1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር

እሑድ፣ ሚያዝያ 8 2009

ኢህአዴግ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ከሚያደርገው ድርድር ጎን ለጎን ለብቻው መደራደር እንደሚፈልግ ያሳወቀው መድረክ ፣ የሚደራደረውም የታሠሩ መሪዎቹ ሲፈቱ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ እና ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪ ሲመራ እንደሚሆን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/2bG5G
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

Diskussionsforum 160417 Verhandlung zwischen EPRDF&Äth.Oppositionsparteien - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግና 21 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥር 10 ፣2009 ዓም የጀመሩት የቅድመ ድርድር ውይይት ሁሉንም ተቃዋሚዎች ይዞ መቀጠል አልቻለም።ትልቁን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ መድረክን ጨምሮ ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድሩን ማን ይምራ በሚለው ጉዳይ ላይ ባለመስማማታቸው ራሳቸውን  ከድርድሩ አግለዋል።ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በመጀመሪያ ከድርድሩ መውጣቱን ያሳወቀ ፓርቲ ነው።ኢህአዴግ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ከሚያደርገው ድርድር ጎን ለጎን ለብቻው መደራደር እንደሚፈልግ ያሳወቀው መድረክ ፣ የሚደራደረውም የታሠሩ መሪዎቹ ሲፈቱ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ እና ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪ ሲመራ እንደሚሆን ገልጿል።ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት መአሕድም ነፃ እና ገለልተኛ አደራዳሪ የማይኖር ከሆነ በድርድሩ እንደማይሳተፉ ገልፀው ራሳቸውን አግለዋል።ኢህአዴግ ገለልተኛ የሚባል ወገን የለም ሲል ድርድሩ በተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በዙር ይመራ ካለ በኋላ ደግሞ ሌሎች ስድስት ፓርቲዎች ያለ አደራዳሪ በሚደረግ ድርድር አንስማማም ብለው ነበር።ሆኖም በዚህ ሳምንት ሰኞ በተካሄደው ስምንተኛው ዙር ውይይት አምስቱ ድርድሩ ከመካከላቸው በሚመረጡ አባላት እንዲመራ በቀረበው ሀሳብ ተስማምተዋል። ኢህአዲግ እና ድርድሩ በዙር እንዲመራ ተስማምተው የነበሩ ሌሎች 13 ፓርቲዎችም ድርድሩን የሚመራ ኮሚቴ ከየፓርቲዎቹ ተውጣጥቶ እንዲቋቋም ተስማምተዋል።ኢህአዴግ እና 18 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመካከላቸው በሚመርጧቸው አባላት እንዲመራ የተስማሙበት ድርድር ፣  እና ፋይዳው የዛሬው እንወያይ ትኩረት ነው።

ኂሩት መለሰ

ልደት አበበ