1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ እና ሩስያ

ዓርብ፣ ሰኔ 1 2010

ሩስያ ለአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት ዋነኛዋ የጦር መሣሪያ አቅራቢ ናት።  ፓውል ስትሮንስኪ በዩናይትድ ስቴትሱ ካርኔጅ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም የሩስያ ጉዳዮች አዋቂ እንደሚሉት ይህ የሆነበት ምክንያት ከሩስያ በቀላሉ መሣሪያ ማግኘት በመቻሉ ነው።

https://p.dw.com/p/2zBBU
Russland St. Petersburg Treffen Präsident Zentralafrikanische Republik und Vladimir Putin
ምስል Imago/TASS/Russian Presidential Press and Information Office/M. Klimentyev

አፍሪቃ እና ሩስያ

በአፍሪቃ እምብርት ላይ የምትገኘው ትልቂቷ  ኮንጎ የምዕራባውያን አጋር ተደርጋ ነበር የምትወሰደው። አሁን ግን መንግሥት ሌሎች አጋሮች የመፈለግ አዝማሚያ ያለው ይመስላል። የኮንጎ ጎረቤት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክም ተመሳሳይ ሙከራ ላይ ናት። የዶቼቬለው ዳንኤል ፔልስ በቀጣዩ ዘገባው ሩስያ በአፍሪቃ ወታደራዊ ትብብርን ለማጠናከር የምታደርግውን ሙከራ ያስቃኘናል።ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
ኮንጎ እና ሩስያ ፣ሩስያ የጦር መሣሪያዎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለኮንጎ ጦር እንድታቀርብ በጎርጎሮሳዊው 1999  ፣ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የፈረንሳዩ ራድዮ ጣቢያ ራድዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ዘገባ ያስረዳል። ስምምነቱ የኮንጎ ወታደሮችን ማሰልጠንንም ያካትታል። ሆኖም ይህ ስምምነት ፍጹም ተግባራዊ አልሆነም። የኮንጎ መንግሥት አሁን ይህን ለመቀየር የሀገሪቱን ምክር ቤት ማማከር ይፈልጋል። ኮንጎን በስተሰሜን የምታዋስናት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክም ከሩስያ ጋር በትብብር እየሰራች ነው። ሩስያ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው ለዚህች ሀገር  የጦር መሣሪያዎችን ጥይቶችን እና የጦር አስልጣኞችን እንድታቀርብ ተፈቅዶላታል። ይህንኑ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈው ታህሳስ ደግፏል።  ሩስያ እነዚህን ሀገሮች የመረጠችው በደንብ አስባበት ነው ይላሉ ፈረንሳዊው የአፍሪቃ ጉዳዮች አዋቂ ሮላንድ ማርሻል። 
«በነዚህ ሀገራት እና በምዕራባውያን መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የሰፈነበት ነው። ሩስያ ወደ ነዚህ ሀገራት የመግባት ፣ተጽእኖ የማድረግ እና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎችን የማሳደግ እድል አላት።»
ወታደራዊው ትብብር የመጀመሪያው ይሆናል።  የጉዳዩ አዋቂዎች ሩስያ ይህን በመጠቀም የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪዋን ማጠናከር እንደምትፈልግ ያምናሉ። ቻተም ሀውስ በተባለው የብሪታንያው የጥናት እና ምርምር ድርጅት ጥናት መሠረት ወደ አፍሪቃ የሚላከው የሩስያ የጦር መሣሪያ መጠን ወደ ክፍለ ዓለሙ ከሚገባው የጦር መሣሪያ 3 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው። ያም ሆኖ በአፍሪቃ አሁን የጦር መሣሪያ ገበያ እያደገ ነው። ሩስያ ለአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት ዋነኛዋ የጦር መሣሪያ አቅራቢ ናት።  ፓውል ስትሮንስኪ በዩናይትድ ስቴትሱ ካርኔጅ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም የሩስያ ጉዳዮች አዋቂ እንደሚሉት ይህ የሆነበት ምክንያት ከሩስያ በቀላሉ መሣሪያ ማግኘት በመቻሉ ነው።
«ለአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት የምዕራባውያንን የጦር መሣሪያዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የሩስያ የጦር መሣሪያ ሽያጭ እንደ አብዛኛዎቹ ሀገራት አዳጋች አይደለም። ሩስያ የጦር መሣሪያ ሽያጭን ከሰብዓዊ መብቶች እና በሀገራቱ ከሚካሄዱ የተለያዩ አካባቢያዊ ግጭቶች ጋር አታያይዝም። ይህም ገበያው እንዲሰፋ እድሉን ሰጥቷታል። የመሣሪያ ሽያጭ ላይ ቁጥጥሯን እንድታጠናክር በተመድ ተገዳለች።»
በዚህ መንገድም እንደ ስትሮንስኪ ሩስያ አሁን በአፍሪቃ የቀድሞ ቦታዋን ለማግኘት እየጣረች ነው። 
«ሩስያ በአፍሪቃ ተጽኖዋን ለማስፋት እየሞከረች ነው። ከሶቭየት ህብረት መፈራረስ በኋላ በ1990ዎቹ ከአፍሪቃ አፈግፍጋ ነበር። ላለፉት 20 እና 25 ዓመታት ሩስያ በአፍሪቃ ዋነኛዋ ተዋናይ አልነበረችም። አሁን ግን ለመመለስ እየሞከረች ነው።»
ሩስያ በጦር መሣሪያ ሽያጭ ብቻ አትወሰንም። ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መጠነ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ኮባልት ወርቅ እና አልማዝ ዋነኛዎቹ የሀገሪቱ የማዕድን ሀብቶች ናቸው። ጎረቤት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክም አልማዝ ለውጭ ገበያ ታቀርባለች። ባለፈው መጋቢት በሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማስታወቂያ ክፍል ምክትል ሃላፊ አርትዮም ኮዝሂን ሩስያ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለጋራ ጥቅሞች የማዋል እድሎችን እየመረመረች መሆኑን ተናግረዋል። ይህ አጋጣሚም ሩስያ ለውጭ ገበያ ለምታቀርባቸው ምርቶች የሚያስፈልጋትን ጥሬ እቃ የሚያስገኝላት ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎችዋን የማስፋት እድልም ይፈጥርላታል። ፈረንሳዊው የአፍሪቃ ጉዳዮች አዋቂ ማርሻል እንደሚሉት ጥቅሙ ከሩስያ ጋር ለመተባበር ለተስማሙት የአፍሪቃ መንግሥታትም ጭምር ነው። 
«ፈተና ውስጥ የሚገኙ መንግሥታት ከሩስያ ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት የሕይወት ዘመን ዋስትና ሊሆንላቸው ይችላል። ለነርሱ ጥሩ ዋጋ አለው። ስለዚህ እነዚህ መንግሥታት ሩስያዎችን ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በማስገባት ምዕራባውያን መንግሥታት ይበልጥ ለጋሽ በመሆን በአካባቢው የሩስያን ተጽእኖ እንዲያደበዝዙ የሚደራደሩበትን ዋጋቸውን ከፍ ያደርጋሉ።»
ሩስያ ከኮንጎ እና ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችው ትብብር የረዥም ጊዜ ተጽእኖ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስቸግራል። ሆኖም ታዛቢዎች እንደሚሉት ሩስያ በሁለቱ ሀገራት ብቻ ተወስና እንደማትቀር ይልቁንም በአፍሪቃ ትብብርዋን አጠናክራ መቀጠል መፈለጓን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚህም የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌይ ላቭሮቭ በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ6 የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ተጓዳኝ የአፍሪቃ አገራት  ያደረጉት ጉብኝት የዚህ ማሳያ ነው። 

Zentralafrikanische Republik - Antibalaka Kämpfer
ምስል Getty Images/AFP/A. Huguet
Militär Kongo
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS/D. Honl

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ