1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

‘ዜና እረፍት’ ወ ‘ዳግማይ ትንሳዔ’

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2010

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወዳጅነት እንደ ፊልም ተዋናይ ወይም እንደ ምናባዊ የተረት ገጸ ባሕርይ ነው። የሚፀልዩላቸው እናቶች አሉ፣ ወጣቶች ባጭሩ እንዳይቀጩ ሊመክሯቸው ይዳዳቸዋል፣ የሕዝብ ማመላለሻ ሹፌሮች ምስላቸውን መስታወታቸው ላይ እንደጌጥ ይለጥፉታል። የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩላቸዋል።

https://p.dw.com/p/303qM
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የተቃውሞ ንቅናቄ መሪዎች በነበሩ አስተባባሪዎች “ለውጡን እንደግፍ፤ ዴሞክራሲን እናበረታታ” በሚል ርዕስ ነገ (ሰኔ 16/2010) አዲስ አበባ ውስጥ ትልቅ ሰልፍ ተጠርቷል። ሰልፉ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ “የቀን ጅቦች” አሉ በማለታቸው ለእርሳቸው ድጋፍ ለማድረግ ቢሆንም፣ በውስጠ ታዋቂነት “የቀን ጅብ” በመባል የተጠቀሱትን እና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ወይም አባላትን ይሆናል በሚል የታመነባቸውን አካላት ለማውገዝም ጭምር ነው። 

አጀማመሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አጋርነትን ማሳየት ነበር። ቅርፅ በማስያዙ ሒደት ውስጥ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ‘የለውጥ አጋርነት’ ነው ሲሉት፥ የመንግሥት ሚድያዎች ደግሞ ሕዝባዊ ‘የመንግሥት አጋርነት’ ሊያስመስሉት እየጣሩ ነው። የሆነ ሆኖ ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ ኢሕአዴግ ላይ ሸፍቶ ነፍጥ ያነሳውን የግንቦት ሰባት ጦር መሪ አንዳርጋቸው ፅጌ የፍቺ አቀባበል ሲያስተባብር የነበረ፣ የኢሕአዴግ ቀንደኛ ተቃዋሚ መሆኑ ትዕይንቱን እንቆቅልሽ ያደርገዋል። የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች የኢሕአዴግን ሊቀ መንበር መደገፋቸው ምን ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ሁለቱ ወገኖች… 

የሰልፉን መጠራት ተከትሎ በዚህ ሳምንት ሁለት ጫፍ የያዙ አጫጭር የጽሑፍ መልዕክቶች ሳስተናግድ ነበር። 
የመጀመሪያው፣ «ከዶ/ር ዐብይ ጎን በመቆም ለአገራችን ያላቸውን ራዕይ እና አቅጣጫቸውን እደግፋለሁ። እባክዎ እርስዎም ይህንኑ መልዕክት ለዐሥር ሰዎች በማጋራት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልዎትን ድጋፍ ያረጋግጡ» ይላል።

ሁለተኛው፣ «ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ድጋፌን ከመስጠቴ በፊት ሕገ መንግሥቱን እና የዘውግ ፌዴራሊዝማቸውን እንደማልቀበለው ልነግራቸው እፈልጋለሁ። እንዲሁም መረን የወጣ እና አድማጩን እየጨፈለቀ ያለውን "የልማት ፈረስ" ግልቢያቸውንም አልቀበልም። እንደ መብራት፣ ቴሌኮም፣ የባቡር መንገድ ወዘተ… የመሳሰሉትን የመንግሥት ድርጅቶች ለግል ይዞታ ለማዛወር ታላቋን ብሪታንያ ከኢንደስትሪ አብዮት በኋላ 200 ዓመታት ወስዶባታል። ታዲያ ኢትዮጵያ ስለምን ገንዘብ የሚታለሙ ድርጅቶቿን ለጥንብ አንሳዎች አሳልፋ ትሰጣለች? የውጭ ምንዛሬው እጥረት እንደሆነ እዚሁ የተፈጠረ ችግር ነው። ጥፋቱ የብሔራዊ ባንክ የ28 ቀኑ ባለ27% መመሪያ ነው። መፍትሔው ቁጥጥሩን ማንሳት እና የውጭ ምንዛሬውን ጉዳይ በነጻ ገበያ መወሰን ነው። እባክዎ ይህንን መልዕክት ለዐሥር ሰዎች ያዳርሱ» የሚል ነው።

በሁለቱ መልዕክቶች መካከል ያለው ልዩነት እንዲህ ነው። የመጀመሪያው (ብዙ ሰዎች የላኩት) መልዕክት እጥር ምጥን ያለ የድጋፍ ጥሪ ብቻ ነው። የድጋፉን ዝርዝር ምክንያት ተቀባዮች ያውቁታል በሚል የተተወ ይመስላል። ሁለተኛው ግን በቀጥታ “አልደግፍም” ማለትን ሸሽቶ ቅድመ ሁኔታዎቹን አስቀምጧል። ዝርዝሩ በውስብስብ የቴክኒክ ቃላት የታጨቀ ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን መተቸት እንከን መስማት ከማይፈልገው ደጋፊያቸው ብዛት አንፃር በጣም አስፈሪና ከባድ ነገር ነው።  አምና በዚህ ጊዜ የሕዝብ አውቶቡስ ውስጥ አጠገባችሁ ለቆመ አንድ እንግዳ ሰው ኢሕአዴግን ብታሙለት፣ መልሶ የሚያማላችሁ የመሆኑ ዕድል ሰፊ ነበር። ዘንድሮ ወሬያችሁ ያለፀብ የሚቋጨው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥም በመልካም ካነሳችሁ ብቻ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወዳጅነት እንደ ፊልም ተዋናይ ወይም እንደ ምናባዊ የተረት ገጸ ባሕርይ ነው። የሚፀልዩላቸው እናቶች አሉ፣ ወጣቶች ባጭሩ እንዳይቀጩ ሊመክሯቸው ይዳዳቸዋል፣ የሕዝብ ማመላለሻ ሹፌሮች ምስላቸውን መስታወታቸው ላይ እንደጌጥ ይለጥፉታል። የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩላቸዋል። እንዲያውም ድምፅ አውጥተው የሚቃወሟቸው በብዛት በፊት የኢሕአዴግ ደጋፊ የነበሩት ሰዎች ናቸው። ለዚህ ሁሉ ያበቃቸው ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ወይም የተቃዋሚ ወኪል መስለው መታየታቸው ነው። 

‘ዜና እረፍት’ ወ ‘ዳግማይ ትንሳዔ’

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሕዝባዊ የለውጥ ጥያቄ ግፊት፥ በኢሕአዴግ አባላት የተመረጡ መሪ ናቸው። ተጠሪነታቸው አንድም ለለውጡ ግፊት፣ አንድም ደግሞ ደግሞ ለኢሕአዴግ ነው። በአንድ በኩል የኢሕአዴግን የቀደመ መንገድ አሽቀንጥረው ሲጥሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኅልውናውን ያስቀጥላሉ። ከተቃዋሚው ጎራ ያሉ ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው ውስጥ ያሉ ነቃፊዎቻቸው ኢሕአዴግ መሆናቸውን ማስታወስ አይፈልጉም። 

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘው የመጡት መንገድ በአንድ በኩል “ኢሕአዴግ ያጠፋውን ኢሕአዴግ ማረም አለበት” የሚል አካሔድ፥ በሌላ በኩል “ኢሕአዴግ የሕዝብን ጥያቄ በትክክል በመመለስ ከመክሰም መትረፍ አለበት” የሚል ነው። ይህንን የተረዱ ጥቂት ተቃዋሚዎች የድምፃቸውም፣ የትግላቸውም መቀማት ያስቆጫቸዋል። ይህንን ያልተረዱት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም የሕወሓት አባላት እና የደኢሕዴን አባላት በከፊል ይቃወሟቸዋል። ተቃውሟቸው ምናልባት ከፖለቲካ የበላይነት አባዜ ወይም ከሙስና ተጠርጣሪነት ፍራቻ የመነጨ ይሆናል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃውሞውን ለራሳቸው ድጋፍ ማሰባሰቢያ አድርገው ተጠቅመውበታል።  

አሁን አንድ ነገር እርግጥ ሆኗል። የቀድሞው ኢሕአዴግ ሞቷል። በሕወሓት የበላይነት የሚታማው ኢሕአዴግ የመመለስ ዕድሉ ጠባብ ነው። አዲሱ ኢሕአዴግ በአዲስ ሕይወትና ስጋ እየተነሳ ነው። በ1993 የሕወሓትን መሰንጠቅ ችሎ አይዘልቅም የተባለው ኢሕአዴግ አንድ ፈላጭ ቆራጭ - መለስ ዜናዊን ይዞ ተነስቷል። በምርጫ 1997 አከተመለት የተባለው ኢሕአዴግ አፈር ልሶ ተነስቷል። አሁንም፣ አምና እና ካቻምና ካንዣበበበት በኃይል የመወገድ አደጋ፣ እንደወትሮው በትዕቢት ሳይሆን “የሕዝብ ጥያቄ እመልሳለሁ” ብሎ፣ ምሎ፣ ተገዝቶ፣ ተንበርክኮ፣ ሞቶ ተነስቷል። ለዚህ ምስክር የሚሆነን ጠቅላይ ሚኒስትሩን "አበጀህ" ለማለት ነገ የተጠራው ሰልፍ ነው።
በፍቃዱ  ዘኃይሉ

አዜብ ታደሰ