣ እንደሚችል በርካታ ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም-የድርድሩ ውጤታማነትም ገና አለየለትም፡፡

የኢንተርናሽናል ክራይስ ግሩፕ ከፍተኛ አጥኚ ሙሩዚ ሙቲጋ ሁሉም አካላት የጋራ መግባቢያ ነጥብ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ልክ የጉዳዩ ውጤታማነት አንደሚወሰን ዕምነታቸውን ያገራሉ፡፡

‹‹በስተመጨረሻ ሚዛን የሚደፋው ጉዳይ የሁለቱ ወገኖች ቅንነት ነው፡፡ሁለቱም ጎኖች የየራሳቸው የሆነ ፍላጎት አላቸው፡፡ሆኖም በትንሹ በሰላም ጥያቄ፤በተወሰነ ደረጃ የማህበረሰብ ስምምነት ጥያቄ ሁለቱን ወገኖች ለድል የሚያበቃ የጋራ ነጥብ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሆኖም በተቃዋሚ ወገኖች ዘንድ የሚነሱ ማሳሰቢያዎችም በቁምነገር መጤን አለባቸው -በቸልታ ሊታለፉ አይገባም፡፡››

ሀብታሙ ስዩም

ሸዋዬ ለገሠ