1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ስደትን ይገታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል

ረቡዕ፣ ኅዳር 20 2010

አውሮጳውያኑ የአፍሪቃ እና የሜድትራኒያን ቀጣና የሚነሳው የስደት ማዕበል ያሳስባቸው ከያዘ ሰነባበተ። 1.5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ባለፉት ሁለት አመታት የተቀበለችው አኅጉር ፖለቲከኞች መፍትሔ ፍለጋ ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/2oUtC
Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን እና የውጭ መዋዕለ ንዋይ እቅድ


አፍሪቃውያን መንገድ ላይ ናቸው። አንዴ ከሰሐራ በርሐ ሻገር ሲሉም ከሜድትራኒያን ባሕር ሞት አድፍጦ ቢጠብቃቸውም አላመነቱም። በሊቢያ «ገበያ እንደ ባሪያ ቢሸጡም» ከመከራ አሻግረው አውሮጳ አለ ያሉትን የሥራ እና የገቢ ዕድል የሚያማትሩት ጥቂት አይደሉም።  በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት መረጃ መሰረት እንኳ 1,831 ኢትዮጵያውያን፣ 1983 ኤርትራውያን፣ 104,539 ሶማሊያውያን እና 1776 ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች በሊቢያ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ጦርነት እና ግጭት የሚሸሹ፤ የተሻለ የሥራ እና የገቢ ዕድል ፈላጊ ወጣቶችም ናቸው። አውሮጳውያን በበኩላቸው ባሕር አቋርጠው ተገን የሚጠይቋቸውን መቀነስ መቆጣጠርም ይሻሉ። ለዚህ ደግሞ የአውሮጳ ኮሚሽን ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ተጠሪዋ ፌዴሪካ ሞግሔሪኒ «ስደትን እንሻለን ነገር ግን ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ሕጋዊ፣ በፈቃደኝነት የሚደረግ እና በአግባቡ ቁጥጥር የሚደረግበት እንዲሆን እንሻለን።» ሲሉ አኅጉራቸው የምትፈልገውን ለውጥ ይናገራሉ። 

እንዴት?

የአፍሪቃ ስደተኞች ሜድትራኒያንን ከመሻገራቸው በፊት ኒጀር እና ቻድን በመሳሰሉ አገሮች በተዘጋጁ የተገን አመልካቾች መጠለያ ጉዳያቸውን መጨረስ አንደኛው መንገድ ነው። የዚህ እቅድ ባለቤት የፈረሳንዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ናቸው። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገሮች በሚገነቡ የማምረቻ ማዕከላት ስደተኞች ሥራ እንዲያገኙ ማመቻቸት ሌላው ነው። ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ይፋ ያደረገችው "ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ማዕቀፍ" በምሳሌነት ይጠቀሳል። ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ይፋ በተደረገው እቅድ ከሚሰሩት ሥራዎች መካከል በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ የተባሉ ሦስት የማምረቻ ማዕከላት ይገነባሉ። 

Hilfsprojekt im Kongo -  Baustelle der neuen Universitaet in Goma.
ምስል picture alliance/M. Schmidt

የአውሮጳ ኮሚሽን በበኩሉ የአፍሪቃ እና የአካባቢውን አገሮች ከልማት እርዳታ ባሻገር ዘላቂ መዋዕለ-ንዋይን ለማገዝ አዲስ ዕቅድ ይፋ አድርጓል። በአውሮጳ ኮሚሽን 4.1 ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚጀመረው ሲሆን «የውጭ መዋዕለ-ንዋይ እቅድ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ካፒታሉ በሚቀጥሉት ሦስት አመታት ወደ 44 ቢሊዮን ዩሮ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተዘጋጀለት ሰነድ ይጠቁማል። ቶርስተን ኤቨርቤክ የአውሮጳ ኮሚሽን የውጭ መዋዕለ-ንዋይ እቅድ ፅ/ቤት ኃላፊ ናቸው። 

«በአጋሮቻችን አገሮች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሕዝቡን መርዳት እንችላለን። ይህ አገሮቹ እንዲያድጉ እጅጉን ጠቃሚ ነው። እቅዱ ለአውሮጳ ኅብረት ኩባንያዎች ብቻ የታለመ አይደለም። የመዋዕለ-ንዋይ አቅማቸውን ለማሳደግ  በአጋር አገሮች ያሉ ኩባንያዎችንም ይረዳል። የምንሰራውም ከአውሮጳ ባንኮች ጋር ብቻ አይደለም። ከአፍሪቃ ልማት ባንክ ጋር ቅርብ ትብብር አለን።»

በዚህ አዲስ ዕቅድ ድጋፍ ለማግኘት የሚችሉት በአፍሪቃ አሊያም የአውሮጳ ጎረቤት ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በሥራ ላይ የሚውሉ ፕሮጀክቶች ናቸው። ግልጽ ዘላቂ ልማት እንዲሁም ለወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ መሆንም ይገባቸዋል። የመዋዕለ-ንዋይ የሥራ እቅዳቸውን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች የአዋጪነት ጥናት ማቅረብ አለባቸው። ዘላቂነት፣ ጤናማ የገበያ ውድድር ከመመዘኛዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ። ፌዴሬካ ሞግሔሪኒ ከጠንካራ ግለሰቦች ይልቅ ጠንካራ ማኅበረሰቦች ላይ አተኩረናል ብለዋል። 


ሙሉ ዘገባውን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ