1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እዲሱ የሮም ሰነድ 

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

አዲሱ ሰነድ የተለያየ የኤኮኖሚ ደረጃ እና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት አባል ሀገሮች እንደ አቅማቸው መጓዝ የሚያስችላቸው አሠራርም ይፈቅዳል ። ይህን አሠራር ሁሉም አባል ሀገራት በመርህ ደረጃ ቢቀበሉትም የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት ግን ስጋት አላቸው ።

https://p.dw.com/p/2a8eQ
EU feiert 60. Geburtstag in Rom
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Medichini

የአውሮጳ ህብረት እና እዲሱ የሮም ሰነድ 

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ባለፈው ቅዳሜ ሮም ኢጣልያ ውስጥ ለአውሮፓ ህብረት ምስረታ መንገድ የጠረገውን የሮም ውል 60 ኛ ዓመት ያከበሩት ያለፈውን ጉዞአቸውን በመገምገም እና የወደፊቱን አቅጣጫ እና ግባቸውን የሚያሳይ አዲስ ሰነድ በማጽደቅ ነበር ። የ27ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች አዲሱን ሰነድ በፊርማቸው ያጸደቁትም በጎርጎሮሳዊው  መጋቢት 25 ፣ 1957 የሮሙ ውል በ6 የያኔው የአውሮጳ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ መሥራቾች በተፈረመበት በሮሙ የካምፒዶልዮ ቤተ መንግሥት ነበር ። ከ6 አሥርት ዓመታት በፊት  የቤልጂግ የፈረንሳይ የኢጣልያ የሉክስምቡርግ የኔዘርላንድስ እና የምዕራብ ጀርመን መሪዎች የሮማውን ውል በፈረሙበት ብዕር የተፈረመው አዲሱ ሰነድ  አውሮጳ የአባል ሀገራቱ የጋራ መጻኤ እድል መሆኑን አስቀምጧል ። የብሪታንያ ሳይታሰብ ባለፈው ሰኔ ከህብረቱ አባልነት መውጣት ህብረቱን ለጊዜውም ቢሆን አስደንግጦ ነበር ። የህብረቱ የወደፊት እጣ ፈንታም ያሰጋቸው ጥቂት አልነበሩም ። የህብረቱ ተቃዋሚዎችም አጋጣሚውን በመጠቀም ህብረቱ አበቃለት የሚል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል ።አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት መወሰኗን በመደገፍ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ይሰጡ የነበረው ፀረ የአውሮፓ ህብረት መግለጫ ህብረቱን ሲያሳስብ ሲያነጋግር የከረመ ጉዳይ ነበር  ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የህብረቱ የወደፊት አቅጣጫ ምን መሆን አለበት አለበት ችግሮስ እንዴት ይፈቱ በሚሉት ነጥቦች  የአባል ሀገራት መሪዎች ሲወያዩ ከቆዩ በኋላ ነው ባለፈው ቅዳሜ የፀደቀውን ሰነድ ያወጡት ።ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት የምትወጣበት ሂደት ከመጀመሩ ከ 4 ቀን በፊት የፀደቀው ይህ ሰነድ የብራሰልስ ቤልጂጉ የአውሮፓ ፖሊሲ ጥናት ማዕከል በምህጻሩ CEPS ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካረል ላኖ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ጠንካራ የሚባል ሰነድ ነው ። በርሳቸው አስተያየት ሰነዱ አውሮጳ ይበልጥ መጠናከሩን ይደግፋል ። 
«ባለፈው ሰኔ የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ድምጹን ከሰጠ በኋላ በአንዳንድ አባል ሀገራትም ሆነ በአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን በኩል በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ አለብን የሚሉ ጥርጣሪዎች ነበሩ ። አሁን ግን በዚህ ሰነድ ቢያንስ 27ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት ህብረቱን ለማጠናከር እና ወደፊት ለመራመድ እንደሚፈልጉ በግልፅ ማስቀመጣቸውን አይተናል ። ወደ ኋላ መመለስም መፍትሄ  እንደማይሆን ነው ያሳዩት ። »
ላኖ እንዳሉት  ሰነዱ በሚቀጥሉት 10 ዓመታትበአገር ውስጥ እና በውጭ ፀጥታ በመከላከያ ፣በእድገት እና በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት እንደሚደርግ ይገልጻል ። መሠረቱ የጋራ እሴት የሆነው የአውሮጳ ህብረት በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ተጨማሪ ሃላፊነቶችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ያስረዳል ። እነዚህና ሌሎችም በሰነዱ የተካተቱ እና ህብረቱ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ቃል የገባባቸው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች እና እቅዶች ሰነዱን ልዩ ያደርጉታል ይላል የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ።አዲሱ ሰነድ የተለያየ የኤኮኖሚ ደረጃ እና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት አባል ሀገሮች እንደ አቅማቸው መጓዝ የሚያስችላቸው አሠራርም ይፈቅዳል ። ይህን አሠራር ሁሉም አባል ሀገራት በመርህ ደረጃ ቢቀበሉትም የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ግን ስጋት አላቸው  ።  እነዚህን ሀገራት ያሰጋው በአዲሱ ሰነድ የተካተተው ይህ አሠራር ከመጀመሪያው ለምን አስፈለገ ? የአውሮፓ ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካረል ላኖ ደግሞ ሰነዱ ያካተተው የዚህ አሰራር መልዕክት ግልጽ ነው ይላሉ ።
«ወደ ኋላ የሚጎተቱ አባል ሀገራት ፣ በጋራ ሊወሰድ የሚገባ እርምጃ ካለ ፣ እነርሱ ሳይጠበቁ የሚፈለገውን ተግባራዊ  ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ ማየት አለባቸው ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጠንካራ አውሮጳ እንዲኖር ከተፈለገ ወይም በአውሮጳ ውስጥም የተጠናከረ ፀጥታ የሚፈለግ ከሆነ ይህን በማይፈልጉት ምክንያት ያሰብነውን ማድረጋችንን አንተውም ለማለት ነው  ።»
ይሁን እና ገበያው እንደሚለው በአባል ሀገራት መካከል ሁለት አይነት አካሄድ የሚፈቅደውን በአዲሱ ሰነድ ውስጥ የተካተተው አሠራር ፣የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት ፣ግዙፍ ኤኮኖሚ ያላቸውን አገራት የበላይነት የሚያሰፍን ፣አለመታተማመንን የሚፈጥር እና ልዩነቱንም የሚያሰፋ ነው ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው ። 
የሮሙ ውል የአልማዝ እዮቤልዩ በተከበረበት በሮም የፀደቀው አዲሱ ሰነድ የህብረቱን ተጠናክሮ መቀጠል የሚያሳይ ቢሆንም በመካከሉ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክስተቶች ሊፈታተኑት እንደሚችሉ ካረል ላኖ  ሳይጠቅሱ አላለፉም  ። 
«ሰነዱ ጥሩ ነው እላለሁ ። ሆኖም እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ማየት አለብን ። ህብረቱ በርካታ ተግዳሮቶች አሉበት ልዩነቶችም አሉ ። በአውሮፓ ህብረት የተለያዩ አመለካከቶች አሉ ። በዚህ ዓመት የሚካሄዱ ትኩረት የሚሰጣቸው ምርጫዎች አሉ ። የፈረንሳይ ምርጫ አለ። የጀርመን ምርጫ አለ ። በኢጣልያም ምርጫ ሊኖር ይችላል ።  በቼክ ሪፐብሊክም እንዲሁ ። የነዚህ ምርጫዎች ውጤት በተወሰነ ደረጃ የተለየ ስሜት ሊፈጥር ይችላል ። ስለዚህ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ የሚጠበቀው ውጤት መገኘት አለመገኘቱ ያኔ የሚታይ ይሆናል ።»

Italien EU Gipfel
ምስል picture-alliance/dpa/A.Tarantino
EU Gipfel Italien
ምስል picture-alliance/AP Photo/A.Medichini

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ