1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት እቅድ እና የሀንጋሪ ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ መስከረም 24 2009

ሀንጋሪያውያን የአውሮጳ ኅብረት ፣ አባል ሀገራት ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ ባወጣው እቅድ ላይ ከትናንት በስተያ የሰጡት ድምፅ ውድቅ ሆኗል። ከድምፅ ሰጭዎቹ አብዛኛዎቹ እቅዱን ቢቃወሙም ድምጹን ለመስጠት የወጣው ህዝብ ቁጥር ከ50 በመቶ በማነሱ ህዝበ ውሳኔው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። መንግሥታት ግን አሁንም የህብረቱን እቅድ መቃወሙን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2Qs5N
Ungarn Premierminister Viktor Orban gibt seine Stimme beim Referendum ab
ምስል picture-alliance/dpa/S. Koszticsak


 መሀል አውሮጳ የምትገኘው ሀንጋሪ ሰባት ሀገሮች ያዋስኗታል። በስተሰሜን ስሎቫክያ ፣ በስተሰሜን ምዕራብ ኦስትሪያ፣ በስተምዕራብ ስሎቬንያ፣ በስተደቡብ ምዕራብ ክሮኤሽያ እና በስተደቡብ ሰርቢያ ፣ በስተምሥራቅ ሩሜንያ በስተሰሜን ምሥራቅ ደግሞ ዩክሬን። ሀንጋሪ የአሁኑን ድንበርዋን የያዘችው ከግዛትዋ 71 በመቶውን፣ ከህዝብዋ ደግሞ 58 በመቶውን ካሳጣት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል። ከጦርነቱ  በኋላ በኮሚንስቶች ጎራ ስር የወደቀችው ሀንጋሪ የምሥራቁ ጎራ ሲፈረካከስ በጥቅምት 1989 ዴሞክራሲያዊ  ምክርቤታዊ ሪፐብሊክ ሆነች። በጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ,ም  የአዉሮጳ ኅብረት የሆነችው ሀንጋሪ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት ። ከጎርጎሮሳዊው 2010 ወዲህ የሀገሪቱን ፖለቲካ የሚመራው ከሀንጋሪ ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛው በአጭሩ «ፊዴስ» የቀድሞው  የወጣት ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ የአሁኑ «የሀንጋሪ ሲቪክ ኅብረት»  ፓርቲ ነው ። የቀድሞው ኮምኒስት የአሁኑ ወግ አጥባቂው የፓርቲው መሪ ቪክቶር ኦርባን የአውሮጳ ኅብረትን የፍልሰት መርህ ከሚቃወሙ ከቀድሞ ኮምኒስት የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት መሪዎች አንዱ ናቸው ። የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ድንበር በሚባሉት ግሪክ እና ኢጣልያን በመሳሰሉ ሀገራት የሚገኙ ስደተኞችን አባል ሀገራት እንዲከፋፈሉ በጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አሳሳቢነት የአውሮጳ ኅብረት ያወጣውን እና አብዛኛዎቹ አባል ሀገራት የደገፉትን እቅድም አጥብቀው ይቃወማሉ ። በዚሁ መሠረት ኦርባን የህዝባቸውን ፍላጎት ለማሳወቅ በሚል ባለፈው እሁድ በእቅዱ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ቢያደርጉም ምኞታቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳካት አልቻሉም ። ድምፅ ለመስጠት ከወጡት ሀንጋርያውያን 98 .3 በመቶው ወይም 3.2 ሚሊዮኑ እቅዱን ተቃውመዋል ። ይሁንና ድምጽ የሰጠው ህዝብ ቁጥር 39.9 በመቶ ብቻ በመሆኑ ህዝበ ውሳኔው ውድቅ ተደርጓል ።ያም ሆኖ ኦርባን ለፓርቲያቸው ለፊዴስዝ ደጋፊዎች ባሰሙት ንግግር ውጤቱን እጹብ ድንቅ ብለውታል ። ኦርባን ሽንፈታቸውን ለህዝቡ ያቀረቡት እንደ ድል ነው  ። በንግግራቸው የህዝበ ውሳኔውን ተቀባይነት አለማግኘት ግን ፈጽሞ አላነሱም ።
«ትናንት ሀንጋርያውያን ታሪክ ጽፈዋል ። አሸናፊዎቹ ታሪክ መጻፋቸው እውነት ከሆነ እምቢ ሲሉ ድምጻቸውን የሰጡት በአብላጫ ድምጻቸው ድል ተቀዳጅተዋል »
ሀንጋሪ ባለፈው ዓመት በርካታ ስደተኞች ወደ ሰሜን አውሮጳ የተሸጋገሩባት ሀገር ናት ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ ስደተኛ በገባበት ባለፈው ዓመት ድንበሯን በመዝጋት የመጀመሪያዋ የምሥራቅ አውሮጳ ሀገር ናት ። እርምጃው በአውሮጳ ኅብረት ቢወገዝም የሀንጋሪ መንግሥት ከዚህ አቋሙ አሁንም ፍንክች አላለም ።ከእሁዱ ህዝበ ውሳኔ በኋላም ኦርባን ግባቸውን ለማሳካት በመጪዎቹ ቀናት ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ህጎችን እንደሚያወጡ እና እንደሚሰሩም አስታውቀዋል ።ኦርባን መንግሥታቸው አሁንም የህብረቱን እቅድ መቃወሙን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
« ለተጨማሪ ትግል መዘጋጀት አለብን ። አሁን ኳሷ በብራሰልስ ሜዳ ላይ ነው የምትገኘው ። ጥያቄው ብራሰልስ አሁን የብዙሃኑን ውሳኔ ይቀበላል አይቀበልም ነው ።»
የኦርባንን ማስፈራሪያ እና አዝማሚያቸውን የብራሰልስ ባለሥልጣናት እንደ ዋዛ አላለፉትም  ። የአዉሮጳ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ማርቲን ሹልትስ   ኦርባን« የአውሮጳ ኅብረት ውሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በሀገር ውስጥ ሥልጣናቸውን ለማራዘም የጀመሩት ጨዋታ አደገኛ ነው » ሲሉ እሁድ አስጠንቅቀዋል ።ሀንጋሪያውያን ለኦርባን ጥሪ ትኩረት አልሰጡም ያሉት ሹልትስ አሁን የአውሮጳ ኅብረት የሚያስፈልገው መፍትሄ የሚያስገኝ ውይይት እንጂ ሰው ሰራሽ ውጥረት አይደለም ሲሉም አሳስበዋል ።  ኦርባን እጅግ በጣም ጥሩ ያሉትን የህዝበ ውሳኔ ውጤት የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት አሌክዛንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ ፣ኦርባን በጥፊ የተመቱ ያህል የሚቆጠር ነው ሲሉ አጣጥለውታል ።
«እጅግ ዝቅተኛው የምርጫ ተሳትፎ ፣ የሌሎችን መብት የሚጋፉ ህዝበ ውሳኔዎች፣ የአውሮጳ ፖለቲካ የሚካሄድበት መንገድ አለመሆኑን በድጋሚ ያሳያል ። እዚህ ጥያቄው ህዝበ ውሳኔ ሳይሆን አንድ አምባገነን መሪ ለፀረ-የውጭ ዜጋ መርሁ ምኞት እና ፍላጎት ማረጋጋጫ ማግኘት ነበር ። የተገኘው ውጤት ግን አሳፋሪ ነበር  ።»
የአውሮጳ ኅብረት  ኢጣልያ እና ግሪክ ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ስደተኞች 160 ሺሁን በሌሎች አባል ሀገራት ለማስፈር  ባለፈው ዓመት ከአባል ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ ቢደረስም እስካሁን ማስፈር የቻለው 5651 ዱን ብቻ ነው ።ህብረቱ እስከ መጪው የጎርጎሮሳውያኑ 2017 ዓም መጨረሻ ደግሞ 30 ሺህ ያህሉን ለአባላቱ ለማከፋፈል አቅዷል ። የህብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት ሀንጋሪ 1300 ስደተኞችን መቀበል አለባት ።  ሀንጋሪ ግን ይህን በመቃወም አቤቱታዋን ለአዉሮጳ የበላይ ፍርድ ቤት አቅርባ ነበር ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በእቅዱ ላይ ህዝበ ውሳኔ ጠራች ። ሀንጋሪያዊው የፖለቲካ ሳይንቲስ ጋቦር ቶሮክ አሁን ሊተኮርበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ ውጤቱ ነው ይላሉ ።
«ህዝበ ውሳኔ ምን እንደሆነ መርሳት የለብንም ። የተጻፈው መልዕክት ለብራሰልስ የሚል ነው ። መልዕክቱ ግን ምንድነው ? መልዕክቱ ህዝበ ውሳኔው ዋጋ ቢስ መሆኑ ነው ።»
ውድቅ ከሆነው ህዝበ ውሳኔ በኋላ ተቃዋሚዎቹ የግራ እና የቀኝ ፓርቲዎች ኦርባን ከሥልጣን ይውረዱ እያሉ ነው ። ዶቼቬለ በየጎዳናው ያነጋገራቸው ሀንጋርያውያንስ ምን ይላሉ ?
«ይህ አንድነት ነው ። ሀገሪቱ አንድ ላይ ናት »
«ዋናው ነገር ብዙሀኑ ኮታውን እምቢ ሲል ድምጹን መስጠቱ ነው ።»
«60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለህዝበ-ውሳኔው ደንታ አልነበረውም ወይም በጥያቄው አልተስማማም ።»
እኚህ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ኦርባን እስካሁን ከተናገሩት በላይ የህዝበ ውሳኔው ውጤት ሊያመጣ የሚችለውን ነገር ያብራሩልን ሲሉ ጠይቀዋል ።
«ቪክቶር ኦርባን ውጤቱ በብራሰልስ ምን እንደሚያስከትል አንድ የተጨበጠ ነገር መናገር ከቻሉ የበለጠ እናውቃለን ። ማንም ምንም እስካልተናገረ ድረስ እኛ የምናውቀው ህዝበ ውሳኔው ተቀባይነት እንደሌለው ነው ።»
ተቃዋሚዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች ህዝቡ ድምጹን ለመስጠት እንዳይወጣ ሲቀሰቅሱ ነበር ። ከተሰጠው ድምፅም ከ230 ሺህ በላይ የሚሆነው ተቀባይነት አላገኘም ። ከህዝበ ውሳኔው በፊት መንግሥት ለቅስቀሳ የተጠቀመባቸው የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ስደተኞችን ከአሸባሪነት እና ከወንጀል ጋር የሚያያዙ ነበሩ ።ፍለስት ደግሞ መርዝ ተደርጎ ነበር የሚቀርበው ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩመን ራይትስ ዋች እጅግ ተጋግሎ ይካሄድ የነበረውን ይህን የኦርባን መንግሥትን የውጭ ዜጎች ጥላቻ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ ተችቷል ።  ሀንጋርያውያን አብዛኛው ህዝብ ስለ መጻኤ እድሉ አለመጨነቁ አሳስቧቸዋል ። ከጎርጎሮሳዊው 2010 አንስቶ ሀንጋሪን የሚመሩት ኦርባን የእሁዱን ህዝበ ውሳኔ ውጤት በፖለቲካ አጀንዳቸው ውስጥ ፍልሰትን አንዱ ጉዳይ አድርገው ለማቅረብ ይጠቀሙበታል የሚል ግምት አለ ።ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በጀመሩት እሰጣ ገባ የቀጠሉት ኦርባን ግባቸውን ለማሳካት እወስዳለሁ ያሏቸው እርምጃዎች በርካታ ትችቶች እየተሰነዘሩባቸው ነው ።

Ungarn Referendum
ምስል picture-alliance/dpa/N. Bruzak
Ungarn Referendum
ምስል picture-alliance/AP Photo/V. Ghirda
Ungarn Orban gibt Statement zum Referendum ab
ምስል Reuters/L. Balogh

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ