1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት ከስደተኞች የሚያገኘው ጥቅም

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2008

አውሮጳ ኅብረት ለስደተኞች የሚያወጣው ገንዘብ በጥቂት አመታት ውስጥ እጥፍ ሆኖ እንደሚመለስለት አንድ ጥናት አመለከተ። የጥናቱ አቅራቢ ፊሊፕ ለግሬይን አውሮጳውያን በስደተኞች የሚገኘው የዚህ ዉጤት ከፍተኛ ተጠቃሚ ለመሆን ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው እና ትክክለኛ ፖሊሲ እንዲያወጡ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/1IrAQ
Islam Ahmed mit Flüchtlingen Willkommenskurs in HWK Cottbus
ምስል HWK Cottbus

[No title]

ስደተኞች ሸክም ሳይሆኑ በደስታ ልንቀበላቸው የሚገባ ዕድል ናቸው ይላሉ ፊሊፕ ለግሬይን። መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ምሁር ጸሐፊና የኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ለግሪይን፣ የስደተኛ ኃይል የምጣኔ ሃብት ጥቅም የሚያስገኝ ሰብዓዊ ኢንቬስትመንት በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥንታዊ ጽሑፍ እንዳስታወቁት በአውሮጳ ህብረት ለስደተኛ ወጪ የሚደረግ ገንዘብ በጥቂት አመታት ውስጥ ትርፍ ይዞ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል። ግሪይን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ስደተኞችን ማስገባት የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን በቀላል ምሳሌ አስረድተዋል።
«የዓለም የገንዘብ ድርጅትን አሃዛዊ መረጃዎች መሠረት ያደረገው የጥናታችን ውጤት እንዳመለከተው ስደተኞችን ለመቀበል ወጪ የሚደረግ አንድ ዩሮ ወይም አንድ ዶላር ከ13 ሳንቲም፤ ከአምስት አመት በኋላ ለአውሮጳ ኅብረት ወደ ሁለት ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ያስገኛል።»
እንደ ጥናቱ ስደተኞች እንደ ሠራተኛ ፣ እንደ ባለሃብት ፣ እንደ አዲስ ነገር ፈጣሪ ፣እንደ ግብር ከፋይ እና ተጠቃሚ ለሚገኙበት ሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለግሬይን በጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደገለጹት ስደተኞች እንደ ስዊድን ኔዘርላንድስ እና ጀርመን በመሳሰሉ የአውሮጳ ኅብረት ሃገራት በአንዳንድ የሥራ መስኮች ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል ያግዛሉ። እናም ለስደተኞች የቋንቋ ስልጠናዎችን ከመስጠቱ ጋር የሥራ ዕድልን እንዲያገኙ እና በአሰቸኳይ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ።
«በአብዛኛዎቹ የአውሮጳ ሃገራት ካሉት ችግሮች አንዱ ተገን ጠያቂዎች ጉዳያቸው ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት ሥራ መሥራት አለመቻላቸው ነው። በዚህ ምክንያትም ለረዥምጊዜ ያለ ሥራ ይቆያሉ። ይህ ደግሞ ክህሎታቸው እንዲሁ እንዲባክን ያደርግል። መደረግ ያለበት ግን ትክክለኛው ችሎታ እንዳላቸው እና እንደሌላቸው ማረጋገጥ ፣ ለሰለጠኑባቸው ሞያዎች እውቅና መስጠት ፣ እንዲሁም የሚመጣጠናቸውን የሥራ ዕድል መስጠት ነው። ብዙውን ጊዜ መንግሥታት ስደተኞችን የሚያሰፍሩት የቤት ክራይ ርካሽ በሆነባቸው ከከተሞች ወጣ ባሉ እና ጥቂት ሥራዎች ብቻ ባሉባቸው አካባቢዎች ነው። ከዚያ ይልቅ ስደተኞችን ሥራ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ማስፈሩ ትርጉም ይሰጣል።»
ከዚህ ሌላ በጥናቱ እንደተገለፀው በዕድሜ የገፉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የሄደባቸው የአውሮጳ ሃገራት ከወጣት ስደተኞች ይበልጡን ተጠቃሚ ይሆናሉ። በአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የጡረታ መውጫ ዕድሜ 65 አመት ላይ የሚደርሱ እና ከዚያ በላይ የሚሆናቸው ዜጎች ቁጥር እስከ ዛሬ 4 አመት ድረስ ወደ 8.5 ሚሊዮን እንደሚያድግ ተተንብዮአል። ይህ አሃዝ ከ14 ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ 27.9 ሚሊዮን ይጠጋል የሚል ግምት አለ። በተለይ በጀርመን ከዛሬ 14 አመት በኋላ የጡረተኛው ቁጥር ከአሁኑ ከአንድ አራተኛ በላይ አድጎ 4.7 ሚሊዮን እንደሚደርስ ፣ የሚሠራው ቁጥር ደግሞ በአንድ ስድሰተኛ ቀንሶ ወደ 8.7 ሚሊዮን ዝቅ እንደሚል ነው ጥናቶች የሚያሳዩት። እናም ይላሉ ለግሬይን የአውሮጳ ሃገራት በተለይ ዕድሜያቸው በ20 ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሆነ ወጣት ስደተኞች በመቀበል ሥስት ትላልቅ ጥቅሞችን ማግኘት ይችላሉ።
«አዳዲስ እና የተለያዩ ነገሮችን ቶሎ የመቀበል አቅም ያላቸው ወጣት ሠራተኞች በዕድሜ የገፉትን ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች ይተካሉ። ስደተኞች በጀርመን እያደገ በመሄድ ላይ ላለው ጡረተኛ ለሚውለው ክፍያ እገዛ ያደርጋሉ ፣ ጡረተኛውንም ይንከባከባሉ። ኅብረተሰቡን መደገፍ ደግሞ ኢንቬስትመንትን እና እድገትን ይደግፋል።»
በጥናት አቅራቢው አስተያየት ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር በቀላሉ ሊዋሃዱ ከሚችሉባቸው ዕድሎች ዋነኛ የሥራ ቦታ ነው። በሥራ ቦታዎች ደግሞ ከሀገሬው ሰዎች ጋር ግንኙነትን ማዳበር እና ቋንቋቸውንም መማር መቻላቸው ብቻ ሳይሆን በመጡበት ሀገር ዋጋ እንዳላቸውም ይሰማቸዋል።

Deutschland Deutschunterricht für Flüchtlinge in Bonn-Bad-Godesberg
ምስል DW/R. Shirmohammadi
Schweden Integration von Migranten Schulunterricht
ምስል Getty Images/D. Ramos


ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ