1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ እና ሕንድ ጉባኤ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2008

ሶስተኛዉ የአፍሪቃ እና ሕንድ ጉባኤ ባለፈዉ ሰኞ ኒዉዴሊ ላይ ተከፍቷል። በሕንድ እና አፍሪቃ መካከል የሚያኬደዉ የሁለትዮሹ ንግድ በየዓመቱ 70 ቢሊየን ዶላር ይገመታል። በዚህ ሳምንት የሚካሄደዉ ጉባኤ ይህን የንግድ ልዉዉጥ ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ባለስልጣናት ጠቁመዋል።

https://p.dw.com/p/1Gw7k
Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Außenminister
ምስል picture-alliance/epa

[No title]


ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ሁለት ተመሳሳይ ጉባኡዎች 15 የአፍሪቃ መሪዎች ነበር የተገኙት። ዘገባዎች እንደሚሉት በዚህ ጉባኤ ግን ከ40 በላይ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ተገኝተዋል። ኢትዮጵያም የንግድ ሕብረተሰቡ ወኪሎች የተካተቱበት የልዑካን ቡድኗን በዚሁ ጉባኤ ተገኝቶ የንግድና የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ላይ ከአጠቃላዩ የሕንድ አፍሪቃ ጉባኤዉ በተጓዳኝ የሁለትዮሽ ግንኙነቷን እንደምታጠናክር ተገልጿል።
የሕንድ እና አፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ የሁለቱን ወገኖች የቆየ ትሥሥር ማሳያ እንደሆነ ነዉ የጉባኤዉ ይፋዊ ድረገጽ የሚያመለክተዉ። በፀረ ቅኝ አገዛዝ እና አፓርታይድ ትግል የተቆራኙት ሕንድ እና አፍሪቃ፤ አፅናፋዊ ትስስር ያስከተለዉን ተግዳሮት ለመቋቋም እስከሚደረገዉ ጥረት በጋራ ለመቆም መቁረጣቸዉንም መድረኩ ያስረዳል። ሕንድ ራሷን እንደአንድ አህጉር የቆጠረች የሚያስመልሰለዉ የመድረኩ ትንታኔ፤ ድሕነትን፣ በሽታን፤ ማይምነትንም ሆነ ረሀባን ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥረት ሁለቱ ወገኖች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንዳላቸዉም ይዘረዝራል። ከትናንት በስተያ ሰኞ ዕለት ኒዉዴሊ ላይ በይፋ የተከፈተዉ ሶስተኛዉ የሕንድ እና አፍሪቃ ጉባኤ፤ በይበልጥ የኃይል ምንጭ ላይ አተኩሮ እንደሚነጋገር ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። የፖለቲካ፤ የኤኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በሚካሄደዉ በዚህ ስብሰባ የ54 ሃገራት ተወካዮች ተገኝተዋል። ከ40 የሚበልጡ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችም የተገኙበት ይህ ጉባኤ በሕንድ እና አፍሪቃ መካከል እስካሁን ያለዉ የንግድ ልዉዉጥ ከፍ በሚልባቸዉ መንገዶች ላይ ይነጋገራል። ከኢትዮጵያ በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዝደንት የተመራ 30 አባላት ያሉት ከንግዱ ማኅበረሰብ በጉባኤዉ ላይ ለመሳተፍ ወደዚያ እንዳመራ በኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ጋሻዉ ደበበ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ጉባኤዉ በመሪዎች እና በሚኒስትሮች ደረጃ ከሚያካሂደዉ ዉይይት በተጨማሪ የሕንድ እና የአፍሪቃን የንግድ ማኅበረሰብ የሚያገናኝ መድረክም አለዉ። ከኢትዮጵያ የሄዱት የንግዱ ማኅበረሰብ ልዑካን ከሕንድ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ከተገኙት ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት አቻዎቻቸዉ ጋር መረጃና ሃሳብ የሚለዋወጡበት አጋጣሚ ነዉ ይላሉ አቶ ጋሻዉ።

የሕንድ እና አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን፤ የቻይና አፍሪቃ፤ እንዲሁም የቱርክ አፍሪቃ መሰል ጉባኤና መድረኮች በተለያዩ ጊዜያት ተካሂደዋል። በዚህ ጉባኤ አማካኝነትም ተሳታፊዎች የበለጠ ባለሃብቶች ወደኢትዮጵያ እንዲመጡና ግንኙነቱም እንዲጠናከር የማድረግ ሚና እንደሚጫወቱም አቶ ጋሻዉ አብራርተዋል። እንደእሳቸዉ ገለፃም ከሕንድ አፍሪቃ ጉባኤ በተጓዳኝ የሕንድ እና የኢትዮጵያ የንግድ ማሕበረሰብን ለማቀራረብና ለማስተሳሰር የሚረዳ የግማሽ ቀን የባለሃብቶች መነጋገሪያ መድረክ ተዘጋጅቷል።

ቻይናም ሆነች ሕንድ በኢንዲስትሪዉ ዘርፍ በፍጥነት እያደጉ የሚገኙ ሃገራት እንደመሆናቸዉ፤ አፍሪቃ ዉስጥ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መነሳሳታቸዉ እና ግንኙነታቸዉን ማጥበቃቸዉ ለጥሬ ሃብት ካላቸዉ ፍላጎት የመነጨ፤ እርስ በርስ የሚያደርጉት ፉክክር ነዉ የሚሉ አሉ። ሁለቱ ሃገራት አፍሪቃ ላይ እየተፎካከሩ ከሆነ፤ በዉድድሩ ለተፈላጊዉ ወገን አማራጭ ያቀርባል ማለት ነዉ ይላሉ አቶ ጋሻዉ፤
የሕንድ አፍሪቃ ጉባኤም ሆነ የኢትዮ ሕንድ የንግድ ማኅበረሰብ መነጋገሪ መድረክ ነገ ሲያበቃ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገኙበት የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ሙምባይ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ ከሕንድ ባለሃብቶች ጋር የሚነጋገርበት መርሃ ግብርም መዘጋጀቱን አቶ ጋሻዉ ደበበ የኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ገልጸዋል። ለአራት ቀናት የሚካሄደዉ የሕንድና አፍሪቃ ጉባኤ ነገ ያበቃል። ሕንድ አፍሪቃ ዉስጥ የኃይል ምንጭን በማስፋፋት እና በቴክኒዎሎጂ ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን አስታዉቃለች።

Neu Delhi Indien-Afrika-Gipfel
ምስል picture-alliance/dpa
Indien-Afrika-Gipfel in Neu Delhi Zuma bei Modi
ምስል Reuters/A. Abidi

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ