1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢቦላ ሕክምና

ዓርብ፣ የካቲት 13 2007

ምንም እንኳን ለኢቦላ ተብሎ በተለይ የተሰራ መድኃኒት ባይኖርም በሽታው በቶሎ ህክምና ካገኘ የኅመምተኛው ሕይወት የመትረፍ ዕድል ከፍተኛ ነው።

https://p.dw.com/p/1Ef2g
Ebola in Liberia (Behandlung im Krankenhaus)
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

የኢቦላ ምርመራ ማድረግ የሞት ፍርድ አይደለም። በሽታውን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ማለትም፤ በማስታገሻ ክኒኖች ኅመምን በመቀነስ፣ ምርቀዛን የሚከላከሉ መድሐኒቶች (አንቲባዮቲክስ) በመስጠት እና የአመጋገብ ስልትን በመቀየር ማከም ይቻላል። ኅመምተኞች ውኃ፣ ሻሂ፣ እና ሾርባ በደንብ መጠጣታቸውም ወሳኝ ነው። አልኮልን ማስወገድ ያሻል። የኢቦላ ታማሚዎች የሚታከሙት ለብቻ በተነጠለ የህክምና ክፍል ነው። በእርግጥ ሐኪሞች እና አስታማሚዎች ከአናታቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ «የጨረቃ ላይ ተጓዥ መስለው» እንደተሸፋፈኑ መመልከት ይረብሽ ይሆናል፤ ሆኖም የሐኪም ቤት ሠራተኞች በአጠቃላይ ራሳቸውን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ያም ማለት የሰውነታቸው እያንዳንዷ ሴንቲሜትር መሸፈን አለባት። በእዚህ መልኩ ነው ኅመምተኛውን መንከባከብ የሚችሉት። በምዕራብ አፍሪቃ የኢቦላ ኅመምተኞች የሚታከሙበት የተነጠሉ የህክምና ክፍሎች ይዞታ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል አሳይተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢቦላ ተሐዋሲ ከተጠቁ ኅመምተኞች መካከል ግማሽ ከመቶ ያህሉ በሕይወት መቆየት ችለዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ከኢቦላ በሽታ ካገገመ ሰው ደም አለያም ሴል የሰውነት በሽታ ተከላካይ ፕሮቲኖችን በቤተሙከራ ነጥሎ በማውጣት በተዘጋጁ ክትባቶች ኅመምተኞች ታክመዋል። የዚህ አይነቱ ህክምና በመጠኑ ውስን ከመሆኑም በተጨማሪ በስፋት አይገኝም። ሌላ አይነት የህክምና ዘዴዎች እና መድኃኒቶች ምርምር እየተደረገባቸው ነው።